1000129048

ከደቡብ ኢትዮጵያ እስከ ዱባይና ሩዋንዳ የተዘረጋው የሌብነት ሰንሰለት፡ የአቶ ጥላሁን ከበደና የግርጌ ተላላፊዎቻቸው የተጋለጠው ግዙፍ የሙስና መረብ – የ WT Media ልዩ የምርመራ ዘገባ

​በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአብዛኞቹ ሕዝብ ዘንድ በአስመስሎ አዋቂነታቸውና ኢፍትሐዊነት በሚታወቁት የክልሉ ከፍተኛ አመራር በአቶ ጥላሁን ከበደ የተመራው እና እስከ ውጭ አገር የዘለቀው የግዙፍ ሌብነትና የሀብት ማሸሽ መረብ በሰነድና በመረጃ ተጋልጧል።

​የWT Media ታማኝ የመረጃ ምንጮች ከስፍራው እንደደረሱት የክልሉ አመራሮች በድብቅና ከሕዝብ ዓይን ጀርባ የሚፈጽሟቸው ሕገ-ወጥ ድርጊቶች እና የድንበር ተሸጋሪ የገንዘብ ዝውውሮች አሁን ላይ ይፋ መውጣታቸውን አመላክተዋል።

​ከዛሬ ሁለት ወር ገደማ አካባቢ ጀምሮ አቶ ጥላሁን ከበደ የክልሉ ሥራ አስፈጻሚዎችም ሆነ የክልሉ ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ፍጹም ሳያውቁ፣ ዎላይታን ወክለው ወደ ፊት እንዲመጡ በሚል የራሳቸውን የጥቅም ስኳድ አባላት ስም ዝርዝር በድብቅ ወደ ፓርቲ ማዕከል (አዲስ አበባ) ልከው ነበር።

​ይሁን እንጂ የፓርቲው ማዕከል የተላኩትን ግለ-ማህደሮች መርምሮና አስበርብሮ “ጠብ የሚል ነገር” (ምንም ዓይነት የሚመጥን ብቃትና ታሪክ) ሲያጣ ጉዳዩን አጣርቶ ለክልሉ ብልጽግና ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በመመለስ ከእንደገና እንዲፈተሽና ማስተካከያ እንዲደረግ አዘዟል።

​በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ የውስጥ ምንጮች፦ “መሠረታዊው ጥያቄ ጥላሁን ለምን እንዲህ አደረገ? ዎላይታን በዚህ ልክ ለምን ናቀ? ማነው በዚህ ልክ ያስናቀንና ያስደፈረን? የኛ ሰዎችስ ለምን በዚህ ልክ ተላላኪ ሆኑ? ሆዳቸውና ክብራቸው ከዎላይታ ማንነታቸው እንዴት ገዘፈባቸው?” በማለት አበክረው ጠይቀዋል።

​እንደዚሁም ሁሉ አቶ ጥላሁን ከበደ የዎላይታን እጩዎች ከሥልጣናቸው ወሰን ውጪ አድርገው እንዳበላሹት ሁሉ የጋሞ ዞንንም እጩዎች በድብቅ ራሳቸው በመልመል ለፓርቲ ማዕከል ልከው ነበር።

​ከነዚህ የጥላሁን የሌብነትና የጥቅም አጋሮች መካከል የክልሉ የከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ የሆነው አቶ ብርሃኑ ዘውዴ ይገኝበታል። ይሁን እንጂ የዚህን ግለሰብ ስም ያዩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) “ይሄን አስወጡት፤ ሌባ ነው፣ የጊዜ ጉዳይ እንጂ” በማሉበት ግልጽ አቋም ምክንያት ጉዳዩ በእንጥልጥል መቅረቱን ለ WT Media ታማኝ የመረጃ ምንጭ ከጠቅላይ ሚኒስቴር ንፅህት ቤት አድርሷል።

​ይህቺ ወሬ መስማቷን ተከትሎ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ ደብዝዞ መጥፋቱ የተነገረ ሲሆን ምስጢሩን የሰሙትና ጥሩ ግንኙነት አላቸው የተባሉት የፌዴራል ከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዎችን የሆኑትን ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒን “አማልጂኝ” እያለ ሲማጸንና ሲያለቅስ መክረሙንም ምንጩ አክለው ገልጿል።

​በቅርቡ በፍትሕ ሚኒስቴር እና በፌደራል ፖሊስ የድንበር ተሸጋሪ ወንጀሎች ምርመራ ዘርፍ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመቀናጀት ባከናወኑት ሰፊ ምርመራ፤ አቶ ጥላሁን ከበደ፣ አቶ ተፈሪ አባተ (የወቅቱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ) እና አቶ ብርሃኑ ዘውዴ ዩናይትድ አረብ ኤሚሬትስ (ዱባይ) ውስጥ በሪል እስቴት ግንባታ ዘርፍ ሚሊዮኖችን አፍስሰው ግንባታ እያከናወኑ መሆናቸውን አረጋግጦ መንግሥት ንብረቶቹን አሳግዷል። ሕዝብን ዘርፈው፣ ሀብት አሽሽተው በጸያፍ የንግድና የኢንቨስትመንት ተግባር ውስጥ መሰማራታቸውም ተረጋግጧል።

