GridArt_20260630_195246979

በዎላይታ ዞን የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም “አመራሮች ከእያንዳንዱ ተፈናቃይ እያስገደዱ ገንዘብ እየተቀበሉና ቤተሰቦቻቸውን በማስፈር መሬት እየሸጡ ነው” ሲሉ ተጎጂዎች ቅሬታ አቅርቧል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፥ በዎላይታ ዞን ካዎ ኮይሻ ወረዳ በደረሰው ድንገተኛ የመሬት መንሸራተትና ናዳ አደጋ ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ንጹሐን ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም የተዘጋጀውን መሬት የወረዳው ከፍተኛ አመራሮችና በአጋርነት ያደራጇቸው ደላሎች የከፍተኛ ሙስና እና የዘመድ አዝማድ መጠቀሚያ ማድረጋቸውን WT Media ያደረገው ልዩ የምርመራ ዘገባ አጋልጧል።

በሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም በዎላይታ ዞን ካዎ ኮይሻ ወረዳ በተከሰተው በድንገተኛ መሬት መንሸራተት እና ናዳ ምክንያት ከቀያቸው ለተፈናቀሉት ወገኖች በአበላ አባያ ወረዳ አባያ ጮካሬ ጥጣ መንደር ላይ ሠፈራ ጣቢያ ተዘጋጅቶ በዘላቂነት የማስፈር ተግባር እየተሰራ መሆኑ ይታወሳል።

ሆኖም ግን ​በምርመራው የተገኘ ተጨባጭ የባንክ ትራንዛክሽን ሰነዶች በእጅ የተጻፉ ይፋዊ አቤቱታዎች እና በተጎጂዎች የተሰጡ የድምፅ ምስክርነቶች እንደሚያስረዱት፤ በካዎ ኮይሻ ወረዳ የተንሰራፋው የሙስና መረብ ተፈናቃዮች የመሬት ዕድል እንዲያገኙ ከእያንዳንዱ ሰው 10,000 ብር እጅ መንሻ እየተቀበለ ይገኛል።

​ለWT Media የደረሱት እነኚህ ሚስጥራዊ የምርመራ ማስታወሻዎችና ሰነዶች እንደሚያስረዱት የሙስናው ሰንሰለት የተዋቀረው በከፍተኛ ባለሥልጣናትና በደላላነት በሚንቀሳቀሱ የመንግሥት ባለሙያዎች ነው።

​በዋናነት ስማቸው የተጠቀሰው የካዎ ኮይሻ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ በላቸው ጌታሁን ሲሆኑ እሳቸው ያደራጇቸው ደላላና የግብርና ባለሙያ የሆኑት አቶ ተመስገን ኮሶ ጮራሞ እንዲሁም የብልጽግና ፓርቲ የአመራር አባል የሆኑት አቶ መስፍን ማንዛ እና መሰል ደላሎች በመሆን ተፈናቃዮቹን “10,000 ብር ካልከፈላችሁ ወደ አባላ አባያ የመልሶ ማቋቋሚያ ቦታ አትሄዱም” በማለት ፍጹም ሕገ-ወጥ መስፈርት አስቀምጠዋል።

በዚህም ምክንያት ገንዘብ ያላቸው ተጎጂዎች ጉቦ እየከፈሉ ሲሄዱ አቅም የሌላቸው ድሆች ግን ተስፋ ቆርጠው ሜዳ ላይ ወድቀዋል። የሰጡ አካላት ጭምር የዕድሉ ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻሉ ቅሬታ አቅርበዋል።
​
​የምርመራ ሰነዱ የወረዳውን መዋቅር ይበልጥ የሚያጋልጡ አራት ዋና ዋና የዘመድ አዝማድ ዝርፊያዎችን እንደሚከተለው ያሳያል።

አንደኛው ​የግብርና ባለሙያው አቶ ተመስገን ኮሶ ጮራሞ እናታቸውን ወይዘሮ ዳልቦሬ ደጋፌን በተፈናቃይ ስም መዝግበው በአባላ አባያ የመሬት ዕድል እንዲያገኙ ያደረጉ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ይህንን የተሰጣቸውን የመሬት ቦታ በ150,000 (መቶ አምሳ ሺሕ) ብር ለመሸጥ እየተደራደሩበት ይገኛል ተብሏል።

በተጨማሪም ​አቶ ተመስገን በተመሳሳይ ሁኔታ የኢንሹራንስ ወይም የዕድል ተጠቃሚ በማድረግ የእናታቸውን ወንድም አቶ ዳቃ ደጋፌን በተፈናቃይነት መዝግበው መሬት እንዲወስድ መደረጉን ሰነዱ ያረጋግጣል።

​የካዎ ኮይሻ ወረዳ አመራር የሆኑት አቶ ማንዳዶ ማላኮ የራሳቸውን የ14 ዓመት ታዳጊ ልጅ የመሬት ዕድል እንዲያገኝ ለማድረግ የአባቱን ስም በመቀየር “ያቢስራ ማላኮ ቾሌ” በሚል የሐሰት ስም መዝግበውታል።

