በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በዎላይታ ሶዶ ከተማ የተቀናጀና ዘመናዊ መልክ ያለው ግዙፍ የፋይናንስ ማጭበርበር ወንጀል መፈጸሙ ተሰምቷል። በወንጀል ድርጊቱ ከ500 ሚሊዮን (ግማሽ ቢሊዮን) ብር በላይ የሚገመት የበርካታ ወገኖች ገንዘብ የተበላ ሲሆን ሰለባ ከሆኑት መካከል ታዳጊ ወጣት ነጋዴዎች፣ ታዋቂ ባለሀብቶች፣ የዞን ከፍተኛ አመራሮች፣ የፖሊስ አዛዦች እንዲሁም የመንግሥት የፋይናንስ ዘርፍ ሰራተኞች እንደሚገኙበት ለ WT Media የደረሱ አዳዲስ ማስረጃዎች ያመላክታሉ።
እንደ ምንጮቻችን ገለጻ የማጭበርበር ድርጊቱ የተካሄደው ከመደበኛው የባንክ አሠራርና ሕግ ውጪ በሆነ መንገድ ነው። ተጠርጣሪዎቹ የሰዎችን ልብ ለማማለልና ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ለመሰብሰብ የተጠቀሙበት ዋነኛ ስልት “በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ የትርፍ ድርሻ ክፍያ” የሚል የተስፋ ቃል ነው።
ተጠርጣሪዎቹ “1 ሚሊዮን ብር ያስቀመጠ ሰው በሳምንት 70 ሺህ ብር (ወይም በወር እስከ 300 ሺህ ብር) የትርፍ ድርሻ ያገኛል” በሚል ማታለያ በርካታ ነጋዴዎችንና ግለሰቦችን ወደ መዋቅሩ አስገብተዋል።
ለተቀበሉት ገንዘብ ዋስትና በሚል ከባንክ ሲስተም ውጪ የተዘጋጁ ደረቅ ቼኮችን (Unfunded Cheques) ለአስቀማጮቹ ይሰጡ የነበረ ሲሆን መጀመሪያ ላይ ለተወሰኑ ሳምንታት የትርፍ ክፍያዎችን በትክክል በመክፈል የሰዎችን አመኔታ አትርፈዋል።
በሂደቱ እምነት ያደሩ በርካታ ግለሰቦች ያሏቸውን ጥሪትና የንግድ እንቅስቃሴ ገንዘብ በሙሉ ወደ መዋቅሩ ያስገቡ ሲሆን ከአንድ ግለሰብ ብቻ ከ2 ሚሊዮን ብር እስከ 30 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ገንዘብ መወሰዱ ተረጋገጧል።
ለ WT Media የደረሱት አዳዲስ ማስረጃዎች በወንጀሉ ሰንሰለት ውስጥ ያሉ ዋና ዋና ተሳታፊዎችን ማንነትና በአሁኑ ወቅት የሚገኙበትን ሁኔታ በዝርዝር ያመላክታሉ።
ብሩክ እሸቱ (በእስር ላይ የሚገኝ) በማጭበርበር መዋቅሩ ውስጥ ዋና የቼክ አሰራጭና አስተላላፊ ሆኖ ሲሰራ የነበረ ግለሰብ ነው። ለአስቀማጮችና ለደንበኞች “በወር እስከ 300 ሺህ ብር ይከፈላችኋል” በሚል ቼክ የመስጠትና ገንዘብ የመሰብሰብ ሚና እንደነበረው የታወቀ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በዎላይታ ሶዶ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ በቁጥጥር ስር ውሎ በምርመራ ላይ ይገኛል።
ዳዊት ሀይለማርያም (ያልተያዘ) ቀደም ሲል የመሉ ወንጌል ቤተክርስቲያን ገንዘብ ያዥ (Treasurer) የነበረ ግለሰብ ሲሆን ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ወደዚሁ ህገወጥ የማጭበርበር አሠራር ማስገበቱ ተገልጿል።
