የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 3ኛ ዓመት የምስረታ በዓል፡ ከግዙፍ የበጀት ብክነት፣ ከአደረጃጀት ምስቅልቅል እስከ ስር የሰደደ የመልካም አስተዳደር ቀውስ – የ WT Media ልዩ ዘገባ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት 3ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ሲያከብር፣ በክልሉ የሚስተዋለው የመዋቅር ምስቅልቅል፣ የአመራሩ ግድየለሽነት እና የሀብት አጠቃቀም ብክነት ክልሉን ሕግና ተጠያቂነት የሌለበት አስመስሎታል የሚሉ ጠንካራ ውንጀላዎችና ቅሬታዎች ተነስተዋል።
WT Media የተለያዩ ምሁራንና ተጨባጭ ማስረጃዎችን አሰባስቦ በሰራው በዚህ ልዩ ዘገባ ሕዝቡ መሠረታዊ አገልግሎት ፍለጋ ከአንዱ ክላስተር ከተማ ወደ ሌላኛው በእንግልት ሲንከራተት፣ አመራሩ ግን ይህንኑ መበታተን እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ለግል ዝርፊያ ማዕከል አድርጎታል ሲሉ የውስጥ ምንጮችና ተገልጋዮች ይወቅሳሉ።
1. ግዙፉ የበጀት ድልድል እና የክልል ማዕከል መዋቅር ውዝግብ
በክልሉ ለበጀት ዓመቱ የተመደበው አጠቃላይ የበጀት ድልድል ይፋ መሆኑን ተከትሎ፣ በክልሉ ማዕከል መዋቅር እና በዞኖች/ከተማ አስተዳደሮች መካከል ባለው የበጀት ቅንብር ላይ ከፍተኛ ውዝግብ ተፈጥሯል።
ለምሳሌ የክልሉ ፊናንስ ቢሮ ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያሳየው ከጠቅላላው የክልሉ በጀት ውስጥ ለክልል ማዕከል ብቻ 15,181,355,209 ቢሊዮን ብር ተመድቧል።

ትክክለኛው የልማት ሥራ እና የሕዝብ ጥያቄ ማረፊያ መሆን የሚገባው በቀበሌ፣ በወረዳ እና በዞን ደረጃ ቢሆንም፤ ለክልል መንግሥት መዋቅር ብቻ ይህን ያህል ግዙፍ በጀት መቆለሉ ለሕዝቡ የሚሰጠው ፋይዳ እጅግ አነስተኛ መሆኑን ምሁራን ይገልጻሉ።
በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት እውቅና ከተሰጣቸው እንደ ፍርድ ቤት፣ ፍትህ፣ ፖሊስና ፀጥታ፣ ኦዲተር እና ሕግ አውጪ ምክር ቤት ውጪ ያሉት የክልል ቢሮዎች ከመጠን በላይ መብዛታቸው ለሙስና እና ለሀብት ብክነት የተጋለጠ አወቃቀር ፈጥሯል።
2. ቢሮዎች በ6 ከተሞች መበታተን እና የቁጥጥር ክፍተት
የክልሉ ቢሮዎች በ6 የተለያዩ ከተሞች መበታተናቸው ለክትትልና ለተጠያቂነት ትልቅ እንቅፋት መፍጠሩ ተነግሯል። ሕዝቡ መሠረታዊ አገልግሎት ለማግኘት ከአንዱ ከተማ ወደ ሌላው ሲንከራተት የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ግን ለልማት የተመደበውን በጀት በተለያዩ ሰበቦችና ስብሰባዎች ስም በነዳጅና በአበል፣ በእቃ ግዢ፣ በመኪና ጥገና፣ በውሸት ጨረታዎች እና በግንባታ ሰበብ እየበዘበዙት ይገኛሉ። ክልሉ የሥራ ሳይሆን ከአንዱ ከተማ ወደ ሌላኛው የሽርሽር መድረክ ሆኗል።
3. የቢሮ ኪራይ ቅሌት እና የፋይናንስ ብክነት
አብዛኛው የቢሮ ኪራይ ለመንግሥት ተቋማት የሚከፈል ቢሆንም፤ ከሌሎች የክልሉ 5 ማዕከላት ለየት ባለ መልኩ በፕሬዚዳንቱ ትዕዛዝ በአርባምንጭ ከተማ ግን ግለሰቦች ሥልጣንን ተጠቅመው በቢሮ ኪራይ ሰበብ በሚሊዮኖች የሚቆጠር የመንግሥት ሀብት ለግል ጥቅም እያዋሉ መሆናቸው ተዘግቧል።
በተለያዩ የክልሉ መዋቅሮች ውስጥ የሚታየው የፋይናንስ ብክነት እና የፍትሕ መጓደል የከፋ ደረጃ ላይ ደርሷል።
4. የፖለቲካ ብልሽቶች፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና የአመራር ፀባይ
