በዎላይታ በግዙፍ እንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብቶች ለአመታት ግብር ሳይከፍሉ መሬቱን አስይዘው በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ከባንክ መውሰዳቸው ተገልጿል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የዎላይታ ዞን ገቢዎች መምሪያ እና የንግድና ገበያ ልማት መምሪያ በጋራ በመሆን ባዘጋጁት የ2018 ዓ.ም የግብር ዘመን የታክስ አሰባሰብና የ2019 በጀት ዓመት የንግድ ፈቃድ ዕድሳት ንቅናቄ ግምገማ መድረክ ላይ በዞኑ የሚንቀሳቀሱ ታዋቂ ባለሀብቶችና ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሮች የተሳተፉበት አሳዛኝና አስደንጋጭ የኢንቨስትመንት ሌብነት ይፋ ሆኗል።
ለ WT Media የደረሱት ተጨባጭ የምርመራ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ሥራ አጥ ወጣቶች ባሉበት በዚሁ ዞን ግዙፍ የኢንቨስትመንት መሬቶችን የተረከቡ ባለሀብቶች ለዓመታት ግብር ከመከልከላቸውም በላይ የሕዝብ መሬትን ለባንክ በማስያዝ ቢሊዮን ብር በመበደር እንዲሁም ከጎረቤት ክልል ከፍተኛ አመራሮች ጋር በጥቅም በመተሳሰር የዞኑን ወል መሬትና ሉዓላዊ ወሰን አሳልፈው እየሰጡ ይገኛሉ።

(በአጠቃላይ የቀድሞው የአባያ እርሻ ልማት ይዞታ 1,262 ሄክታር ሲሆን የባለሀብት በረከት ይዞታ 1,540 ሄክታር ነው፤ የሁለቱ ድምር ብቻ 2,800 ሄክታር የዎላይታ ለም መሬት በእነዚህ ባለሀብቶች እጅ ይገኛል)።
በመድረኩ ላይ በስፋት ከተነሱት ጉዳዮች መካከል የባለሀብት በረከት አደራ (በረከት ገበረዋ) የኢንቨስትመንት ይዞታ ዋነኛው ነው። ይህች ባለሀብት ከዎላይታ ዞን ሰፊ መሬት (ከ600 በላይ ሄክታር እንዲሁም በጥቅል ይዞታው 1,540 ሄክታር የሚደርስ) በመውሰድ ከፍተኛ ምርት እያመረተች ቢሆንም ለዞኑ አግባብ የሆነውን ግብር ሳትከፍል መቆየቷ ተገልጿል።
ለጊዜው በእርሻው ውስጥ የሚሰሩ የሠራተኞች ቁጥር በትክክል ያልተገለጸ ሲሆን በርግጥ ባለሀብቷ አንዳችም መረጃ ለዎላይታ ዞን ለመስጠት ፈቃደኛ እንዳልሆነች የአባላ አባያ ወረዳ ገቢዎች ጽሕፈት ቤት በግምገማ መድረኩ ላይ ግልጽ አድርጓል።
የአባላ አባያ ወረዳ ገቢዎች ጽሕፈት ቤት ይፋ እንዳደረገው በረከት ገበረዋ “ግብር አልከፍልም” በማለቷ ፍርድ ቤት ከተከሰሰች በኋላ በፍርድ ቤት የተወሰነባትን የ2 ዓመት የኢንቨስትመንት እና የተቀጣሪ ሠራተኞች የደሞዝ ሥራ ግብር ጭምር ሳትከፍል በአሁኑ ወቅት አካባቢውን ለቅቃ ጠፍታለች።
ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢና አስደንጋጭ የሚያደርገው ግን ይህ ብቻ አይደለም፤ ባለሀብቷ ይህንን የወሰደችውን የሕዝብ መሬት በዋስትናነት ለባንክ በማስያዝ ከባንክ ወደ አንድ ቢሊዮን የሚጠጋ ከፍተኛ ገንዘብ ተበድራ መጥፋቷ በመድረኩ ላይ ይፋ ሆኗል።
