1000136132


የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በክልሉ እየተስተዋለ ባለው የልማት ክፍፍል እና የፍትሃዊነት እጦት ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ዜጎችን “ስራ ሳይሰሩ በባዶ የሚለፍፉ” በሚል መልክ ማሸማቀቃቸው በብዙዎች ዘንድ ከፍተኛ ትችትና ቁጣ አስነስቷል።

​ርዕሰ መስተዳድሩ በይፋዊ የፌስቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት ንግግር፤ በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን በመጥቀስ፣ ስለ ፍትሃዊነት የሚጠይቁ አካላት “ሥራ ሳይሰሩ” ሰበብ የሚፈልጉ እና ሕዝብን የሚያደናግሩ ናቸው የሚል ይዘት ያለው አስተያየት ሰንዝረዋል።

ይሁን እንጂ ይህ ንግግር ለረጅም ጊዜ በፍትሃዊ ልማት እጦት እና በመልካም አስተዳደር ችግር ሲማቅቁ የቆዩ የክልሉ ነዋሪዎችን ክብር የሚነካና የሕዝብን ጥያቄ ችላ ያለ አደገኛ አካሄድ መሆኑን ተቺዎች እየገለጹ መሆኑን WT Media ለመታዘብ ችሏል።

አቶ ጥላሁን ከበደ “ፍትሃዊነት” የሚለውን ሕጋዊና ሰብአዊ ጥያቄ ወደ “ሥራ አለመሥራት” እና “ስድነት” በመቀየር ለሕዝብ የቀረበውን የልማት ፍትሃዊነት ጥያቄ ለማጣጣል መሞከራቸው፤ በክልሉ ያለው የልማት አድሎአዊነት ሥር የሰደደ መሆኑንና አመራሩ ለሕዝብ ብሶት ያለው ቦታ ምን ያህል ጠባብ እንደሆነ ያሳያል ተብሏል።

​ሕዝቡ የሚጠይቀው “ልማት እንዲሰራ ብቻ ሳይሆን ልማቱ በየትኛውም የክልሉ ክፍል በፍትሃዊነት እንዲዳረስ ነው” ያሉት ነዋሪዎች፤ መሪዎች ሕዝብን ከማሸማቀቅ ይልቅ የገባነውን ኪዳን ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባቸው ነበር ሲሉ መልሰዋል።

​WT Media የሕዝብን ጥያቄ “ባዶ ንግግር” በሚል ስም ማጥላላት በራሱ የመሪዎችን ኃላፊነት የጎደለው አካሄድ የሚያሳይ መሆኑን ይገነዘባል።

የሕዝብን የልማትና የፍትህ ጥያቄ ማፈንና ማሸማቀቅ የትም አይደርስም፤ በክልሉ ያለው የልማት ክፍፍል ግልጽነትና ፍትሃዊነት እንዲኖረው WT Media ዘውትር ይሟገታል።
​
​Voice of Marginalized Community – WT Media