IMG-20260816-WA0054

​የዎላይታ ሕዝብ ታሪክ ተመራማሪና የዎላይታ ሶዶ ከተማ የቀድሞ ከንቲባ አቶ አብራሃም ባቾሬ ሥርዓተ ቀብር በዛሬው ዕለት ተፈፅሟል።

​አቶ አብራሃም ባቾሬ በሕይወት ዘመናቸው በልማት፣ በአስተዳደር፣ በኮሙኒኬሽን፣ በባህልና ታሪክ ጥናት፣ በማኅበረሰብ ዕርቅ ዘርፍ ለሀገርና ለሕዝብ ጉልህ አሻራቸውን አሳርፈዋል።

​የዎላይታ ብሔር የዘመን መለወጫ “ጊፋታ” በዓል ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ እውቅና አግኝቶ በዩኔስኮ የዓለም የማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ ላይ እንዲሰፍር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

​በኢትዮጵያ አየር ኃይል፣ በዓለም አቀፉ የሕፃናት አቀፍ ድርጅት እና በዎላይታ ልማት ማኅበር ውስጥ እንዲሁም የሶዶ ከተማ ከንቲባ በመሆን አገልግለዋል።

​በተጨማሪም የወላይታ የሀገር ሽማግሌ በመሆን በህዝብ ለህዝብ ግኑኝነት፣ በማስታረቅ እና በሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ በእድሜ ዘመናቸው የማይረሳ ታሪክ አኑረው አልፈዋል።

​አቶ አብራሃም ባቾሬ ባለትዳር እና የሶስት ልጆች አባት ነበሩ።

​የዎላይታ ሕዝብ ታሪክ ተመራማሪና የዎላይታ ሶዶ ከተማ የቀድሞ ከንቲባ የነበሩት አቶ አብራሃም ባቾሬ ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ነሐሴ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ይታወሳል።

​የአቶ አብርሃም ባቾሬ አጭር የህይወት ታሪክ 👇

​አቶ አብርሃም ባቾሬ ከአባታቸው ከአቶ ሽርኮ ሃላላ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ጋልዳሜ ባቾሬ በ1946 ዓ.ም በቀድሞ የዎላይታ አውራጃ በሶዶ ዙሪያ ወረዳ ዛላ ሻሻ ቀበሌ ተወለዱ። አቶ አብራሃም ይጠሩ የነበሩት በአያታቸው በአቶ ባቾሬ ስም ነበር።

​አቶ አብርሃም በልጅነት ዘመናቸው እንደማንኛውም የገጠር ልጅ እርሻ አርሰው እንጨት ሰብረው ውሃ ቀድተው ያደጉ ሲሆን ለወላጆቻቸው ታዛዥ በዕድሜ እኩዮቻቸው ተወዳጅ ልጅ ነበሩ።

​ዕድሚያቸው ለትምህርት ሲደርስ በቦሣ ሉትራን ሚሺን ት/ቤት ፊደል በመቁጠር የጀመሩ ሲሆን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በሶዶ ጊዮርጊስ ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በሶዶ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተከታትለዋል።

​አቶ አብርሃም ባቾሬ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ እያሉ በ1967 ዓ.ም በጊዜው የነበረው መንግስት መሀይምነትን ለማጥፋት ባዘጋጀው የእድገት በህብረት የእውቀትና የሥራ ዘመቻ ለመሳተፍ ወደ ገጠሪቱ ኢትዮጵያ ዘመቱ።

​በዚህም ዘመቻ ከሌሎች ዘማቾች ጋር በመሆን ህዝቡን በማስተማር፣ በመንቃትና በማደራቸት መሬት ላራሹ የመሳሰሉ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ያደረጉ የጊዜው መንግስት አዋጆች መሬት ላይ እንዲወርዱ በማድረግ የህዝብ አገልጋይነትን መለማመድ ጀመሩ።

​ከዘመቻው ፍጻሜ በኋላ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በማጠናቀቅ ከልጅነታቸው ጀምረው ሲመኙት ነበረውን ህልማቸውን ለማሳካት በ1969 ዓ.ም የኢትዮጵያ አየር ኃይልን በፍላጎት ተቀላቀሉ።