ከዚህም በተጨማሪ በሕግ ከተሰጣት ይዞታ ውጪ በማን አለባኝነት በአካባቢው የሚገኘውን የሕዝብ ወል መሬት ጭምር ወደ ራሷ ይዞታ እያካለለች መሆኑ ተጋልጧል።
ይሁን እንጂ ይህንን በግልጽ እየተፈጸመ ያለ ዝርፊያ ደፍሮ “ለምን ግብር አትከፍይም? የሕዝብስ መሬት እንዴት ለባንክ ይያዛል?” ብሎ የጠየቃት አንድም የወረዳም ሆነ የዞን አመራር የለም።
ማኅበረሰቡ ይህ መሬት በአስቸኳይ ተነጥቆ ለዞኑ ተመላሽ እንዲደረግና ለሥራ አጥ ወጣቶች እንዲሰጥ ተከታታይ የሕዝብ ጫና ሊፈጠር እንደሚገባ አሳስቧል።
ሌላው ስማቸው በከፍተኛ ሁኔታ የተነሳው ባለሀብት አቶ ዳኜ ዳባ ሲሆኑ/ ግለሰቡ እስካሁን ባለው ሂደት ለዞኑ አንድም ቀን ግብር ከፍለው እንደማያውቁ የወረዳው ገቢዎች ጽሕፈት ቤት በይፋ አጋልጧል።
አቶ ዳኜ የተቀጣሪዎች ደሞዝ ግብር የኢንቨስትመንት ግብር እንዲሁም የመሬት መጠቀሚያ ኪራይ በተደጋጋሚ ቢጠየቁም ሕግን በመናቅ መከልከላቸው ታውቋል።
የቀድሞው የአባያ እርሻ ልማት ይዞታ 1,262 ሄክታር ሲሆን ከዚህ ውስጥ 500 ሄክታር ይዞታን በአንድ ሄክታር 500 ብር ብቻ በሊዝ ውል የተረከቡት አቶ ዳኜ (ዎልማ ለመንግሥት በሄክታር 1,000 ብር እየከፈለ 500 ብር ከስሮ ያከራያቸው መሆኑ ይታወቃል)፤ ውል ይኑራቸው እንጂ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ የሌላቸው በመሆኑና ወሰኑ ባለመታወቁ ጎርፍ ያልገባበትንና ከሲዳማ ያልሆነውን የዎላይታ ለም መሬት በሙሉ እያማረጡ ሲያርሱ ቆይተዋል። በተጨማሪም በሕግ ከተሰጣቸው 1,060 ሄክታር በላይ በጅምላ ሰፊ መሬት መውረራቸው ተገልጿል።
ይበልጥ አሳሳቢው ጉዳይ አቶ ዳኜ ዳባ በአባያ ብላቴ ከሚያለማው 500 ሄክታር ውስጥ 200 ሄክታሩ በምስጢር የተያዘው በሲዳማ ክልል ከፍተኛ አመራር በአቶ አብርሃም ማርሻሎ እና በቤተሰቦቻቸው መሆኑ ነው። በዚህም ምክንያት በአባያ ብላቴ ላይ የተፈጸመው የመሬት ወረራ ከዚሁ የጥቅም ትስስር ጋር የተያያዘ መሆኑ ተረጋግጧል።
ታዋቂው ባለሀብት አቶ በላይነህ ክንዴ በአበላ አባያ ወረዳ ብላቴ ቀበሌ የሚገኘውን ቢሊዮን የሙዝ ዘለላ ለዘመናት የሚያሳፍሰውን 550 ሔክታር ለም የእርሻ ኢንቨስትመንት ይዞታ ለ45 ዓመታት ለማልማት የሚያስችል የካርታ እና የሊዝ ውል ሰነድ ከዎላይታ ዞን የወሰደ ቢሆንም ላለፉት ሦስት ዓመታት ዓመታዊ የመሬት መጠቀሚያ ኪራይ እና የገቢ ግብር ለዎላይታ ሳይሆን ለሲዳማ ክልል ሎክ አባያ ወረዳ ተደራቢ ውል በመውሰድ እየከፈለ እንደሚገኝ ተጋልጧል።
ይህም ቦታው ከሲዳማ ጋር ያልተቋጨ የወሰን ውዝግብ ያለበት መሆኑን ተገን በማድረግ የተፈጸመ የታክስ ክህደት ነው።
