በሳውዲ አረቢያ እስከ 200 የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን የሞት ፍርድ አፈፃፀምን በመጠበቅ ላይ እንደሚገኙ ተገለፀ

በሳውዲ አረቢያ በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ እስከ 200 የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ዜጎች የተበየነባቸውን የሞት ፍርድ አፈፃፀም በመጠበቅ ላይ እንደሚገኙ ተነግሯል። ይህም በሳውዲ አረቢያ በስደት ላይ በሚገኙ የውጭ ሀገር ዜጎች ላይ የሚሰጠው የሞት ፍርድ ውሳኔ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን የሚያሳይ ሆኗል።

ቢቢሲ ትግርኛ ያገኛቸውን የምስክሮች ቃል መሰረት በማድረግ እንደዘገበው በሳውዲ አረቢያ እስር ቤቶች ውስጥ የሚገኙ በርካታ የሞት ፍርድ የተበየነባቸው ኢትዮጵያውያን የደረሰባቸውን በደል እና ያለፉበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅ ከእስር ቤት የሞባይል ስልክ በመጠቀም መረጃ ማቃበል ችለዋል።

ጋዜጠኞች ፍርዱ ከተበየነባቸው መካከል ከሰባት ኢትዮጵያውያን እስረኞች ጋር በቀጥታ የተነጋገሩ ሲሆን በደርዘን የሚቆጠሩ ወገኖቻቸው የሞት ፍርድ አፈፃፀምን በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ አረጋግጠዋል።

ይህ መረጃ በኢትዮጵያውያን ዜጎች ላይ የሚበየነው የሞት ፍርድ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ያሳያል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት እ.ኤ.አ. በ2024 በሳውዲ አረቢያ የሞት ፍርድ የተፈጸመባቸው ኢትዮጵያውያን ቁጥር ሁለት የነበረ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2025 ግን ይህ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ ወደ 35 ደርሷል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ በሳውዲ ልዩ ልዩ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ እስከ 200 የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን በሞት ፍርድ ጥላ ስር እንደሚገኙ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች አስጠንቅቀዋል።

የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች እና ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች በሳውዲ የፍትህ ስርዓት ውስጥ የሚያልፉ ስደተኞች ህጋዊ ወኪል (ጠበቃ) የማግኘት፣ አስተርጓሚ የማግኘት እና የችሎት ሂደቶች ግልፅነት ማጣት ላይ ደጋግመው ስጋታቸውን ገልፀዋል።

 ይህ በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረው የበረታ ቅጣት የሲቪል ማህበራት እና የቀጠናው የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች የኢትዮጵያ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ጣልቃ እንዲገባ እና የህግ ድጋፍ እንዲያደርግ ዳግም ጥሪ እንዲያቀርቡ አስገድዷቸዋል።

#WTMedia #Ethiopia #SaudiArabia #HumanRights #AmnestyInternational