​በአየር ኃይል ቆይታቸው በአየር ትንበያ (ሜትሮሎጂ) ባለሙያነት በደብረዘይት፣ በጎዴ እና በአሥመራ ተዘዋውረው ፍጹም በሆነ የሀገር ፍቅር ስሜት ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል።

​በአየር ኃይል ቆይታቸው በቀድመው የሶቬት ህብረት የትምህት ዕድል በማግኘት በኪርጊዝስተን (Kyrgyzstan) ለአምስት ዓመት ተጨማሪ ትምህርት ተከታትለው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።

​ከ”Kyrgyzstan” በተጨማሪ በሥራ ዓለም በነበሩበት ጊዜ ወደ ዩክሬን፣ ኡዝቤኪስታን እና ደቡብ አፍሪካ ተጎዘው የሥራ ልምድ ቀስመዋል።

​አቶ አብራሃም ከሶቬት ህብረት ከተመለሱ በኋላ የተጨማሪ ትምህርት ፍላጎታቸውን ለማሳከት በተሰጣቸው ፈቃድ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማታው ፕሮግራም በመመዝገብ ለትምህርት በነበራቸው ጽኑ ፍላጎት በየቀኑ ከደብረዘይት እስከ ስድስት ኪሎ በመመላለስ በፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት በማዕረግ ተመርቀዋል።

​አቶ አብርሃም በ1983 ዓ.ም የመንግስት ለውጥ ተከትሎ ከሥራ ተፈናቅለው በነበሩበት ወቅት እጮኛቸው ከነበሩት የትዳር አጋራቸው ጋር በ1986 ዓ.ም በሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን በተቀደሰ ጋብቻ ትዳር በመመስረት አንድ ወንድ እና ሁለት ሴቶችን በድምሩ ሦስት ልጆችን እና ሦስት የልጅ ልጆችን አፍርተዋል።

​አቶ አብራሃም ከልጆቻቸው በተጨማሪ እህት ወንድሞቻቸውን እንዲሁም የወንድምና የእህቶቻቸውን ልጆች ምንም ልዩነት ሳያደርጉ አስተምረው ለወግ ለማዕረግ ያበቁ በቤተሰቦቻቸው ዘንድ “ጎዶ” እየተባሉ በፍቅር ስም የሚጠሩ የሁሉም አባት ነበሩ።

​አቶ አብርሃም ትዳር ከመሠረቱ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ “Save the Children” በተባለ ግብረሰናይ ድርጅት በከፍተኛ ደመወዝ ተቀጥረው ሥራ ጀመሩ።

​ይሁን እንጂ ለዎላይታ ህዝብ በኢኮኖሚ መለወጥ በነበራቸው ጽኑ ፍላጎት በአዲስ መልክ የተቋቋመው የወላይታ ልማት ማህበር ባደረጉላቸው ጥሪ መሠረት የተሻለ ደመወዝና ጥቅማጥቅም በመተው ከመጀመሪያው በግማሽ በሚያንስ ደመወዝ በመቀጠር የልማት ማህበሩ የመጀመሪያው ፕሮጀክት ማናጀር በመሆን አገልግለዋል።

​ለዎላይታ ሊቃ ትምህርት ቤት መመስረትም የመጀመሪያውን ሀሳብ በማቅረብ የሊቃ ት/ቤት ዕውን እንዲሆን በማድረግ የአቶ አብርሃም ድርሻ ከፍተኛ ነበር።

​ከዚህም ሌላ በልማት ማህበሩ እስከ ቦርድ ሰብሳቢነት በማገልገል ወልማ አሁን ለደረሰበት ደረጃ መሠረት የጣሉ የህዝብ ልጅ ነበሩ።

​አቶ አብራሃም በወልማ የጀመሩትን የህዝብ አገልግሎት አጠናክረው በመቀጠል የሶዶ ማዘጋጃ ቤት ሥራ አስኪያጅ በመሆን በጊዜው በከተማው ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ ያስከትሉ የነበሩትን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለማሻሻል በነበራቸው ህልም ያለምንም ማጋነን ዘወትር ከጠዋቱ አንድ ሰዓት እስከ ምሽቱ ሦስት ሰዓት በቢሯቸው ተቀምጠው ባለጉዳይ አገልግሎት በመስጠት ራሳቸውን አደጋ ላይ ጭምር በመጣል ታሪክ የማይረሳውን ውለታ ለዎላይታ ሶዶ ከተማ ህዝብ ውለዋል።

