የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ የተሳነውና በእገታው ዙሪያ ዝምታን የመረጠው የዎላይታ ዞን አመራር ድክመት ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ስለመድረሱ ነዋሪዎች ቅሬታ አቀረቡ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በዎላይታ ዞን እና በሲዳማ ክልል ድንበር ዎላይታ አበላ አባያ፣ ብላቴ ቀበሌ ስድስት ሰዎች መታገታቸውን ተከትሎ፣ የዎላይታ ዞን አመራሮች ወንጀለኞችን ለብላቴ መከላከያ ኃይሎች አሳልፈው መስጠታቸውና የመንግሥት አካላት ለጉዳዩ ምላሽ አለመስጠታቸው ከፍተኛ ውዝግብ አስነስቷል።
ባለፈው አርብ 3 ሚሊሻዎችና 3 ሲቪሎች በማይታወቁ ታጣቂዎች የታገቱት፣ ባለፈው ሐሙስ ዕለት የተፈጸመውን አንድ ክስተት ተከትሎ እንደሆነ መረጃዎች እየጠቆሙ ነው።
ባለፈው ሕዳር ወር በሲዳማ በኩል ዘልቀው በገቡ ታጣቂዎች ከተገደሉት የዎላይታ ምልምል ወታደሮች መካከል አንዱን ገድሏል ተብሎ የተጠረጠረ ግለሰብ፣ ከብላቴ አቅጣጫ ወደ ዎላይታ ድንበር ሲገባ በአካባቢው ነዋሪዎችና በሚሊሻዎች ተይዞ በፓራቾ ፖሊስ ጣቢያ ታስሮ ነበር።
ይህ ግለሰብ በተያዘ በሁለተኛው ቀን ቅዳሜ ዕለት፣ በአካባቢው ስድስት ሰዎች እገታ ተፈጽሞባቸዋል።
የሟች ቤተሰቦችና የዞኑ አመራሮች ጉዳዩን በሕግ አግባብ ለመጨረስ ንግግር ላይ በነበሩበት ወቅት፣ የመከላከያ አመራሮች ጣልቃ በመግባት “የተያዘውን ገዳይና ቀደም ሲል በሶዶ ማረሚያ ቤት የሚገኝ ሌላ ተጠርጣሪን በአስቸኳይ ለብላቴ መከላከያ ግቢ አምጥታችሁ አስረክቡ” የሚል ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው ተገልጿል።
የዎላይታ ዞን አመራሮችም በጉዳዩ ላይ ጠንካራ አቋም ከመያዝ ይልቅ፣ ተጠርጣሪዎቹን ወስደው ማስረከባቸውን የመረጃ ምንጮች አረጋግጠዋል።
ይህም በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ወንጀለኞችን ለማሸሽ የተደረገ ሴራ ተደርጎ ተወስዷል።
WT Media ትናንት የ6ቱ ሰዎች እገታ መፈጸሙን ተከትሎ ሰበር ዜና ማውጣቱ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ ዘገባው ከወጣ በኋላም ሆነ አሁን አዳዲስ መረጃዎች እስከተገኘበት ሰዓት ድረስ የዎላይታ ዞን አስተዳደርም ሆነ የጸጥታ መዋቅሩ፤
እንዲሁም የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ሆነ የሲዳማ ክልል የሚመለከታቸው አካላት እስካሁን ድረስ ስለ እገታውም ሆነ ስለ ተጠርጣሪዎቹ ርክክብ የሰጡት ምንም ዓይነት ይፋዊ ምላሽ የለም።
የታገቱት ዜጎች የት እንዳሉና በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ አለመታወቁ ቤተሰቦችን ለከፍተኛ ስቃይ ዳርጓል።
በተለይም በለጋ ዕድሜው ለተቀጨው ወታደር ቤተሰቦች ፍትህ ከመስጠት ይልቅ፣ ተጠርጣሪዎችን “በአደራ” በሚል ስም ወደ መከላከያ ግቢ መውሰድ በሕዝቡ ዘንድ የመንግሥትን ታማኝነት ጥያቄ ውስጥ ከትቶታል።
WT Media የዚህን አሳዛኝ ክስተት ሂደትና የሚመለከታቸው አካላትን ዝምታ በጥብቅ እየተከታተለ መረጃዎችን ይፋ ማድረጉን ይቀጥላል።
🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏
Voice of Marginalized Community – WT Media