GridArt_20260714_145033536

ሠራተኛው ደመወዝ አጥቶ ወደ ጎዳና በሚወጣበት ዎላይታ ዞን ለአመራርና ነዳጅ 4.3 ሚሊዮን ብር በዛሬው ዕለት በባንክ የተቀነሰ ሲሆን የ159 ሚሊዮን ብር የቅንጦት መኪናዎች ግዢ በአከባቢው ውጥረት ፈጠረ

​የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ተከልክለው በቤት ኪራይ ዕዳ ምክንያት ወደ ጎዳና እየተባረሩ ባሉበት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዎላይታ ዞን የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች በዛሬው ዕለት ሐምሌ 07 ቀን 2018 ዓ.ም. ጭምር የፈጸሙት አዲስና አስደንጋጭ የገንዘብ ምዝበራ እና የቅንጦት ዝግጅት ሚስጥር ይፋ ሆኗል።

​WT Media ከዞኑ ከፍተኛ ባለሙያዎች እና ከውስጥ ምንጮች ያገኘው አዲስ መረጃ እንደሚያሳየው፤ የዞኑ አመራሮች የሠራተኛውን ደመወዝ አግደው የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበርና የሕዝብን ሀብት ለመቀራመት የሄዱበት ርቀት ተቋማዊ ብስባሹ ምን ያህል አደገኛ ደረጃ ላይ መድረሱን ያረጋግጣል።
​
​የዞኑ አመራሮች ለሠራተኞች ደመወዝ የሚሆን ገንዘብ የለም በሚሉበት በዚህ አስከፊ ወቅት ለራሳቸው የቅንጦት ሕይወት እያንዳንዳቸው 53 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ሦስት (3) ዘመናዊ የ“ገመችሳ” መኪናዎችን በአጠቃላይ በ159 ሚሊዮን ብር ለመግዛት ሰፊ ዝግጅት አድርገው ነበር።

እነዚህ መኪናዎች ሊገዙ የታሰቡት፦ ​ለዞኑ ፋይናንስ መመሪያ (1)፣ ​ለዞኑ አስተዳደር (1) እንዲሁም ​ለዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት (1) ነበሩ።

​ይሁን እንጂ WT Media እና አንዳንድ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ የሕዝብ ደጋፊዎችና ተቆርቋሪ የመንግሥት ተቋማት ይህንን የቅንጦት ግዢ በጽኑ በመቃወማቸው ምክንያት ግዢው እንዲሰናከል ተደርጓል። ነገር ግን አመራሮቹ ይህንን የተቃወሙበትን 159 ሚሊዮን ብር ለሠራተኛው ደመወዝ ከመክፈል ይልቅ ገንዘቡን በአየር ላይ አዘግይተው ለራሳቸው የውሎ አበልና ጥቅማጥቅም ማመቻቻ እያደረጉት መሆኑን የውስጥ ምንጮች አጋልጠዋል።

​ቀደም ሲል ለዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ሕንፃ ጥገና እና ቀለም ቅብ ተብሎ የተመደበው በጀት 148 ሚሊዮን ብር የነበረ ቢሆንም፣ አመራሮቹ ምንም ዓይነት መዋቅራዊና የሕግ አሠራር ሳይከተሉ ተጨማሪ አንድ መቶ ሚሊዮን (100,000,000) ብር በመጨመር አጠቃላይ ወጪውን 253 ሚሊዮን ብር አድርገውታል።

ይህንን እጅግ ግዙፍ የሕዝብ ሀብት ለህንጻው ጌጣጌጥና ለቀለም ቅብ ካፈሰሱ በኋላ አሁን ላይ “ደመወዝ ለመክፈል የጥሬ ገንዘብ አቅም አጣን” በሚል ሰበብ የሠራተኛውን ጉሮሮ ዘግተዋል።