ይህ ድርጊት በሕዝብ ጥቆማ ደርሶበት በወረዳው ዋና አስተዳደሪ ውድቅ ተደርጎ ሰሞኑን በወረዳ ደረጃ ግምገማ ቢደረግበትም እስካሁን በአመራሩና በልጃቸው ላይ የተወሰደ አንዳችም ሕጋዊ እርምጃ የለም።

​አቶ ተመስገን ኮሶ ጮራሞ በድጋሚ የቅርብ ዘመዳቸው የሆኑትን የአቶ ኢያሱ ዱባ ሚስት ወይዘሮ ትዕግሥት ባፋን መልምለው አስገብተው የነበረ ቢሆንም ይህኛው ምልመላ በዋና አስተዳዳሪው ውድቅ ተደርጓል።

​የወረዳውን አመራሮችና ደላሎች የሙስና ሰንሰለት እጅ ከፍንጅ የሚይዘው ዋነኛው ማስረጃ ላይ የቀረበው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ (CBE) የገንዘብ ማስተላለፊያ ደረሰኝ ነው።

ይህ የባንክ ሰነድ እንደሚያሳየው ከተጎጂዎች የተሰበሰበው የሙስና ገንዘብ በቀጥታ ወደ ደላላውና የግብርና ባለሙያው አቶ ተመስገን ኮሶ ጮራሞ የባንክ አካውንት በሞባይል ባንኪንግ ገቢ ሆኗል።

​በተጨማሪም የተጻፉ ይፋዊ የአቤቱታ ሰነዶችና የወረዳው ይፋዊ የደብዳቤ ልውውጦች እንደሚያስረዱት፤ ቅሬታ አቅራቢዎቹ የደረሰባቸውን ግፍና የ10,000 ብር እጅ መንሻ ጥያቄ በመቃወም በግንቦት 21 ቀን 2018 ዓ.ም ለወረዳው አስተዳደር በጽሑፍ አቤቱታ ቢያቀርቡም እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት ምላሽና ፍትሕ አልተሰጣቸውም።
​
​የመሬት ናዳ ሥጋት ካለበት አካባቢ እንዲነሱ የተወሰነው በአጠቃላይ ወደ 300 የሚጠጉ አባወራዎች መሆናቸውን ድርጊቱ በክልሉ፣ በዞኑና በአጋር ድርጅቶች እገዛ እየተከናወነ እንደሚገኝ WT Media ከዎላይታ ዞን አደጋ ሥጋትና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

​በመጀመሪያው ዙር 100 አባወራዎች በአበላ አባያ ወረዳ በተዘጋጀው የሰፈራ ጣቢያ ላይ የሰፈሩ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በ2ኛው ዙር ከ70 በላይ አባወራዎችን በተመሳሳይ ቦታ ለማቋቋም የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ ስለመሆኑ ፅህፈት ቤቱ አክለው ገልጿል።

ይሁን እንጂ ይህ በጎ ሥራ በወረዳ አመራሮችና በደላሎች ስግብግብነት ሳቢያ ፍጹም የሙስና መነገጃ መሆኑን የተገኙ መረጃዎችና ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ።

​ለ WT Media በተጨማሪነት እየደረሱ የሚገኙ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በመጀመሪያው ዙር በአባላ አባያ ስፍራው ላይ የሰፈሩት 100 አባወራዎች የተቋቋሙበት ሂደትም በተመሳሳይ መልኩ የተበላሸ ነው።

አብዛኞቹ ሰፋሪዎች በመሰል ሙስና እና በሐሰተኛ ሰነድ የተደራጁ መሆናቸውን፣ እንዲሁም የወረዳው አመራሮች የገዛ ቤተሰቦቻቸውን በመጠቀም ከፍተኛ የሙስና ወንጀል የፈጸሙበት መሆኑን መረጃዎቹ ያረጋግጣሉ።

በመሆኑም አጠቃላይ በመጀመሪያው ዙር በተከናወነው የማቋቋም ሒደት ላይ ጥብቅ የምርመራ ማጣራት እንዲካሄድበት ተጎጂዎችና አካባቢው ማኅበረሰብ ጥሪ አቅርበዋል።

WT Media የደረሱትን የባንክ ሰነዶች፣ ለሚመለከታቸው አካላት የተጻፉ የቅሬታ ደብዳቤዎችንና የድምፅ መረጃዎችን ለጊዜው ወደ ሚዲያ ያላወጣነው ህጋዊ የፍርድ ሂደትን ያሰናክላል፣ የመረጃ ሰጪ ግለሰቦች ተጋላጭነት ለመቀነስ ቀጥታ ለሚመለከተው ፍትህ አካላት አሳልፈን የምንሰጠው ሲሆን ይህንንም መሠረት በማድረግ የዞኑ ፍትሕ መዋቅርና የጸረ-ሙስና ኮሚሽን በተጠያቂዎቹ አመራሮች ላይ የሚወስዱትን ሕጋዊ እርምጃ በቅርበት እየተከታተለ ለሕዝብ ይፋ ማድረጉን ይቀጥላል።