የዘይሴ በደል እና የትንቢት መጋረጃ፡“ነቢይ” ኤልሳዕ ቱራ በአርባ ምንጭ ምን አሰቡ? ትንቢት ወይስ የፖለቲካ አጀንዳ ?
በተለያዩ ጊዜያት በሚሰጡት “ትንቢቶች” የሚታወቁት ኤልሳዕ ቱራ፣ በዎላይታ የፖለቲካ መዋቅር ውስጥ ተከታታይ እና ተቃራኒ ትንቢቶችን በመናገር ይታወሳሉ። አሁን ደግሞ የትንቢት ጉዞአቸውን ወደ ጋሞ ዞን በማዞር፣ በዘይሴ ብሔረሰብ ላይ እየደረሰ ነው በተባለው በደል ዙሪያ በአደባባይ ጸሎት ማድረጋቸው አዲስ ውይይት ፈጥሯል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የዎላይታ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ዳጋቶ ኩምቤ በነበሩበት ወቅት ኤልሳዕ ቱራ ለአስተባባሪዎቹ “ጌታ ዎላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሲመሰረት አሳይቶኛል” በማለት ትንቢት ተናግረው ነበር።
ሆኖም አዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምስረታ ሲቃረብ፣ በተለያዩ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት የጉተራ አዳራሽ፣ ከቀደመው ትንቢታቸው በተቃራኒ “ዎላይታ በአዲሱ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሲደራጅ አይቸዋለሁ” በማለት ተደምጠዋል። ይህ አቋማቸው በወቅቱ ብዙዎችን ግራ ያጋባ እና የፖለቲካ ድጋፍ መለዋወጥን የሚያሳይ ነው የሚል ትችት ሲቀርብበት ቆይቷል።

አሁን ደግሞ ኤልሳዕ ቱራ ወደ ጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ከተማ በማቅናት፣ በዞኑ መዋቅር ውስጥ በሚገኘው የዘይሴ ብሔረሰብ ላይ እየደረሰ ያለውን በደል እና መፈናቀል መነሻ በማድረግ በአደባባይ ጸሎት አድርገዋል። በዘይሴ ብሔረሰብ ላይ እየደረሰ ያለው ግድያ፣ ንብረት ውድመት እና መጠነ-ሰፊ መፈናቀል የክልሉን ፖለቲካ በከፍተኛ ሁኔታ በውጥረት ውስጥ በከተተበት ወቅት፣ የኤልሳዕ ቱራ የጸሎት መርሃ-ግብር የብዙዎችን ቀልብ ስቧል።
ጉዳዩን በተመለከተ የሚነሱ ዋና ዋና ጥያቄዎች፦ ቀደም ሲል ለዎላይታ የራስ ገዝ አስተዳደር ትንቢት ተናግረው፣ በኋላ ወደ ክልልነት መቀየራቸው የፖለቲካ ፍላጎት አለው ወይስ የትንቢት መለዋወጥ? በዘይሴ ማኅበረሰብ ላይ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰትና መፈናቀል እየተፈጸመ ባለበት ወቅት የኤልሳዕ ቱራ የአደባባይ ጸሎት የሕዝቡን ስሜት ለመጋራት ነው ወይስ በዞኑ አመራሮች ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት?
ይህ የኤልሳዕ ቱራ እንቅስቃሴ፣ ትንቢት በፖለቲካ መድረክ ላይ እንዴት እንደሚንጸባረቅ እና የሃይማኖት አባቶች በወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ያላቸው ሚና ምን መሆን እንዳለበት እንደገና እንድንጠይቅ እያደረገ ይገኛል።
ማስታወሻ፦ ይህ ዘገባ የተዘጋጀው ኤልሳዕ ቱራ ከተናገሯቸው ተቃራኒ ትንቢቶች እና ከአሁኑ የአርባ ምንጭ ጸሎት መርሃ-ግብር ጋር በማያያዝ ተመልካቾቻችን ሁኔታውን እንዲገመግሙ ታሳቢ በማድረግ ነው። WT Media እንደ መገናኛ ብዙኃን፣ በጉዳዩ ዙሪያ ያላቸውን አመለካከት በገለልተኛነት ለሕዝብ ይተውላችኋል።