በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን ጌዜ ጎፋ ወረዳ የደመወዝ ክፍያ መዘግየትን አስመልክቶ በመምህራን እና በመንግሥት ሠራተኞች የቀረበው አቤቱታ ወደ ከፍተኛ ማህበራዊ ቀውስ ማምራቱን ከስፍራው ለ WT Media የደረሰው መረጃ ያመለክታል።
ጉዳዩን አስመልክቶ ከመምህራን ተወካዮች የደረሱን ተጨማሪ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ችግሩ ከአስተዳደራዊ መዘግየት አልፎ የሠራተኞችን መብትና ሕልውና የሚፈታተን አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።
ከአራት ቀን በፊት ለ WT Media በደረሰው በመምህራን ተወካዮች በተፈረመ ማመልከቻ እንደተገለጸው፤ ሠራተኞቹ የሐምሌ ወር ደመወዛቸው በCBE Birr ሂሳባቸው እንዲገባ በወቅቱ ጥያቄ አቅርበው የነበረ ቢሆንም ለሌሎች ሠራተኞች በዋናው የባንክ ሂሳብ በኩል ሲከፈል የCBE Birr አማራጭ የመረጡት ሠራተኞች ደመወዝ እስካሁን ሳይለቀቅ ቀርቷል።



ሠራተኞቹ ከወረዳ እስከ ዞን ማዕከል ድረስ በአካል ተጉዘው ማብራሪያ ቢጠይቁም በቂ ምላሽ እንዳላገኙና ጉዳዩ ከሥራ ሰዓት ውጪ ከፍተኛ እንግልት እንደፈጠረባቸው አስታውቀዋል። (ማመልከቻውን የፈረሙ ነባር ሠራተኞች ዝርዝር በሰነዱ ላይ ሰፍሯል)።


ይህ በእንዲህ እንዳለ በዚሁ በጌዜ ጎፋ ወረዳ 68 ነባር መምህራን እና የመንግሥት ሠራተኞች ከደመወዝ መዝገብ (ፐሮል) ውጭ በመሆን በምትካቸው አዲስ ሠራተኞች ቅጥር መፈጸሙ ተረጋግጧል።


በዚህም ሳቢያ ደመወዝ ያጡ እና ለኑሮ ውድነት የተጋለጡ 68 ሠራተኞች ወደ ዞን ከተማ ሳውላ 17 ኪሎ ሜትር በእግር በመጓዝ ፍትህ እንዲሰጣቸው ጥያቄ ያቀረቡ ቢሆንም በወቅቱ በጸጥታ አካላት በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
በሌላ በኩል በጎፋ ዞን በሚገኙ 12ቱ መዋቅሮች ውስጥ ያሉ በርካታ የመንግሥት ሠራተኞች እስካሁን ደመወዝ ባለመከፈሉ ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸውን ገልጸዋል።
“ክራይ ቤት ነው የምኖረው፤ ነገር ግን የቤት ኪራይ ባለመክፈሌ ዛሬ ከሥራ ሲመለስ የባለቤቱ ቁልፍ ተደርቦ ቆልፎብኛል፤ ከፍተኛ ችግር ላይ ነኝ። ይህ የበርካቶች ተመሳሳይ ችግር ነው፤ ለከባድ ማህበራዊ ቀውስ ተዳርገናል” በማለት ድምፃቸው እንዲሰማላቸው ጠይቀዋል።
WT Media ጉዳዩን አስመልክቶ የሚመለከታቸውን የአስተዳደር አካላት ምላሽ ለማካተት ያደረገው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም። ሚዲያችን የሠራተኞቹን ሰብአዊና የኑሮ ውድቀት ሁኔታዎች እንዲሁም የሕግ ጥያቄዎች በቀጣይነት የሚከታተል ይሆናል!
🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏
Voice of Marginalized Community – WT Media
R