GridArt_20260702_142638482

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የዓመቱን የማጠቃለያ ፈተና እስካሁን መውሰድ እንዳልቻሉ የተማሪ ወላጆች በምሬት ገልጿል።

ፈተናው ሊሰጥ ያልቻለው “መንግሥት የኑሮ ውድነትን ለመደጎም ያደረገው ውዝፍ የደመወዝ ጭማሪ በተሟላ ሁኔታ አልተከፈለንም” ያሉ መምህራን ወደ ትምህርት ገበታቸው ሳይመጡ በመቅረታቸው እንደሆነ ታውቋል።

​የዞኑ አስተዳደር የ2018 ዓ.ም የመስከረም ወር ውዝፍ ክፍያቸውን በ50 በመቶ ብቻ መክፈሉ ቅሬታ እንዳሳደረባቸው የሚናገሩት መምህራኑ ጥያቄያቸው ምላሽ ባለማግኘቱ ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ አለመግባታቸውን ለዶቼ ቬለ አረጋግጠዋል።

​የኮሬ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታረቀኝ በቀለ የመምህራኑ የጥያቄ ተገቢነት ትክክለኛ መሆኑን ያረጋገጡ ሲሆን የዞኑ አስተዳደር በተለያየ አግባብ ካገኘው በጀት ለጉዳዩ ቅድሚያ በመስጠት መምህራንን ጨምሮ ለሁሉም የመንግሥት ሠራተኞች እየከፈለ መቆየቱን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ አሁን ላይ በአስተዳደሩ ባጋጠመው ከፍተኛ የበጀት እጥረት የተነሳ የመስከረም ወር ውዝፍ ክፍያውን ሙሉ በሙሉ መክፈል እንዳልተቻለና በ50 በመቶ ብቻ የተወሰነበት ምክንያት ይህው መሆኑን አስረድተዋል።

​ቀሪውን 50 በመቶ ክፍያ ለመፈጸም ዞኑ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ አማራጮችን እያፈላለገ እንደሚገኝ የጠቀሱት ዋና አስተዳዳሪው በማኅበረሰቡ ዘንድ እየተናፈሰ ያለውን ወሬ አስተባብለዋል።

​“የፌዴራል መንግሥት የመስከረም ወር ውዝፍ ክፍያ ገንዘብ ልኮ እያለ የዞኑ አስተዳደር ለሌላ ዓላማ አውሎታል የሚል የተሳሳተ ሐሳብ አለ። ይህ ፍጹሞ ሐሰት ነው” ብለዋል።
​
​መምህራኑ የወሰዱት ከሥራ የመቅረት እርምጃ ንጹሐን ተማሪዎችንና ወላጆችን የሚጎዳ መሆኑን የገለጹት አቶ ታረቀኝ፤ በአሁኑ ወቅት የመምህራኑን ጥያቄ በሒደት ለመመለስና ተማሪዎችም የተቋረጠውን ፈተናቸውን በአስቸኳይ እንዲወስዱ ለማድረግ ከአስተማሪዎችና ከወላጆች ጋር የጋራ ምክክር እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

​አስተዳደሩ “በቅርቡ ከመግባባት ላይ እንደርሳለን ብለን እንገምታለን” ሲል የገለጸ ቢሆንም ወላጆች ግን የልጆቻቸው የትምህርት ዘመን እንዳይስተጓጎል ጉዳዩ በአስቸኳይ እልባት እንዲያገኝ በከፍተኛ ስጋት እየጠየቁ ይገኛሉ።