GridArt_20260623_184151435

ከአንድ ወር በፊት WT Media በሐዋሳ ከተማ እየተገነባ ስላለው የ”ሐይቅ ዳር ልማት ፕሮጀክት” እና ተያይዞ ስለሚነሳው የነዋሪዎች መፈናቀል ስጋት መዘገቡ ይታወሳል።

WT Media ጉዳዩን በቅርበት መከታተሉን በመቀጠል በአሁኑ ወቅት በተለምዶ ኃይቅ ዳር ቁጥር 1 እና ቁጥር 2 መንደር ነዋሪዎች በቀጥታ ለጣቢያችን የሰጡትን የድምፅ ምስክርነት እና ያቀረቧቸውን ይፋዊ የሕግ አቤቱታዎች በማስረጃነት በመያዝ ይህንን ተከታታይ ዝርዝር ዘገባ አውጥቷል።

​ነዋሪዎቹ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የሐዋሳ ቅርንጫፍ እና ለሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ቢሮ ያስገቧቸው ይፋዊ ሰነዶች እና  ለ WT Media የደረሱት የድምፅ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ያለ ምንም ምትክ ቦታ እና ፍትሐዊ ካሳ ከአርባ እና ሃምሳ ዓመታት በላይ ከኖሩበት ቀያቸው በአስቸኳይ እንዲነሱ ታዘዋል።

በጉዳዩ ላይ የሐዋሳ ከተማ አስተዳደርን እና የሚመለከታቸውን የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ኃላፊዎችን ለማግኘት WT Media በተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም ለጊዜው ሳይሳካ ቀርቷል።

​ቀደም ሲል የተፈናቃዮች ቁጥር 200 አባወራዎች ተብሎ የተገመተ ቢሆንም ነዋሪዎቹ ለ WT Media በሰጡት ቀጥተኛ የድምፅ መረጃ አሁን ላይ ቁጥሩ እጅግ ጨምሮ ከ300 በላይ የሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን እንደሚያካትት አረጋግጠዋል።

አብዛኛዎቹ ተፈናቃዮች የዎላይታ ማኅበረሰብ አባላት መሆናቸውን የገለጹት ምስክሮቹ ድምፃቸው እየታፈነ መሆኑን በምሬት ያስረዳሉ።

​ነዋሪዎቹ ለሐዋሳ ከተማ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት በይፋ ባስገቡት ሰነዶች መሠረት በአካባቢው ከ52 ዓመታት በላይ የኖሩ መሆናቸውን ያስረዳሉ።

በሰነዱ ላይ እንደተጠቀሰው ነዋሪዎቹ እስከ 2000 ዓ.ም. ድረስ መደበኛ የመሬትና የእርሻ ግብር ሲከፍሉ የቆዩ ቢሆንም ከዚያ በኋላ በአስተዳደሩ በኩል “የከተማ መሬት አይገብርም” በሚል መመሪያ ግብር እንዳይከፍሉ መከልከላቸውንና የዓመታት የግብር ደረሰኞች በሙሉ በየነዋሪው እጅ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

​ነዋሪዎቹ የመኖሪያ ቤት ቁጥር የተሰጣቸው የኤሌክትሪክ መስመር እና የውኃ አቅርቦትን በራሳቸው ወጪ ያስገቡ ከመሆኑም በላይ በአካባቢው የሚገኘውን የብልጽግና ቢሮ ግንባታ ሳይቀር 100% በራሳቸው ማኅበረሰብ መዋጮ ማከናወናቸውን በሰነዱ ጠቅሰዋል።
​
​ በተያያዘው ይፋዊ ሰነድ እንደተመለከተው ነዋሪዎቹ ወደ አዋሳ ከተማ ማዘጋጃ ቤት እና ወደ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አስተዳደር በመሄድ ቅሬታቸውን ለማቅረብ ቢሞክሩም ሰብዓዊ ምላሽ አላገኙም።

በተለይም አቶ ቸርነት የተባሉ የከተማው ማዘጋጃ ቤት ኃላፊ እና የአካባቢ ጥበቃና ጸጥታ ኃላፊዎች ነዋሪዎቹ አካባቢውን በአስቸኳይ እንዲለቁ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

በመልካም አስተዳደር ዘርፍ ከአቶ ብርሃኑ ጋር በተደረገ ንግግርም “እኛ አካባቢውን ነጻ አድርጉ ስንል ሕዝቡን በትኑ ማለታችን አይደለም፤ ነገር ግን ኮሚቴው የሰጣችሁን ምላሽ ተቀበሉ” የሚል የተድበሰበሰ ምላሽ እንደተሰጣቸው ነዋሪዎቹ በድምፅ ምስክርነታቸው ገልጸዋል።