ግለሰቡ የፖሊስ አዛዥና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ወዳጅ እንደሆነ የተጠቀሰ ሲሆን እስካሁን በቁጥጥር ስር እንዳልዋለና በነጻነት እንደሚንቀሳቀስ ምንጮች አረጋግጠዋል።
ተጠርጣሪዎቹ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ከሰበሰቡ በኋላ የታቀደውን የትርፍ ክፍያ ማቆማቸውንና ዋና ዋና አስተባባሪዎች መሰወራቸውን ተክተሎ በከተማዋ ትልቅ ውጥረት ነግሷል።
የምርመራው ሂደት ሊንቀሳቀስ የቻለው የፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች ራሳቸው በዚሁ የማጭበርበር ድርጊት የገንዘብ ተጎጂ መሆናቸው ከተረጋገጠ በኋላ እንደሆነ ይነገራል።
ጉዳዩ ወደ ህግ ከተመራ በኋላ ግን ሂደቱ በሚፈለገው ፍጥነት እየሄደ እንዳልሆነ ተጎጂዎች ይናገራሉ። በወንጀሉ ውስጥ የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች፣ የፖሊስ አመራሮች እና የፋይናንስ ዘርፍ ኃላፊዎች ስም በሰፊው በመነሳቱ “ምስጢሩ ይወጣል” በሚል ስጋት በምርመራው ላይ ተጽዕኖ የማሳደርና ሂደቱን የማደናቀፍ እንቅስቃሴዎች መኖራቸው ተጠቁሟል።
በአሁኑ ወቅት በርካታ አመራሮች፣ ነጋዴዎችና ባለሀብቶች በእጃቸው ምንም ዋጋ የሌላቸው ደረቅ ቼኮችን ይዘው ዋጋ አጥተው ይገኛሉ። ተጎጂዎች ጉዳዩ በዞን ደረጃ ተሸፍኖ እንዳይቀር የፌደራልና የክልል የፍትህና የህግ ማስከበር አካላት በገለልተኝነት ጣልቃ በመግባት የህዝቡን ገንዘብ እንዲያስመልሱና አጥፊዎችን ለፍትህ እንዲያቀርቡ በጥብቅ እየጠየቁ ይገኛሉ።
እየተካሄደ ያለውን የህግና የምርመራ ሂደት ላለማደናቀፍ እንዲሁም የህግ ሂደቱን ጥራት ለመጠበቅ ሲባል የገንዘብ ተጎጂ የሆኑ ግለሰቦችን ስም ዝርዝር እና ማስረጃዎችን WT Media ለጊዜው ይፋ ካደረጋቸው መቆጠቡን ያስታውቃል።
ተጎጂዎች ጉዳዩ በዞን ደረጃ ተሸፍኖ እንዳይቀር የፌደራልና የክልል የፍትህና የህግ ማስከበር አካላት በገለልተኝነት ጣልቃ በመግባት የህዝቡን ገንዘብ እንዲያስመልሱና አጥፊዎችን ለፍትህ እንዲያቀርቡ በጥብቅ እየጠየቁ ይገኛሉ።
በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎችና ተጎጂዎች “ሕግን ለማስከበር ኃላፊነት ያላቸው አካላት ጭምር በዚህ መንገድ ሕገወጥ ድርጊት ውስጥ ተዘፍቀው የሚገኙ ከሆነ ሕብረተሰቡ ሳያውቅ አሁንም ስንት ዓይነት ወንጀል እየተሠራ ይሆን?” ሲሉ ከፍተኛ ሥጋት እንዳደራባቸው ገልጸዋል።
በመሆኑም ሁኔታው በገለልተኝነት እንዲጣራ እና ጥፋተኛ በሆኑት አመራሮችና አካላት ላይ አስፈላጊው ማጣራት ተደርጎ አርአያነት ያለው እርምጃ እንዲወሰድ በጥብቅ እየጠየቁ ይገኛሉ።
WT Media ይህንን ግዙፍ የፋይናንስ ማጭበርበር ጉዳይ በጥልቀት መከታተሉን የሚቀጥል ሲሆን የከተማዋን ፖሊስ፣ የዞኑን አስተዳደር እና የሚመለከታቸውን የፍትህ አካላት ይፋዊ ምላሽ ለማካተት ጥረት በማድረግ ላይ ነው።