GridArt_20260731_113147180

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሟች ታዋቂው ተጫዋች አለልኝ አዘነ መዝገብ ላይ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

​በታዋቂው አለልኝ አዘነ የግድያ መዝገብ ላይ የፍትሕ ሂደቱ አዲስ ምዕራፍ ይዟል!

​ከዚህ ቀደም በጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሰውና በሰነድ ማስረጃዎች ተረጋግጦባቸው የ16 እና 15 ዓመት ፅኑ እስራት ተፈርዶባቸው የነበሩት የሟች ባለቤት ወ/ሮ አደይ ጌታቸው እና የእህቷ ባለቤት ሉንጎ ሉቃስ በይግባኝ ሰሚው ችሎት ሙሉ በሙሉ በነፃ እንዲሰናበቱ መወሰኑ ይታወሳል።

ይህ ውሳኔ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ማህበረሰብን፣ የሟች ቤተሰቦችን እና ፍትሕ ናፋቂዎችን በእጅጉ ያሳዘነና በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ጥያቄ ያስነሳ መሆኑ በወቅቱ በሰፊው ተዘግቦ ነበር.

​ይሁን እንጂ ጉዳዩን ይዞት የቆየው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መዝገብ ቁጥር 010926 (ቀን 09/11/2018 ዓ.ም) ባሰፈረው ሐሳብ እና በሰጠው የፍሬ ትዕዛዝ፣ መዝገቡ ተጨማሪ ምርመራ እና ማጣራት እንዲደረግበት መወሰኑን አዳዲስ የፍርድ ቤት ሰነዶች ለ WT Media አረጋግጠዋል።
​
​የፍርድ ቤቱ ሰነዶች እንደሚያመለክቱት በቀድሞው የፍርድ ሂደት ውስጥ የሚከተሉት ነጥቦች በድጋሚ ሊመረመሩ እንደሚገባ ታዟል።

​መዝገብ ውስጥ መገኝት የሚገባው መረጋገጥ የሚገባው ድምፅ መኖሩ፣ የአርሶ አደር ምስክርነት ቃል የተሰጠበት ሁኔታ፣ እና ከሶስተኛ ወገን ወንጀል ጥፋተኛ የመሆን አለመሆን ጉዳይ። የዶክተር የምርመራ ውጤት እንደየሁኔታው ሊመረመር እንደሚገባ፣ እንዲሁም በእያንዳንዱ አካባቢዊ ማረጃ ቃል ላይ ጥርጣሬ የተፈጠረ በመሆኑ የፓቶሎጂ ወይም የአካባቢዊ ማረጃ ኘሩፍ አመጣጥ ሥርዓት ሕግ አግባብ በድጋሚ መታየት እንዳለበት ተመልክቷል።

​ሰበር ሰሚ ችሎቱ ጉዳዩን በጥልቀት ለመመርመር ያስችል ዘንድ ​መልስ ሰጪዎች (ተጠሪዎች) ለቀረበው የሰበር አቤቱታ የሚሰጡትን መልስ በጽሁፍ አዘጋጅተው ከፍ/ቤት መፃፍ ጋር እንዲያቀርቡ አዟል።

​ለዚህም መከላከያ መልስ ለመስጠት የችሎቱ ቀነ-ቀን 23/11/2018 ዓ.ም ተቆርጧል፤ ተጠሪዎችም በዕለቱ ላልተዘጋጀው መልስ በጽሁፍ አዘጋጅተው ለአርባ ምንጭ ለሚገኘው ተከታይ ችሎት እንዲያቀርቡ ተወስኗል።

​የሟች ቤተሰቦች ከዚህ ቀደም ለ WT Media በሰጡት ቃል ወንጀሉ የተፈፀመበት ቦታ አርባ ምንጭ ሆኖ ሳለ የፍርድ ሂደቱ አግባብ ባልሆነ መንገድ ወደ ዎላይታ ሶዶ እንዲዛወር መደረጉ ለዚህ ውዛግብ መነሻ መሆኑን በዕንባ ገልጸው ነበር።

በተለይም በጥፋተኝነት ተፈርዶባት በነበረችው በአደይ ጌታቸው ጀርባ የወቅቱን የክልሉን ባለስልጣናት የዝምድና ትስስር እና ስልጣን በመጠቀም ፍርዱን ለማዛባት ሲሸረብ የነበረው ሴራ የንብረት ባለቤትነት ክሶችን ጭምር ለማደናቀፍ የታለመ እንደነበር ቤተሰቡ በምሬት ይናገራል።

​በአሁኑ ወቅት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ያስቀመጠው አቅጣጫ እና የሰጠው ትዕዛዝ መዝገቡ በድጋሚ በህግ ማዕቀፍ ውስጥ ተፈትሾ እውነተኛው ፍትሕ እንዲሰፍን የሚያስችል ተስፋ የሰነቀ ቢሆንም የሟች ቤተሰቦች እና መላው የስፖርቱ ማህበረሰብ የጉዳዩን ሂደት በጥንቃቄ እየተከታተሉት ይገኛሉ።