​በዚህም የስራ አፈጻጸማቸው ተገምግሞ የሶዶ ከተማ ከንቲባ በመሆን ተሹመው ከተማዋ አሁን ለደረሰችበት ደረጃ የማይናቅ አሻራ አሳርፈዋል።

​የፖለቲካል ሳይንስ እና አለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ አቶ አብራሃም ባቾሬ ከህዝብ አመራርነት በተጨማሪ በዎላይታ ዞን ባህል ቱሪዝምና የመንግስት ኮሙኒኬሽን መምሪያ የኮሙኒኬሽን ዘርፍ አስተባባሪ በመሆን በዕድሜ ጡረታ እስከተገለሉበት እስከ 2010 ዓ.ም. ድረስ አገልግለዋል።

​በዚህም ሙያቸው በሚፈቅደው መሠረት ለየዞኑ ህዝብ ወቅታዊ መረጃዎች ተደራሽ እንዲሆኑ በማስቻል፣ በህዝብና በመንግስት መካከል ጤናማ የመረጃ ፍሰት እንዲኖር በማድረግ ዘርፋን በዕውቀት መርተዋል።

ከዚህም ሌላ የወላይታ ቴሌቪዥን የቦርድ አባል በመሆንም አገልግለዋል።

​አቶ አብራሃም ከመደበኛ ሥራቸው በጡረታ ከተገለሉ በኋላ የወላይታ ህዝብ የሀገር ሽማግሌ በመሆን የህዝቡ ባህልና ታሪክ እንዲሁም የፈጠራና የስነጥበብ ውጤት የሆኑ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ትውልድ ተሻጋሪ እንዲሆኑ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

​በተለይም የዎላይታ ዘመን መለወጫ የጊፋታ በዓል የሰው ልጆች ወካይ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ በመሆን በUNESCO እንዲመዘገቡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

​አቶ አብርሃም በመንፈሳዊ ህይወታቸው በሚያመልኩበት ቤተ እምነት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ተቀብለው በስሙ በመጠመቅ በቅድስና እግዚአብሔርን በመፍራት የሐዋርያዊት ቤተክርስቲን የእምነት አንቀጽ ጠብቀው የኖሩ፣ በማገልግሎታቸው የበረቱ ወንድም ነበሩ።

​አቶ አብርሃም በህይወታቸው ዘመን ሁሉ አምላካቸውን፣ ህዝባቸውን እና ሀገራቸውን በፍጹም ታማኝነት አገልግለው ባደረባቸው ህመም ምክንያት በህክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ72 ዓመታቸው ነሀሴ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ወደ አምላካቸው ተሰብስበዋል።

​አቶ አብርሃም በመልካም ተግባራቸው ምክንያት ስማቸው ሁል ጊዜ ከመቃብር በላይ ሆኖ ይኖራል።

​የአሁኑ ትውልድ ከወንድም አብርሃም የአላማ ፅናትን፣ ለህዝብ መኖርን፣ የሰው ፍቅርን፣ ለተወለዱበት ማህበረሰብ ባህልና ታሪክ መቆርቆርን፣ የልብና የእጅ ንፅህናን፣ በፍጹም ንፅህና ሀገርና ህዝብን ማገልገልን፣ አስታራቂነትን ወዘተ ይማራል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።

​አቶ አብርሃም ለህዝብና ለሀገር ለከፈሉት መልካም ተግባር በተለይም ለዎላይታ ህዝብ ባህል፣ ታሪክና ቋንቋ እድገት ላበረከቱት ትውልድ ለማይረሳው ተግባራቸው ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት ኃላፊዎች አንድ ቋሚ ማስታወሻ እንዲያቆሙላቸው በአክብሮት እንጠይቃለን።

​ለባለቤታቸውና ለልጆቻቸው እንዲሁም ለወዳጅ ዘመዶቻቸው ጌታ ኢየሱስ መጽናናትን ይስጣችሁ🙏