​ሠራተኛው በረሃብ እየተቆላ ባለበት በዛሬው ዕለት (ሐምሌ 7 ቀን 2018 ዓ.ም.) ሌላ አስደንጋጭ ድርጊት ተፈጽሟል። የዞኑ ምክትል ኃላፊ አቶ ማቴዎስ ማሞ በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሶዶ ቅርንጫፍ በአካል በመገኘት ለዞኑ አመራሮች የውሎ አበልና ለነዳጅ ክፍያ የሚሆን 4.3 ሚሊዮን ብር ከዞኑ የሂሳብ መዝገብ (ሌጀር) ላይ ተቀንሶ እንዲገባ ለማድረግ ከፍተኛ ግፊት ሲያደርጉ ውለዋል።

​ይህ ህገወጥ ዝውውር ያለምንም መደበኛ አሠራር እንዲፈጸም ለማድረግ በንግድ ባንክ ቅርንጫፉ ላሉ ሥራ አስኪያጆች (ማናጀሮች) እና ኦዲተሮች ከፍተኛ የውሎ አበልና ጉቦ በመክፈል የባንኩን የውስጥ አሠራር ለመጠምዘዝ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የምርመራ ቡድናችን አረጋግጧል።
​
​ሁኔታው እጅግ የከፋ ማኅበራዊ ቀውስ እያስከተለ መሆኑን ሁለት የዎላይታ ዞን ከፍተኛ ባለሙያዎች ለWT Media በሰጡት ምስክርነት አረጋግጠዋል።

እነዚህ ባለሙያዎች በከፍተኛ እምባና ሐዘን ውስጥ ሆነው የሚከተለውን ብለዋል፦ “የመንግሥት ሥራ እየሠራን ላለፉት ወራት ደመወዝ ባለማግኘታችን ምክንያት የቤት ኪራይ መክፈል አቅቶናል። ተከራይተንባቸው የነበሩት አባወራዎች ከቤት አስወጥተውናል። አሁን ላይ እቃዎቻችንን ይዘን ወደ ጎዳና ወጥተናል። ድምፃችንን የሚሰማ፣ የደሃ እምባ የሚታየው ካለ ፈጣሪ ይስማን! እኛስ ለፈጣሪ ሰጥተናል!!”

​ይህ ምስክርነት በዞኑ ውስጥ ከ200 ሺህ በላይ የተማሩ ወጣቶች ሥራ አጥ በሆኑበት እና የመንግሥት ሠራተኛውም ያለበትን ዝቅተኛ ደመወዝ ተከልክሎ ለከፋ ማኅበራዊ ውድመት መዳረጉን የሚያሳይ ጥቁር ጠባሳ ነው።

​ከቀናት በፊት ያጋለጥናቸው ትይዩ የባንክ አካውንቶች መከፈት በፎርጅድ ደረሰኞች ገቢን መመዝበር፣ የአርሶ አደሩን የአፈር ማዳበሪያ ገንዘብ ለግል ጥቅም ማዋል እና ከ3.4 ቢሊዮን ብር በላይ በነዳጅና መስተንግዶ ማባከን ሳያንስ፤ ዛሬ ደግሞ በምክትል ኃላፊው በአቶ ማቴዎስ ማሞ አማካይነት በባንክ የተፈጸመው የ4.3 ሚሊዮን ብር ህገወጥ ዝውውር የዞኑ አስተዳደር ምን ያህል ከሕግ በላይ መሆኑን ያሳያል።

​WT Media በሙያዊ ስነ-ምግባር መሠረት ለዞኑ አመራሮች በተደጋጋሚ የስልክ ጥሪና መልዕክት በማስተላለፍ ማብራሪያ ለመጠየቅ ቢሞክርም፣ አመራሮቹ አሁንም በዝምታ መሸሸግን መርጠዋል።

​ይህ በደሃው የመንግሥት ሠራተኛ እና በአካባቢው ማኅበረሰብ ላይ እየተፈጸመ ያለው የጭካኔና የዝርፊያ ጥግ በአስቸኳይ በክልሉ እና በፌደራል የፍትሕ አካላት እንዲሁም በፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጥብቅ ምርመራ ተደርጎበት፣ በዛሬው ዕለት ጭምር በባንክ የተንቀሳቀሱት አመራሮች በአስቸኳይ ለሕግ እንዲቀርቡ በጥብቅ የአከባቢው ነዋሪዎች በመግለፅ ላይ ይገኛሉ።