የክልሉ ምሁራን እና ከፍተኛ ባለሥልጣናት ለ WT Media እንደገለጹት፤ አደረጃጀቱ ለሕዝቦች የዘመናት የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣል ተብሎ ቢጠበቅም በ3 ዓመት ቆይታው ለህዝብ የዕዳ ከበድ ሆኗል።
ክልሉን አሁን በተደራጀው ቅርጽ እንዳይደራጅ በህቡዕ ሲሰሩ የነረሩ ኃይሎች ስልጣን በመያዛቸው፣ በመደመር ፋንታ በመከፋፈል፣ በጎራ በመቧደን እና በአግላይነት እሳቤ እየተሰራ ይገኛል።
በክልሉ ሕግና ሥርዓት ጠፍቶ በርዕሰ መስተዳድሩ ፍላጎት ብቻ እየተመራ ይገኛል። በክልሉ የጅምላ እስራት የተፈጸመ ሲሆን በፍርድ ቤት እንዲለቀቁ የተባሉትም ጭምር በፖሊስ ጣቢያዎች እንዲማቀቁ እየተደረገ ነው።
ከማዕድን፣ ከእርሻ መሬት፣ ከከተማ መሬት ምዝበራ ባለፈ የኮንትሮባንድ ንግድ በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽንና በከፍተኛ አመራሮች ቅንጅት ዋና የገቢ ምንጭ ሆኗል።
5. የፖለቲካ ቀውስ ስጋት እና የምሁራን ጥሪ
ደቡብ ኢትዮጵያ ለሥራ ምቹና ሰላማዊ ብትሆንም፣ ሀቀኛና ቆራጥ መሪ በማጣቷ ለዝርፊያ ተጋልጣለች። በዚህም ምክንያት በዘንድሮው ሀገራዊ ምርጫ የሕዝቡ ብሶት ወደ አማራጭ ኃይሎች እያዘነበለ መሆኑ ይታያል።
ገዢው ፓርቲ ከገጠመው ከፍተኛ የቅቡልነት መሸርሸር አንጻር፣ ክልሉ ያልተጠበቀ የፖለቲካ ውጤት ሊያስተናግድ ጫፍ ላይ ይገኛል።
ጉዳዩ ተባብሶ ወደ ከፋ ማኅበራዊ ቀውስ ከመቀየሩ በፊት የፌዴራል መንግሥት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ላይ አስቸኳይ የአሠራርና የአመራር ለውጥ እንዲያደርግ ምሁራንና ዜጎች በጽኑ ይጠይቃሉ።
የበጀት አጠቃቀሙ ከመሠረቱ ተገምግሞ ሀብቱ ወደ ታችኛው የመዋቅር ደረጃ (ለዞኖች፣ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች) እንዲወርድ ጥሪ ቀርቧል።
በመጨረሻም ለ WT Media አስተያየት የሰጡ ምሁራን፦ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት 3ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ሲያከብር በይፋ ከሚነገረው የልማት ትርክት ባሻገር መሬት ላይ ያለው እውነታ ግን ከዕድገትና ከሰላም ይልቅ የከፋ የመልካም አስተዳደር ቀውስ፣ የበጀት ብክነት እና የፍትሕ መጓደል የነገሰበት መሆኑን ለመረዳት ይቻላል።
ማዕከል-ተኮር የሆነው ግዙፉ የበጀት ድልድል፣ የቢሮዎች በ6 ከተሞች መበታተን ለአገልግሎት ሰጪው ሕዝብ እንግልት እንጂ ለልማት ፋይዳ አልሰጠም በሚለው ይስማማሉ።
በመሆኑም የፌዴራል መንግሥትም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት ጉዳዩ ከባባሶ ወደ ከፋ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ እንዳያመራ አስቸኳይ የአሠራርና የአመራር ማሻሻያ (Reform) በማድረግ የበጀቱን ፍሰት ወደ ታችኛው የመዋቅር ደረጃ (ለዞኖች፣ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች) ማውረድ እና የሕዝብን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል ይላሉ።
🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፥ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏
Voice of Marginalized Community – WT Media