በኬንያ መንግሥት በትንንሽ ንግዶች ላይ የተጣለውን ዕገዳ ተከተሎ፣ ሰኞ ጳጉሜን 2 ቀን 2018 ዓ.ም. (ሴፕቴምበር 7) በናይሮቢ በሚገኙ የውጭ ሀገር ዜጎች እና የስደተኞች የንግድ ማዕከላት ውስጥ ከፍተኛ ፍርሃትና አለመረጋጋት ሰፍኖ ውሏል።
ይህ እርምጃ የተወሰደው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ የውጭ ሀገር ዜጎች በችርቻሮ እና በጎዳና ላይ ንግድ (ሀውኪንግ) ላይ እንዳይሰማሩ፣ እነዚህ የንግድ ዘርፎች ለኬንያ ዜጎች ብቻ የተከለሉ ናቸው በማለት ካስተላለፉት ትዕዛዝ በኋላ ነው። የመንግሥት ባለሥልጣናት ሕጋዊ የሥራ ፈቃድና የንግድ ፈቃድ ያላቸው የውጭ ዜጎች በሕግ የተጠበቁ ናቸው ቢሉም፣ በቦታው ላይ የተካሄደው የፖሊስ ቁጥጥር ግን በከተማዋ ፈጣን ምስቅልቅል ፈጥሯል።
የ WT Media ሪፖርተሮች ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን በብዛት በሚኖሩባቸውና በሚሠሩባቸው እንደ ያያ ሴንተር (Yaya Center)፣ ጃሙሁሪ (Jamhuri)፣ እስትሌይ (Eastleigh) እና ኪያማይኮ (Kiamaiko) ባሉ አካባቢዎች ባደረጉት ምልከታ፣ በርካታ አነስተኛ ንግዶች መዘጋታቸውን አረጋግጠዋል። ብዙዎቹ ስደተኞች ከእስራት፣ ከእንግልትና ከግዴታ ንግድ መዘጋት በመሰጋት ቤቶቻቸው ውስጥ ለመሸሸግ ተገደዋል።
በናይሮቢ የሚኖሩት ስደተኞች የታወቁ ስደተኞችን፣ ጥገኝነት ጠያቂዎችን፣ ፓስፖርት ያላቸውንና ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸውን ያካተቱ ናቸው። ለብዙዎቹ፣ መደበኛ የሥራ ፈቃድ ማውጣት በከፍተኛ ክፍያ ምክንያት ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ፣ ቤተሰቦቻቸውን ለማስተዳደር አነስተኛና ያልተደራጁ ንግዶች ብቸኛ የኢኮኖሚ ምንጫቸው ነበሩ።
በያያ ሴንተር አቅራቢያ አነስተኛ የምግብ ቤት ንግድ የሚያካሂዱ አንድ ኢትዮጵያዊ ለ WT Media ሲናገሩ “ምን እንደሚፈጠር ስላላወቅን ዛሬ ለመክፈት ፈርተናል። ውሳኔው ግልጽ አይደለም፣ ድንገት የመጣ ነው፤ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ነን” ብለዋል።
በናይሮቢ የሚኖሩ አንድ ኤርትራዊ ባለሱቅ በበኩላቸው፣ አነስተኛ ንግድ ከሃገራቸው የሸሹበትን አደጋ ተቋቁመው ለመኖር ብቸኛ አማራጭ እንደሆነ ገልጸዋል።
“አብዛኞቻችን ወደዚህ የመጣነው በትውልድ ሀገራችን ባለው ስደት፣ ጦርነትና የፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት ነው” ሲሉ ሱቃቸውን ከዘጋጉ በኋላ ለ WT Media ተናግረዋል። “እዚህ ናይሮቢ ውስጥ አነስተኛ ንግድ የምንሠራው በሕይወት ለመቆየትና መሠረታዊ ፍላጎታችንን ለማሟላት እንጂ ከማንም ጋር ለመወዳደር አይደለም። አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶችን ማሟላት ከፍተኛ ገንዘብ ስለሚጠይቅ አብዛኞቹ ስደተኞች የሥራ ፈቃድ የላቸውም።” አክለውም የኬንያ መንግሥት ውሳኔውን እንዲያልፍበት ጠይቀዋል።
የሕግ ባለሙያዎችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ሁሉንም የውጭ ዜጎች በአንድ “የውጭ ሀገር ዜጋ” በሚል መደብ ሥር አጠቃሎ ማገድ፣ በተለይም በስደተኞች መብት በኩል ከፍተኛ የሕግና የኢኮኖሚ ጫና እንደሚፈጥር ያሳስባሉ። የሕግ ተንታኙ ደራሶ ኮሌ (Deraso Dokhole) በ The Standard ጋዜጣ ላይ ባስፈሩት ጽሑፍ፣ በ 2021 የወጣው የኬንያ የስደተኞች ሕግ (Refugees Act, 2021) የታወቁ ስደተኞች በንግድና በሥራ የመሰማራት ሕጋዊ መብት እንዳላቸው ጠቁመዋል።
ከዚህም በተጨማሪ፣ ይህ እርምጃ ኬንያራሷ ካወጣችው የሺሪካ ዕቅድ (Shirika Plan) ጋር ይጋጫል። የመንግሥት የስደተኞች አገልግሎት መሥሪያ ቤት ዕቅዱን ስደተኞችን ከእርዳታ ጠባቂነት ወደ ራሳቸው ወደሚችሉበት የኢኮኖሚ ተሳታፊነት ለማሸጋገር ያለመ እንደሆነ ይገልጸዋል።
ተሟጋቾች እንደሚሉት፣ ኬንያ የሀገር ውስጥ የንግድ ዘርፏን የመጠበቅ መብት ቢኖራትም፣ መሬት ላይ ባለው ቁጥጥር ወቅት በሕግ ጥሰት ላይ ባሉ የውጭ ዜጎችና ሕጋዊ የስደተኝነት መብት ባላቸው መካከል ልዩነት ካልተደረገ፣ ስደተኞች የጉዳቱ ሰለባ ይሆናሉ።
በከተሞች ያለው ቁጥጥር እየጠነከረ ሲሄድ፣ የስደተኞች መብት ተሟጋች ድርጅቶች የመንግሥት አካላት የጥገኝነት ጠያቂዎችንና የስደተኞችን ሕጋዊ ሁናቴ የሚገልጽ ግልጽ መመሪያ እንዲያወጡና ያለ አግባብ የሚደረግ ጥቃትን እንዲያስቀሩ በመጠየቅ ላይ ናቸው።