በስደት በኬንያ ናይሮቢ የሚገኘው ጋዜጠኛና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ያዕቆብ ያታኔ ትናንት በመኖሪያ ቤቱ ህይወቱ አልፎ መገኘቱን የዓይን ምስክሮች ለ WT Media ገልጿል።
ከደቡብ ኢትዮጵያ (ኮንሶ) ተሰዶ በናይሮቢ በስደት ይኖር የነበረው ያዕቆብ ያታኔ፣ በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያና አካባቢው የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በማጋለጥና ስለ ወገኖቹ ድምፅ በመሆን የሚታወቅ ብርቱ ጋዜጠኛ ነበር።
የጋዜጠኛው የሞት ዜና ከተሰማ በኋላ በስደት የሚገኙ የሙያ አጋሮቹና ወዳጆቹ ከፍተኛ ድንጋጤ የገጠማቸው ሲሆን፣ በተለይ በስደት ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰው ዛቻና ስጋት በጨመረበት በዚህ ወቅት የያዕቆብ ሞት “ጥልቅ ምርመራ ያስፈልገዋል” የሚሉ ድምፆች እየበረከቱ ይገኛሉ።
የኬንያ ፖሊስና የሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች በጋዜጠኛው ሞት ዙሪያ ገለልተኛና ፈጣን ምርመራ እንዲያደርጉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅቶችና የሙያ አጋሮቹ ጥሪ አቅርበዋል።
WT Media ለጋዜጠኛ ያዕቆብ ያታኔ ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች በሙሉ መጽናናትን ይመኛል።
የጋዜጠኛውን ሞት መንስኤ በተመለከተ የሚገኙ ተጨማሪ መረጃዎችን ተከታትለን የምናቀርብ ይሆናል።