GridArt_20260815_220956411

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በኮሬ ዞን ጎርካ ወረዳ ቆሬ ቀበሌ በዛሬው ዕለት በፀረ-ሰላም ኃይሎች በተከፈተ ድንገተኛ ጥቃት የሁለት ንጹሐን አርሶ አደሮች ሕይወት ማለፉን የኮሬ ዞን አስተዳደር አስታውቋል።

አርሶ አደሮቹ በማሳቸው የእርሻ ሥራ ላይ እያሉ የተፈጸመው ይህ እኩይ ድርጊት የሕዝቡን የጋራ ሰላም ለማናጋት፣ አብሮነትን ለማላላት እና የልማት ሥራዎችን ለማደናቀፍ የታለመ በመሆኑ በጽኑ መወገዙ ተገልጿል።

​የኮሬ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ረ/ፕሮፌሰር ሚሊዮን ደሳለኝ በሰጡት መግለጫ፤ ይህ አሳዛኝ ድርጊት ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት ከማጠናከር ውጪ ወደኋላ እንደማያስቀረው ገልጸዋል።

በቀጣይም ከአጎራባች ዞኖች፣ ከክልል መንግሥት እና ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ለአካባቢው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እና የህዝቡን ደህንነት ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

​ሕዝቡ በዚህ አሳዛኝ ክስተት ሳይደናገጥ አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ መደበኛ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴውን እንዲቀጥል ጥሪ የቀረበ ሲሆን ለአስተዳዳሪው መግለጫ መሠረት ለሟቾች ቤተሰቦች፣ ወዳጅ ዘመዶች እና ለመላው የኮሬ ሕዝብ መጽናናት ተመኝቷል።