​የአቶ ተፈሪ አባተና የአቶ ጥላሁን ከበደ የዝርፊያ ቁርኝት 12 ዓመታትን ይሻገራል። ጥላሁን የጋሞ ጎፋ ዞን አስተዳዳሪ በነበረበት ወቅት ተፈሪ የምክትል አስተዳዳሪና የፋይናንስ መምሪያ ኃላፊ በመሆን የሌብነቱን መረብ ተቆጣጥረውት ነበር። በአርባምንጭ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውኃ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ጋር ተያይዞ በ27 ሚሊዮን ብር ሙስና ሲከሰሱ ተፈሪ አባተ የጥላሁን አጃቢና አስፈጻሚ ነበር።

​በኋላም ጥላሁን ወደ ክልል ሲመጣ ተፈሪንና አርኮን እንደ የግል ምስጢር አደራ ያዘው። በዶ/ር ተስፋዬ በልጂጌ ቀና ዕይታና በጥላሁን የሞት ሽረት ትግል ተፈሪ የክልል ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊነትን በመጨበጥ ከአርባምንጭ እስከ ዱባይና አቡዳቢ የዘለቀ ቤተሰባዊ የሌብነት ሰንሰለት መዘርጋት ችለዋል።

​ይሁን እንጂ ተፈሪ ለቅርብ ሰዎቹ ጥላሁንን እያማና ሴረኝነቱን እየመሰከረ እንደሚገኝ ይነገራል። በተለይ በአርባምንጭ ከተማ በተከበረው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን አከባበር ስም አቶ ጥላሁን በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ጉድ እንዳደረገበት በምሬት ይጠቅሳል።
​
​የመረጃ ምንጮቻችንና የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ እነዚህ አካላት በሕዝብ ስም እየሠሩ በግል ሕይወታቸው ያከማቹት ሀብት እጅግ አስደንጋጭ ደረጃ ላይ ደርሷል።

​ዱባይ እና ሩዋንዳ፡ የሪል እስቴት ግንባታዎች፣ የቡናና የሻይ ቅጠል ማሳዎች፣ እንዲሁም የከብት ማደለብና የውጪ ኤክስፖርት ንግዶች።

​ባንኮችና አክሲዮኖች፡ ኦሞ ባንክ ላይ ያላቸው የአክሲዮን ድርሻ፣ የጋሞ ልማቱ ሰላም ማክሮ ፋይናንስ ባለቤትነት። ዮ ሆልዲንግ (የሰል ማጠቢያ) የማን ነው?

​ሹፌር የነበረው የብርሃኑ ዘውዴ ወንድም እንዴት በአንድ ሌሊት ቢሊየነር ሆነ? የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዱፄ ታአምሩ ከየት አምጥቶ ነው አዲስ አበባ ሃያት ሰሚት አካባቢ በሚሊዮኖች አውጥቶ ጂ+3 መኖሪያ ቤት የገዛው?!
​
​አቶ ጥላሁን ከበደ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጽኑ አቋም ባለመውደዳቸው “አሁንስ ተስፋዬ ማነው? አደም ፋራህ አይደለምን?” እያሉ ሲያወጡ ሲያወርዱ ይገኛሉ። በጎን በኩል ደግሞ “ሌሎቹን በልቻለሁ፣ እኔ እቀጥላለሁ” እያሉ የተሳሳተ ወሬዎችን ቢያናፍሱም፣ ከሰአት በኋላ ግን የክልሉን መንበር እንዳይመሩ ውሳኔዎች ላይ መደረጉ ታውቋል።

በተለይ እንደ መረጃ ከሆነ ሲያሳድዳቸው የነበረው የቀድሞው የጋሞ ጎፋ ዞን ድርጅት ኃላፊ አቶ አባይነህ አዴቶ ለክልሉ ፓርቲ ኃላፊነት መታጨቱ አንጀቱን አጭዶታል።

​የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ጉባኤውን ነገ ሐምሌ 17 እና 18 ቀን 2018 ዓ.ም. ከጧቱ 2:30 ጀምሮ በአርባምንጭ ከተማ እንደሚያካሂድ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ይህ ስብሰባ አዲስ ሀገራዊ ምርጫ በመካሄዱ ምክንያት የቀጣዩ አዲስ ምክር ቤት ከመመስረቱ በፊት የሚደረግ የመጨረሻው የምክር ቤት ስብሰባ ነው።