ይባስ ብሎ በአካባቢው ግጭት በተከሰተበት ወቅት የአይን እማኞች ለ WT Media እንዳረጋገጡት ”ጥቃቱ በተፈፀመበት ቀን ጥቃት አድራሽ ወታደሮች በበላይነህ ክንዴ እርሻ ውስጥ ባለው ማዕድ ቤት ምግብ ተመግበው የእርሱ መኪኖችን ለዘመቻ ተጠቅመዋል።
የአቶ አብርሃም ማርሻሎ ወንድም ሳይቀር በዚሁ መኪና ውስጥ ሆኖ ኦፕሬሽኑን ሲመራ ነበር” ሲሉ የአይን እማኞች ሁኔታውን በምሬት ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ መሬቱ የሚገኘው በዎላይታ ዞን ውስጥ መሆኑን የሚቃረኑ ተደጋጋሚ ዘገባዎች በተለያዩ ሚዲያዎች ቢወጡም የሚመለከተው የዞን አመራር ማብራሪያ እንዲሰጥበት በተደጋጋሚ ቢጠየቅም እስካሁን ዝምታን መርጧል።
በመድረኩ ላይ የቀረበው ይፋዊ ሪፖርት እንደሚያሳየው እስከ ግንቦት 30 ቀን ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ የዎላይታ ሶዶ ከተማን ሳይጨምር 5.5 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 5.3 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ተችሏል።
የዞኑ የጤናና ትምህርት ቤቶች ውስጥ ገቢን ጨምሮ የተለጠጠው (ትክክለኛው) የገቢ አቅም ግን 7.2 ቢሊዮን ብር እንደነበር ተመላክቷል። በሌላ በኩል የዎላይታ ሶዶ ከተማ የዘንድሮ ዕቅድ 3.8 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ የእስካሁን አፈጻጸሙ ከ2.85 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑ ተገልጿል።
ይህ ማለት የዎላይታ ሶዶ ከተማ አፈጻጸምን ጨምሮ በአጠቃላይ በዞኑ የተሰበሰበው የገቢ መጠን ከ8.15 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑን ያሳያል። ይህም ዎላይታ ዞን በክልሉ ውስጥ ከየትኛውም ዞን በላቀ ደረጃ ከፍተኛ ግብር የሚገብርና ለክልሉ ምጣኔ-ሀብት ዋነኛ የገቢ ምንጭ መሆኑን በግልጽ ያረጋግጣል።
ይሁን እንጂ ዞኑ ይህንን ያህል ግዙፍ ገቢ ወደ መካከለኛው ካዝና የሚያስገባ ቢሆንም በተቃራኒው በአካባቢው የተጀመሩ መሠረታዊ የልማት ፕሮጀክቶች ሳይጠናቀቁ ለዓመታት ተንጓትተው መቅረታቸውና በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ተስፋ-ቆራጭ ሥራ አጥ ወጣቶች እስካሁን ድረስ አንዳችም ተጨባጭ የሥራ ዕድል ፈጠራና መፍትሔ አለመገኘቱ የሪፖርቱን መራራ እውነታና ከፍተኛ ተቃርኖ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ሆኗል።
ይህ ዘገባ እስከተጠናቀቀበት ጊዜ ድረስ በስም የተጠቀሱት ባለሀብቶችም ሆኑ የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች በዝምታቸው የቀጠሉ ሲሆን የዜና ክፍላችን ጉዳዩን በጥብቅ በመከታተል ተከታታይ የምርመራ ክፍሎችን ለሕዝብ ይፋ ማድረጉን ይቀጥላል።