ከ4 ዓማት በፊት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 1264/2014 ጥሎት የነበረውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሙሉ በሙሉ እንዲነሳ በአብላጫ ድምፅ መወሰኑ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ ይህ በሀገር ደረጃ እንዲሻር የተደረገው ሕግ በዎላይታ ሶዶ ከተማ ተግባራዊ አለመሆኑና በሕዝብ እንቅስቃሴ ላይ የተጣለው የጊዜ ገደብ በነዋሪዎች፣ በነጋዴዎችና በትራንስፖርት ዘርፍ ተሰማርተው በሚገኙ ዜጎች ላይ ከፍተኛ ቅሬታና እንግልት እየፈጠረ ይገኛል።
የ WT Media የሪፖርተር ቡድን በዎላይታ ሶዶ ከተማ ላይ የአዋጁን ተፈጻሚነት በተመለከተ በምሽት ተዘዋውሮ ባደረገው የመስክ ቅኝትና ከሕብረተሰቡ ክፍሎች በሰበሰበው አስተያየት በከተማዋ በአሁኑ ወቅት የሞተር ሳይክል እንቅስቃሴ እስከ ምሽቱ 12:00 ሰዓት ጥቂት ከተፈቀደላቸው ውጪ የባጃጅ ትራንስፖርት ደግሞ እስከ ምሽቱ 3:00 ሰዓት ብቻ እንዲንቀሳቀሱ ገደብ ተጥሎባቸዋል።

ይህንን የጊዜ ገደብ አሳልፈዋል የተባሉ የትራንስፖርት አሽከርካሪዎችና ተጠቃሚ ዜጎች በጸጥታ ኃይሎች አማካኝነት ያልተገባ ወከባና ከባድ ሰብዓዊ የመብት ጥሰት እንደሚደርስባቸው፣ የአካልና የሞራል ጉዳት እንደሚደርስባቸው እንዲሁም በንብረቶቻቸው (በሞተርና ባጃጆች) ላይ ጉዳት እየተደረሰ መሆኑን ነዋሪዎቹ በምሬት ተናግረዋል።
አስተያየታቸውን ለ WT Media የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች እንዳሉት መንግሥት በአገር ደረጃ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያነሳው በመላ ሀገሪቱ የተሻለ ሰላምና ጸጥታ መኖሩን በማመንና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው እንዲነቃቃ ታስቦ ነው።
ይሁን እንጂ በሶዶ ከተማ ሌላ የትራንስፖርት አማራጭ በብዛት በሌለበት ሁኔታ ይህ ዓይነቱ ገደብ መቀጠሉ አግባብ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
”የጊዜ ገደብ መጣሉ ለዕለት ተዕለት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ማኅበራዊና ድንገተኛ የጤና ችግሮች ምክንያት በምሽት ወደ ሕክምና ተቋማት በፍጥነት ለመድረስ ለሚፈልጉ ዜጎች ትልቅ እንቅፋት እየሆነ ነው” ሲሉ ነዋሪዎቹ አስረድተዋል።
ነዋሪዎቹ አክለውም፣ ምሽትን ተገን በማድረግ በሞተርና በባጃጅ ሕገ-ወጥ ድርጊት የሚፈጽሙ ጥቂት ግለሰቦች ሊኖሩ እንደሚችሉ በመጠቆም፤ “ይህንን ችግር የአካባቢው መስተዳድር ከጸጥታ መዋቅሩና ከሕብረተሰቡ ጋር በቅንጅት በመሥራት በመደበኛው ሕግ መከላከልና መቆጣጠር አለበት እንጂ ጥቂት ሕገ-ወጦችን ለመከላከል በሚል ሰላማዊውን ሕዝብና መላውን የከተማዋን ኢኮኖሚ የሚጎዳ ገደብ ሊጣል አይገባም” ሲሉ በጥብቅ አሳስበዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ይህ ዓይነቱ የተለየ የጊዜ ገደብና በምሽት የሚደረግ ወከባ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ ከዎላይታ ውጭ ባሉ በአቅራቢያው በሚገኙ ሌሎች ከተሞች ላይ ተፈጻሚ አለመደረጉ የሕግ አፈጻጸሙን አድሏዊና አሻሚ አድርጎታል።
ከአራት ዓመት በፊት በመላው ሀገር ደረጃ በምክር ቤት የጸደቀ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሌለበትና በተሻረበት ሁኔታ በዎላይታ ሶዶ ከተማ በባጃጅና በሞተር ላይ ብቻ ተለይቶ በምን ሕጋዊ አግባብና መመሪያ የጊዜ ገደብ እንዲጣል እየተደረገ እንደሆነ ከሚመለከታቸው የከተማዋና የዞኑ የጸጥታ መሥሪያ ቤቶች መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።