በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ጤና ቢሮ የእናቶችና ህፃናት ጤና ዳይሬክቶሬት፤ ለህፃናት እና እናቶች ጤና የተመደበ በጀት ለቅንጡ ስልኮች ግዥ መዋሉ በሰነዶች መረጋገጡ ከፍተኛ አነጋጋሪ ሆኗል።
የተገኙት የደብዳቤ እና የደረሰኝ ሰነዶች እንደሚያሳዩት፣ የበጀቱ የመጀመሪያ ዓላማ በምግብ እጥረት ለተጎዱ ህፃናትና እናቶች ድጋፍ ለማድረግ (ተሽከርካሪ ኪራይና ጥገና) እንዲሁም የህክምና መመሪያዎችን (AIMAM quick reference) ለማተም የታለመ ነበር።
ይሁን እንጂ ከዚህ የተያዘ በጀት ላይ በማዘዋወር ሁለት iPhone 17 Pro Max (12GB/512GB Silver) ስልኮች እንዲገዙ ተደርጓል።


በደብዳቤው ላይ እንደሰፈረው የአንዱ ስልክ ዋጋ 398,000 ብር ሲሆን ለሁለቱ ስልኮች በአጠቃላይ 796,000 ብር ወጪ ተደርጓል።
በተያያዘው የንብረት ግቢ ውጪ ደረሰኝ ላይ የሲም ካርድ፣ የካርድ አየር ሰዓት እና የዳታ አገልግሎትን ጨምሮ አጠቃላይ ወጪው በአንድ ስልክ እስከ 398,091.05 ብር መድረሱ ተመላክቷል።
በደብዳቤው የታዘዘው የስልክ ግዥ ሲሆን በደረሰኝ ላይ የሲም ካርድ እና የኤርታይም ወጪዎች መቀላቀላቸው የበጀቱ አጠቃቀም ሰፊ ምስቅልቅል ያለበት መሆኑን ያረጋግጣል።
በምግብ እጥረት ለተጎዱ እና ለታመሙ ወገኖች መድረስ ያለበት የህዝብ ገንዘብ ለአንድ ስልክ ወደ 398 ሺህ ብር በሚጠጋ ወጪ መወሰኑ የሞራልና የአስተዳደር ጥሰት መሆኑን አመላክቷል።
ስለሆነም የሚመለከታቸው አካላት፣ የሲቪክ ማህበራት እና የፀረ-ሙስና ተቋማት በጉዳዩ ላይ ግልፅ ምርመራ እንዲያደርጉበት ጥሪ ቀርቧል።
Voice of Marginalized Community – WT Media