የዎላይታ ዞን ንግድ ማህበረሰብ በከፍተኛ የግብር ጫና ውስጥ መውደቁንና የአመራሩ የፋይናንስ ብልሽት ተጋለጠ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዎላይታ ዞን ከዞን እስከ ቀበሌ ባለው መዋቅር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎች በዞኑ አስተዳደር እየተፈጸመ ባለው ኢ-ፍትሃዊ የግብር አሰባሰብ እና የመንግሥት በጀት አያያዝ ችግር ምክንያት ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ መዳረጋቸውን ለ WT Media ተናግረዋል።
የንግድ ማህበረሰቡ እንደገለጸው፣ መንግሥት ለሕዝብ አገልግሎት እንዲውሉ ያሰፈራቸው አመራሮች የመንግሥትን አሠራር በመጣስ በዘር ሐረግና በዝምድና በተመሠረተ የጥቅም መረብ የሕዝብ ሀብትን እያባከኑ ይገኛሉ።
ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት የዞኑ አመራሮች ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ ከአርሶ አደሩ በእጅ የተሰበሰበውን የአፈር ማዳበሪያ ገንዘብ ለፌደራል መንግሥት ከማስገባት ይልቅ ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸው የችግሩ መነሻ ሆኗል።
የዞኑ አመራሮች የ2018 ዓ.ም. በጀትን በግል ጥቅም አውለው በመጨረሳቸው የበሉትን ገንዘብ ለመሸፈን ሲባል አሁን ላይ በንግድ ማህበረሰቡ ላይ ከፍተኛ የግብር ጫና እየተጫነባቸው መሆኑ ተነግሯል።
ከዚህም በተጨማሪ አመራሮቹ የ2018 ዓ.ም በጀትን በመጨረሳቸው የ2019 ዓ.ም በጀትን ለመበደር ያደረጉት ሙከራ በመንግሥት ዘንድ ውድቅ በመደረጉ የደረሰውን የገንዘብ ጉድለት በንግድ ማህበረሰቡ ላይ አዲስና ያልተገባ የግብር ተመን በመጣል ለመሸፈን እየሞከሩ መሆኑን የንግዱ ማህበረሰብ ክፍሎች አረጋግጠዋል።
የንግድ ማህበረሰቡ አባላት በበኩላቸው “ለሕዝብ ይሰራሉ ብለን የመረጥናቸው አመራሮች በሙስናቸው ምክንያት የደረሰብንን የገንዘብ እጥረት በግድ እንድንሸፍን እየተገደድን ነው፤ የደረሰብንን ግፍ የሚሰማን በማጣታችን ለፈጣሪ ሰጥተናል” በማለት ስሜታቸውን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ከዞን እስከ ቀበሌ ባለው መዋቅር ውስጥ የሚታየው “ማን አለብኝነት” እና የመንግሥት የገቢ አሰባሰብ መመሪያን የተከተለ ያልሆነው የግብር አወጣጥ፣ በክልሉ ያለውን የንግድ እንቅስቃሴ አደጋ ውስጥ ጥሎታል” በሚል ንግድ ማህበረሰቡ ቅሬታ አሰምተዋል።
የWT Media የምርመራ ቡድን ያገኘው መረጃ እንደሚያሳየው አመራሮቹ በፎርጅድ ሰነዶች እና በሕገ-ወጥ የሂሳብ አያያዝ የመንግሥትን ገቢ ወደ ግል ጥቅም እየቀየሩ ይገኛሉ።
የንግድ ማህበረሰቡ ይህንን ኢ-ፍትሃዊ የግብር ጫና አጥብቆ የሚቃወም ሲሆን የሚመለከታቸው የክልልና የፌደራል የፍትሕ አካላት በአስቸኳይ ጣልቃ ገብተው ችግሩን እንዲያጣሩ ጥሪ እያቀረቡ ይገኛሉ።
WT Media በቀጣይ ቀናት በዞኑ ስላለው የፋይናንስ አያያዝ እና ስለ ግብር አሰባሰቡ አሠራር ዝርዝር የምርመራ ዘገባዎችን ይዞ የሚቀርብ ይሆናል።
🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏
Voice of Marginalized Community – WT Media