በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በዎላይታ ሶዶ ከተማ በአንድ የግል ባለሀብት ይዞታ ምክንያት ተዘግቶ የቆየውን የህዝብ መተላለፊያ መንገድ በተመለከተ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የመጨረሻ ውሳኔ የሰጠ ቢሆንም ውሳኔውን በመጣስ በቦታው ላይ አዲስ ግንባታ እየተካሄደ መሆኑ የአካባቢውን ነዋሪዎች እያማረረ እንደሚገኝ WT Media ዘገባ አረጋግጧል።
የከተማው ማዘጋጃ ቤት አመራሮች ጉዳዩን እያወቁ ዝምታን መምረጣቸው ደግሞ በነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ጥርጣሬና ቅሬታን ፈጥሯል።
ጉዳዩ በዎላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር መርካቶ ክፍለከተማ ፋና ቀበሌ ውስጥ በዎላይታ ሶዶ ዩንቨርስቲ ዋናው መግቢያ ፍትለፍት ላይ በሚገኘው በአቶ ማርቆስ ጣሰው በተባሉ ግለሰብ እና በአካባቢው ማህበረሰብ መካከል የተፈጠረውን የይዞታ ውዝግብ የተመለከተ ነው።



ግለሰቡ በቦታው ላይ የ G+3 ህንጻ የገነቡ ሲሆን ከህንጻው ጎን በደቡብ በኩል ቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን ምዕመናንን፣ ከ2,000 በላይ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን እና የአካባቢውን ነዋሪዎች የሚያገለግለውን የህዝብ መተላለፊያ መንገድ ዘግተውት ቆይተዋል።
የዎላይታ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀደም ሲል ለግለሰቡ የሚደግፍ ውሳኔ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም የአካባቢው ነዋሪዎች ጉዳዩን ወደ ላይኛው የፍትህ አካል በመውሰድ ይግባኝ ጠይቀው ነበር።
በዚህም መሠረት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 68670 በዕለት 27/07/2016 ዓ.ም በሰጠው የመጨረሻ ውሳኔ የዎላይታ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ሽሮታል።
የተዘጋው ቦታ በከተማው ማስተር ፕላን መሠረት የህዝብ መተላለፊያ መንገድ መሆኑን አረጋግጧል።
ማዘጋጃ ቤቱ ለግለሰቡ የሰጠው የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እና የህንጻ መሥሪያ ፈቃድ የከተማውን ፕላን የሚጥስ በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲሰረዝ ወስኗል።

ይህ የመጨረሻው የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ ተላልፎ እያለ መሬት ላይ ያለው እውነታ ግን ፍጹም ተቃራኒ ሆኗል። WT Media ከአካባቢው ነዋሪዎች በደረሱት ማስረጃ እና መረጃዎች መሠረት በቦታው ላይ አሁንም በርካታ የቀን ሠራተኞች ተቀጥረው አዲስ የድንጋይ መሠረት ግንባታ በይፋ እያከናወኑ ይገኛሉ።
በዚህ ሁኔታ የተማረሩት የአከባቢው ነዋሪዎች፦ ”ይህ የፍርድ ቤት ውሳኔ በግልጽ እያለ ግንባታው እንዲካሄድ መደረጉ እጅግ ያሳዝናል። የማዘጋጃ ቤት አመራሮች ከግለሰቡ ጥቅማጥቅም (ገንዘብ) በመቀበል ግንባታው እንዲቀጥልና መንገዱ እንደተዘጋ እንዲቆይ እያደረጉ ነው” ሲሉ ቅሬታቸውን ለ WT Media ገልጸዋል።


WT Media የአካባቢውን ነዋሪዎች ቅሬታ መነሻ በማድረግ እና የተገኙትን የፍርድ ቤት የውሳኔ ሰነዶች በመያዝ በጉዳዩ ዙሪያ የሚመለከታቸው የዎላይታ ሶዶ ከተማ ማዘጋጃ ቤት አመራሮችን እና የአስተዳደር አካላትን ሰፊ ማብራሪያና አስተያየት እንዲሰጡ በተደጋጋሚ የጠየቀ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
የፍርድ ቤትን የበላይነት የሚጥሰውና የአካባቢውን ማህበረሰብ መብት የሚጋፋው ይህ ህገ-ወጥ ግንባታ እንዴት ሊቀጥል እንደቻለ እና የሚመለከታቸው አካላት ውሳኔውን ለማስፈጸም ምን እያደረጉ እንደሆነ WT Media ጉዳዩን በቅርበት መከታተሉን ይቀጥላል።