GridArt_20260629_164509305


በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በዎላይታ ዞን ቦዲቲ ከተማ በሀሰተኛ ትንቢት እና “ተፈውሰሻል፣ ወደ ህክምና መሄድ አያስፈልግሽም” በሚል የተሳሳተ ምክር ምክንያት የአንዲት ወጣት እናት ህይወት ማለፉ በማህበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ሀዘንንና ቁጣን ቀስቅሷል።

​የቅርብ ወዳጆቿ ለ WT Media እንደገለጹት ህይወቷ ያለፈው እናት ታክማ መዳን የሚችል የጤና እክል የነበረባት ቢሆንም፣ በአካባቢው “የእምነት መሪዎችና ነቢያት ነን” በሚሉ አካላት በተሰጣት የሀሰት ማረጋገጫ ምክንያት ወደ ህክምና ተቋም እንዳትሄድ ተደርጋለች።

“ከዚህ በኋላ ወደ ሀኪም ቤት መሄድ አያስፈልግሽም” በሚል ክልከላ እምነቷን ተጠቅመው ህክምናዋን እንድታቋርጥ ማድረጋቸው በመጨረሻም ለሞት ዳርጓታል።

​ይህንን ክስተት ተከትሎ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች እና የሟች ወዳጆች ድርጊቱን በጽኑ አውግዘዋል።

ፈጣሪ ለሰው ልጅ የሰጠው እውቀትና የህክምና ጥበብ ህይወትን ለመታደግ እንጂ ለመከልከል እንዳልሆነ በመጥቀስ በእምነት ስም የሚነገሩ የሀሰት ትንቢቶችና ከመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ውጭ የሆኑ አካሄዶች በአስቸኳይ ሃይ ሊባሉ እንደሚገባ አሳስበዋል።

​የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት እግዚአብሔር ያልተናገረውን “ተናግሯል” በማለት ከምእመናን ገንዘብ ለመሰብሰብ እና የውሸት ተስፋ በመስጠት የሰዎችን ህይወት አደጋ ላይ የሚጥሉ ሀሰተኞች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።

ይህ አሳዛኝ ክስተት ማህበረሰቡ ከመቼውም ጊዜ በላይ እንዲነቃ እና መሰል ድርጊቶችን በጋራ እንዲከላከል ጥሪ አስተላልፏል።

​በዚህ አሰቃቂ ክስተት ምክንያት ህይወቷ ለቀጠፈው ወጣት እናት ፈጣሪ ነፍሷን በሰላም እንዲያሳርፍ፣ ለልጆቿ፣ ለቤተሰቦቿ እና ለቅርብ ወዳጆቿ በሙሉ መጽናናትን እንመኛለን።