​የነገዎቹ የምክር ቤት ተሳታፊዎች ይህ የመጨረሻው የውይይት መድረክ መሆኑን ተገንዝበው፦ ​የውሸት ሪፖርቶችን ውድቅ አድርጉ፤ ​የጥላሁንን “የሰላምና የብልጽግና ተምሳሌት ክልል” ዲስኩር ውሸታም በሉት፤

​የዜይሴን ሰቆቃ፣ የቁጫን እንባ፣ የኮሬን መገደል፣ የቡርጂን መገለል፣ የደቡብ ኦሞን መገፋት፣ የአሪን መጠላት፣ የኮንሶ አለመልማት፣ የኧሌ መረሳት፣ የጎፋን መድከም እና የዎላይታ ሕዝብ የበይ ተመልካችነት አስታውሱ፤

​“ከወል ውሳኔ ይልቅ በአንባገነንነት የሚደረግ እንቅስቃሴ በቃ ሊባል ይገባል፤ ያልተሰራን ማንቆለጳጰስ የህሊና እስረኛ መሆን ነውና ከእስራችሁ ተፈቱ፤ የዱባዩን ሪል እስቴትና የሩዋንዳውን የንግድ ንብረት ከየት አምጥተህ ነው የምትገነባው ብላችሁ ጠይቁ!”

​“ሌባ ነህ ሲባል ‘ዎላይታ ስለሆንኩ፣ ጋሞ ስለሆንኩ’ እያሉ ብሔር ላይ የሚለጠፉትን አትስሙአቸው! የትኛውም ብሔር ማንነት የሌባ መደበቂያ አይደለም!” ያሉት የምንጭ ቃላት፣ የዚህን መንበር ቆሻሻ አጋልጦ በሕዝብ እንባ ላይ የሚሳለቁትን በአግባቡ መፈተሽ እንደሚገባ አሳስበዋል።

WT Media ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን በስም እየጠቆመና በሰነድ የተደገፉ የሙስና፣ የዘረፋ እና የብልሹ አሠራር መረጃዎችን ለሕዝብ ይፋ እያደረገ የሚገኘው ከማንኛውም ግል ጥቅም ወይም ከግል ጥላቻ በመነሳት ሳይሆን ሕዝቡ እየደረሰበት ያለውን መረን የለቀቀ ሰቆቃና ግፍ ለማጋለጥ በመሆኑ፤ አንባቢዎቻችን ይህንን አሠላለፍ በውል እንዲረዱልን እንወዳለን።

ሚዲያችን ይህንን ርምጃ የወሰደባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች በክልሉ የመንግሥት ሠራተኞች በጊዜው የሠሩበትንና ላባቸው ያፈሰሱትን የወር ደመወዝ በሰዓቱ ለማግኘት በመቸገራቸው ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ውድቀትና እንግልት መዳረጋቸው፤

​እናቶች መንገድና የጤና ተቋማት ባለመኖራቸው በወሊድ ወቅት ሕይወታቸው እያለፈ መሆኑ፣ ማኅበረሰቡም ንጹሕ መጠጥ ውኃ በማጣቱ ለተለያዩ በሽታዎችና ስቃይ መጋለጡ፤

​አብዛኛው የክልሉ ሕዝብ መሠረተ ልማት በማጣቱ ሲማሰን፣ በየአካባቢው የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ለሌብነትና ለትኩረት ማጣት ተጋልጠው መቆማቸው፤

​ለአብነትም በተፈጥሮ አደጋ ለተጎዱና ለሞቱ የጎፋ ወገኖች የተሰበሰበው ቢሊዮን የሚጠጋ ገንዘብ ተዘርፎ ፍጹም ተጠያቂነት የጠፋበት መሆኑ፤

​የዜይሴ እና የቁጫ ማኅበረሰቦችና ሌሎች መሰሎቹ በማንነታቸው ብቻ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ግድያ፣ እስራት እና ስደት እየተፈጸመባቸው መሆኑ ከበርካታ ምክንያቶች ጥቂቶች ናቸው።

በመሆኑም WT Media እንደወትሮው ሁሉ የሕዝብ ድምፅ ሆኖ ሕዝባዊ አደራን ለመወጣት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን፣ ፍትሕ ለተነፈጋቸው ወገኖች ቋሚ ጠበቃ በመሆን እንዲሁም በክልሉ ያለውን መንግስታዊ ብልሹ አሠራር፣ ሌብነት፣ ኢፍትሃዊነት፣ ሰብዓዊ መብት ጥሰት እና በሕዝቡ ላይ እየደረሰ ያለውን ከፍተኛ እንግልት በተጨባጭ መረጃና ማስረጃ አስደግፎ ማጋለጡን አጠናክሮ እንደሚቀጥል በድጋሚ ያረጋግጣል።