1000126545

በደቡብ ኢትዮጵያ በቁጫ እና በዘይሴ ብሔረሰቦች ላይ በምርጫ ምክንያት የተቀናጀ የኃይል ጥቃት፣ የጅምላ እስራት፣ ግድያ እና መጠነ-ሰፊ መፈናቀል እየተፈጸመ መሆኑ ተገልጿል።

​በክልሉ በጋሞ ዞን ስር በሚገኙ የቁጫ እና የዘይሴ ብሔረሰቦች ላይ በመንግሥት የፀጥታ መዋቅር እና በታጣቂዎች አማካኝነት ስልታዊ ጥቃት፣ እስራት፣ ግድያ እና መፈናቀል እየተፈጸመ መሆኑ ታውቋል።

ትናንት ምሽት የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁሕዴፓ) ለWT Media በላከው አስቸኳይ መግለጫ በአባላቱ እና በደጋፊዎቹ ላይ እየደረሰ ያለውን ሰቅጣጭ ድብደባ ያወገዘ ሲሆን፤ በተመሳሳይ በዘይሴ ወረዳዎች ትናንት እና ዛሬ በመንግሥት ታጣቂዎች በተፈጸመ ቃጠሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች መፈናቀላቸው ተረጋግጧል።

​የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁሕዴፓ) በቁጫ ምርጫ ክልል በፓርቲው አባላት፣ ደጋፊዎች እና በንጹኃን ዜጎች ላይ በመንግሥት አመራሮችና በፀጥታ አካላት እየተፈጸመ ያለውን ሕገ-ወጥ እስር፣ የአካል ድብደባ፣ የማሰቃየት (ቶርቸር) ድርጊት፣ የሕክምና አገልግሎት መከልከል እና ማስፈራራት በጽኑ አውግዟል።

​በቁጫ ወረዳ ሲቆሌ ቀበሌ እና በአካባቢው በርካታ የፓርቲው አባላት እና ደጋፊዎች ላይ የመንግሥት አመራሮች እና የፀጥታ አካላት እጅግ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ጥቃት እየፈጸሙ ይገኛሉ።

የጥቃቱ ሰለባ የሆኑት ዜጎች በጥያቄነት የቀረበባቸው፦ ​”በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ለምን ለቁሕዴፓ ድምፅ ሰጣችሁ?” ​”በምርጫው ማጭበርበር ጉዳይ ለአጣሪ ቡድኑ ለምን መሰከራችሁ?” ​”በሀገራዊ ምክክር የቁሕዴፓ ተሳትፎ ለቁጫ ሕዝብ ድል ያመጣል ብላችሁ ለምን ደስታ ገለጻችሁ?” የሚሉ መሆናቸውን ፓርቲው ገልጿል።

​ዜጎች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለብዙ ቀናት ታስረው ይገኛሉ። በየሌሊቱም ከቁጫ ወረዳ እና ከጋሞ ዞን በተመደቡ መደበኛ ፖሊሶች የከፋ የአካል ድብደባ፣ የገንዘብ ቅጣት እና የማሰቃየት ድርጊት እየፈፀሙባቸው ይገኛል።

​ፓርቲው አክሎ እንዳሳሰበው ይህ ድርጊት የሀገራዊ ምክክሩ ሊቆምባቸው ከሚገቡት የሰብዓዊ ክብር እና የሕግ የበላይነት መሠረቶች ጋር በቀጥታ ይጋጫል። ይህ ጥቃት በአስቸኳይ የማይቆም ከሆነ ቁሕዴፓ በሀገራዊ ምክክሩ ላይ ያለውን ተሳትፎ ጨምሮ ተገቢ የፖለቲካ ውሳኔዎችን ለመውሰድ እንደሚገደድ በጥብቅ አስታውቋል።

​በዚሁ በጋሞ ዞን መዋቅር አመራሮች እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በአቶ ጥላሁን ከበደ በሚመራው የፀጥታ መዋቅር ስም የተደራጁ ክልሉ የማያውቀው ኢ-መደበኛ የታጠቁ ኃይሎች በዘይሴ ሕዝብ ላይ ያነጣጠረ መጠነ-ሰፊ ጥቃት እያደረሱ መሆኑን ከሥፍራው የደረሱን ታማኝ መረጃዎች አመላክተዋል።

​ጥቃቱ የተሰነዘረው የዘይሴ ሕዝብ በ7ኛው ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ገዢውን ብልጽግና ፓርቲ ለሁለተኛ ጊዜ አልመረጠም በሚል ጭፍን ጥላቻ መሆኑ ተገልጿል። ከምርጫው ማግስት ጀምሮ በንጹኃን የዘይሴ ብሔር ተወላጆች ላይ እየተፈጸመ ባለው ብሔር ተኮር ጥቃት ሳቢያ እስካሁን ድረስ ከ30 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ለ WT Media ታማኝ ምንጮች ያቀረቡት ሪፖርት ያመለክታል።

