“ግንባታው ለጊዜው ቢታገድም የፍርድ ቤት ውሳኔ አለመከበሩ በዎላይታ ሶዶ ከተማ የህግ የበላይነት ጥሰት ስጋት ፈጥሯል” ሲሉ ነዋሪዎች ቅሬታ አቅርቧል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መዲና በሆነቸው በዎላይታ ሶዶ ከተማ፣ መርካቶ ክፍለ ከተማ ፋና ቀበሌ (በዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ዋና መግቢያ ፊትለፊት) በህዝብ መተላለፊያ መንገድ ላይ የክልሉን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ በመጣስ ይካሄድ የነበረው አነጋጋሪ ግንባታ፣ WT Media ያቀረበውን የምርመራ ዘገባ ተከተሎ ለጊዜው በቃል ትዕዛዝ እንዲታገድ መደረጉን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
WT Media ሰኔ 8 ቀን 2018 ዓ.ም (June 15, 2026) ባስነበበው አጋላጭ ዘገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት መዝገብ ቁጥር 68670 በዕለት 27/07/2016 ዓ.ም የዞኑን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ በመሻር፣ ቦታው የህዝብ መተላለፊያ መሆኑን ማረጋገጡንና ህገ-ወጥ የይዞታ ካርታውና ግንባታው እንዲሰረዝ መወሰኑን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ዘገባው ይፋ በሆነ በሁለተኛው ቀን የከተማው አስተዳደር አካላት በቦታው ላይ ተገኝተው ግንባታው ለጊዜው እንዲቆም በቃል ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። በተጨማሪም ጉዳዩን በአካል አጣርቶ እልባት የሚሰጥ ኮሚቴ በሳምንት ውስጥ እንደሚዋቀር ተገልጾ የነበረ ቢሆንም የተቀመጠው ጊዜ አልፎ ኮሚቴው ሳይመጣ ቀርቷል።

የአካባቢው ነዋሪዎች WT Media የህዝብ ድምፅ በመሆን ላደረገው ሽፋን ከፍተኛ ምስጋናቸውን ያቀረቡ ቢሆንም ግንባታው በይፋ በጽሁፍ ደብዳቤ ሳይሆን “በቃል ብቻ” እንዲቆም መደረጉ ግን ከፍተኛ ስጋት ፈጥሮባቸዋል።
የማዘጋጃ ቤቱ አመራሮች ህዝቡ እንዲረጋጋ ጊዜ በመግዛት፣ ግንባታውን ድጋሚ ለማስጀመር ይመቻል ያሉትን ሁኔታ እያመቻቹ ሊሆን እንደሚችል ነዋሪዎቹ ይጠረጥራሉ።
በአካባቢው የተፈጠረው ውዝግብ የማዘጋጃ ቤቱን ጥልቅ የአሰራር ብልሽት እና የጥቅም ግጭት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ።
ቀደም ሲል የነበረውን የህዝብ መንገድ በመዝጋት የመጀመሪያውን ህገ-ወጥ አሰራር የዘረጉት አካል፣ አሁን ደግሞ ተመልሰው አመራር ሆነው መሾማቸው አሰራሩን ሙሉ በሙሉ ለግል ጥቅም የተጋለጠ አድርጎታል።
ከዚህ ቀደም ይኸው ማዘጋጃ ቤት መስጊድ የተነሳበትን ቦታ ለባለሀብት በመሸጥ፣ የማዘጋጃ ቤቱ የሥራ ኃላፊዎች ባገኙት ህገ-ወጥ ጥቅም በሌላ ከተማ መኖሪያ ቤት እስከ መግዛት መድረሳቸውን ነዋሪዎች በምሬት ይገልጻሉ።

በአሁኑ ወቅት ግንባታው ቆሞ የሚገኝ ቢሆንም፣ “በቃል የተሰጠ እገዳ የነገ ተስፋችንን አይታደግም” የሚሉት ነዋሪዎቹ፦
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጠው የመጨረሻ ውሳኔ በመሬት ላይ ተተግብሮ የተዘጋው መንገድ ሙሉ በሙሉ እንዲከፈት፣
በህዝብ መንገድ እና መሬት ላይ ንግድ የሚያካሂዱ የማዘጋጃ ቤት አመራሮች ላይ ተጠያቂነት እንዲሰፍን፣
እንዲሁም ዘላቂ እና ህጋዊ ፍትህ እንዲሰጣቸው ጥሪያቸውን አሁንም በምሬት እያቀረቡ ይገኛሉ።
WT Media የህዝብ ዓይንና ጆሮ በመሆን ይህ የፍርድ ቤት ውሳኔ ተከብሮ የህዝብ መንገዱ ሙሉ በሙሉ እስኪከፈት ድረስ ጉዳዩን በቅርበት መከታተሉን እና ማጋለጡን ይገፋበታል።