“ከንቲባው መልካም ሰው ናቸው ቢባልም እንድናገኘው ተከልክለናል” ሲሉም ያክላሉ።

​ነዋሪዎቹ ልማቱን በመርህ ደረጃ እንደሚደግፉ በሰነዱ ቢገልጹም በአጠቃላይ 1.5 ቢሊዮን ብር እንደሚፈጅና በሶስት ዙሮች እንደሚሠራ ከሚዲያ የሰሙት ይኸው የ”ሀይቅ ዳር ልማት” ፕሮጀክት አሁን በደረሰበት 3ኛ ዙር ላይ ያለ ምንም ቅድመ ዝግጅት “እስከ አርብ ድረስ ለቃችሁ ውጡ” የሚል አስገዳጅ ትዕዛዝ አስተላልፎባቸዋል።

ባለፈው አርብ ሰኔ 12 ቀን 2018 ዓ.ም. የተሰጠው የጊዜ ገደብ የመጨረሻ ቀን መሆኑን ተከትሎ በአካባቢው የሚገኙ የ8ኛ እና የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ተፈታኝ ተማሪዎች በትምህርታቸው ላይ ከፍተኛ የስነ-ልቦና እና የዕድል ስጋት ወድቆባቸዋል።

አስተዳደሩ “የዕቃ ማጓጓዣ ገንዘብ እንሰጣችኋለን እናንተ ግን የቤት ኪራይ ፈልጋችሁ ውጡ” ማለቱን የገለጹት ነዋሪዎች በአሁኑ ወቅት በሐዋሳ ከተማ ቤት መከራየት እጅግ አስቸጋሪ እና ውድ በመሆኑ ወደ ሜዳ የመውጣት አደጋ እንደተደቀነባቸውም ለ WT Media በዕንባ ያስረዳሉ።

​ነዋሪዎቹ በሰነዶቻቸው ላይ የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር እየወሰደ ያለው እርምጃ የሀገሪቱን የበላይ ሕግጋት የጣሰ መሆኑን በነጥብ አስፍረዋል።

​የኢፌድሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 40(1) ማንኛውም ዜጋ የግል ንብረት ባለቤትነት መብቱ የተጠበቀ መሆኑን ቢደነግግም አስተዳደሩ ቤቶቻቸውን ለማፍረስ መንቀሳቀሱ ሕገ-መንግሥታዊ ጥሰት ነው።

​በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 40(8) እና በመሬት ለሕዝብ ጥቅም የመልቀቅ አዋጅ ቁጥር 1161/2011 (እንዲሁም በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 1307/2016) መሠረት መሬቱ ለልማት የሚፈለግ ቢሆን እንኳ በቅድሚያ ተመጣጣኝ ካሳ ተከፍሎ እና ምትክ መሬት/መኖሪያ ተሰጥቶ መፈጸም ሲገባው ይህ ሳይደረግ በኃይል “ውጡ” መባሉ ሕገ-ወጥ ነው።

​በመሆኑም ነዋሪዎቹ ጉዳዩ በሕግ አግባብ ታይቶ ዕገዳ እስኪሰጥ ድረስ የሚከተሉትን መፍትሔዎች አጥብቀው ጠይቀዋል።

​በሕጉ መሠረት ግልጽና የተሟላ መረጃ ለሕዝቡ እንዲሰጥ፣ ​ፍትሐዊ ካሳ እና ምትክ የመኖሪያ ቦታ/መሬት በቅድሚያ እንዲዘጋጅና ከማህበረሰቡ ጋር ሰብዓዊ ክብርን የጠበቀ ውይይት እንዲካሄድ ጠይቀዋል።

በተጨማሪም ​ማንኛውም እርምጃ ሕጋዊ ሂደቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ እንዲቆምም ተማፅነዋል።

​ይህ ይፋዊ የአቤቱታ ሰነድ ለፍላደልፊያ ቀበሌ፣ ለአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አስተዳደር፣ ለኢፌድሪ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና ለሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በግልባጭ (CC) ደርሷል።

WT Media ከከተማው አስተዳደር በኩል ምላሽ ለማግኘት የሚያደርገውን ጥረት አሁንም የሚቀጥል ሲሆን አዳዲስ መረጃዎችን እንደደረሱት ለሕዝብ ይፋ ያደርጋል።

🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏

Voice of Marginalized Community – WT Media