​በተጨማሪም በኢ-መደበኛ የታጠቁ ኃይሎች በተፈጸመ የቤትና ንብረት ማውደም ተግባር በ100 ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች መኖሪያ ቤቶች ሙሉ በሙሉ በእሳት ወደ አመድነት ተቀይረዋል። በዚህም ምክንያት በርካታ የአካባቢው ተወላጆች ለከፍተኛ መፈናቀል ተዳርገው በጫካዎች፣ በገደላገደሎችና በአጎራባች አካባቢዎች ተሰደው በከፋ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ።

​ይህ በእንዲህ እያለ በትናንትናው ዕለት (ሐምሌ 6 ቀን 2018 ዓ.ም.) እና በዛሬው ዕለትም በዘይሴ ወዘቃ ቀበሌ ልዩ ስሙ ሐውሻ (በዘይሴ እና በዱራ ቀጠናዎችና ንዑስ ቀበሌዎች) በክልሉ የፀጥታ ኃይሎች በርካታ የነዋሪዎች ቤቶች በእሳት እንዲወድሙ ተደርጓል።

ይህንን ተከትሎም በትናንትናው እና በዛሬው ዕለት ብቻ በሺዎች የሚቆጠሩ የዘይሴ ነዋሪዎች ከቀያቸው ተፈናቅለው ለአዲስ ስደት ተዳርገዋል።

​ነዋሪዎች እንደገለጹት፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ “ክልላችን የሰላም ተምሳሌት ነው” በማለት እውነታውን በመደበቅ ለሕገ-ወጥ ታጣቂዎቹ ቀጥተኛ ሽፋን እየሰጡ ይገኛል። ጥቃቱ የረጅም ጊዜ ስትራቴጂ ተነድፎበት በዘይሴ ማህበረሰብ ላይ እየተፈጸመ ያለ ቀጥተኛ ብሔር ተኮር ጥቃት (Genocide) ነው ሲሉ ነዋሪዎቹ በምሬት ይናገራሉ።

​WT Media ከዚህ ቀደም ባደረጋቸው ተከታታይ የምርመራ ዘገባዎች እንደገለጸው፣ በጋሞ ዞን ውስጥ በሚገኙ አነስተኛ ብሔረሰቦች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ታሪካዊ መሠረት አለው።

​ሰሞኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ባወጣው አስቸኳይ መግለጫ የመንግሥት ታጣቂዎች በዘይሴ ቀበሌዎች ባደረሱት ጥቃት የ10 ሰዎች ሕይወት ማለፉን፣ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን እና የጅምላ እስር መፈጸሙን አረጋግጦ ነበር።

​በ6ኛው እና በ7ኛውም አገራዊ ምርጫ የዘይሴን ሕዝብ ወክለው በኢዜማ ፓርቲ የተመረጡት የፓርላማ አባል አቶ አብርሃም አሞሼ የሕዝባቸውን የደኅንነት እና የማንነት ጥያቄ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፊት በፓርላማ እንዳያቀርቡ በአፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ (የጋሞ ተወላጅ) ትዕዛዝ በበር ላይ መከልከላቸው ይታወሳል።

​WT Media ከዚህ ቀደም በዘይሴ ደምበሌ፣ በኦጎሌ እና በጋርዘታ አካባቢዎች ላይ የተካሄደውን የቤት እንስሳት ዘረፋ እና የሲቪሎች ግድያ በስፋት መዘገቡ ይታወሳል።

ይህ ጥቃት አሁን ላለው መጠነ-ሰፊ መፈናቀል መነሻ መንገድ የጠረገ ነበር። ​የዘይሴ ብሄረሰብ እንደ ጎረቤት ብሔረሰቦች ሁሉ ራሱን የቻለ «ልዩ ወረዳ» ተዋቅሮለት በራሱ በጀት እንዲተዳደር የሚፈልግ ቢሆንም የጋሞ ዞን ባለሥልጣናት ግን ግዛታዊ የበላይነታቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ ይህንን ሕገ-መንግሥታዊ ጥያቄ በኃይል እያፈኑት ይገኛሉ።

​በጋሞ ዞን ውስጥ በቁጫ እና በዘይሴ ብሔረሰቦች ላይ የተከፈተው ይህ ጥቃት በምርጫ ወቅት ካሳዩት የፖለቲካ አቋም እና ካነሱት የማንነት ጥያቄ ጋር በቀጥታ የተያያዘ መሆኑን ሁለቱም ወገኖች ያረጋግጣሉ።

የቁሕዴፓ አመራሮች፣ የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች እና ተቆርቋሪ ወገኖች የፌዴራል መንግሥት፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በጉዳዩ ላይ አስቸኳይ እና ገለልተኛ ምርመራ እንዲያካሂዱ በጽኑ እየጠየቁ ይገኛሉ።

​ይህ ሰፊ እና ዝርዝር ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ፣ በቀጥታ ስማቸው ከተነሳው ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ጽሕፈት ቤትም ሆነ ከጋሞ ዞን ከፍተኛ አስተዳደር በኩል የተሰጠ ይፋዊ ምላሽ የለም።

​🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏

Voice of Marginalized Community – WT Media