1000142699

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌዴኦ ዞን ​በዲላ ከተማ ጪጩ ቀበሌ ክልል ውስጥ በሚገኘው የጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያ አካባቢ በፌዴራል ፖሊስ አባላት በፈጸመ ሕገወጥ የተኩስ እርምጃ የ3 ወር አዲስ ሙሽራ የሆነው ወጣት አቢቲ ብርሃኑ በግፍ መገደሉን ለ WT Media የደረሰው መረጃ ያመለክታል።

​እንደ መረጃው ከሆነ ከሞያሌ ወደ ዲላ ከተማ መግቢያ በር ላይ ከሚገኙ ዋና ዋና ኬላዎች አንዱ በሆነው የጪጩ ጉምሩክ ኬላ ትናንት 04/13/2018 ዓ.ም ምሽት ላይ ተረኛ የነበረ አንድ የፌዴራል ፖሊስ አባል “ውስጥ ለውስጥ ኮንትሮባንድ እቃ ጭኖ የሚሄድ ሞተረኛ አለ” የሚል ጥቆማ ይቀበላል።

ሆኖም ፖሊሱ ሞተረኛውን ተከታትሎ ከመያዝ ይልቅ የናኘውን ተኩስ በመክፈቱ፣ ኮንትሮባንድ የያዘውን አካል ሳይሆን በሌላ ሞተር ተሳፍሮ ከስራው ወደ ቤቱ በመመለስ ላይ የነበረውን ከጉዳዩ ጋር ፍጹም ንጹህ የሆነውን ወጣት አቢቲ ብርሃኑን ሕይወት በቀጥታ በጥይት ቀጥፎታል።

ይህ ከጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያ ውጭ በሆነ ቦታ እና በሃላፊነት በጎደለው መልኩ የተፈጸመው አስደንጋጭ ግድያ የአካባቢውን ማህበረሰብ ከፍተኛ ቁጣ ቀስቅሷል። በግፍ በተገደለው ወጣት ወገኖችና በፌዴራል ፖሊስ መካከል ከፍተኛ ግብግብ የተፈጠረ ሲሆን በቁጣ የተነሳው ማህበረሰብ የጪጩን የፌዴራል ኬላ በእሳት አቀጣጥሎ አቃጥሎታል።

ከአካባቢው ነዋሪዎችና ከተለያዩ ምንጮች በ WT Media የተጠናቀረ መረጃ እንደሚያሳየው የዲላ ከተማ እና የዞን ፖሊስ አካላት ከወንጀለኛው የፌዴራል ፖሊስ ጋር በመቀናጀት ተጠያቂነትን ለማስቀረት እና ህገወጥ ድርጊቶችን ለመሸፈን እየሞከሩ ይገኛሉ።

ኬላውን በአግባቡ ከመጠበቅ ባለፈ በከተማው ዋና ገበያ (ታይዋን) ውስጥ ገብተው ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ንጹህ ነጋዴዎችን የሚያስጨንቁ፣ ዜጎችን ያለአግባብ የሚያስሩ እና በግለሰቦች ደረጃ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በመሰብሰብ ላይ የሚገኙ አካላት አሁን ደግሞ የዋሁን ወጣት ህይወት ቀጥፈው በመሰወር ላይ እንዳሉ የደረሰን መረጃ ያረጋግጣል።

የጌዴኦ ዞን ፖሊስ መምሪያ ህዝብ ግንኙነት በበኩሉ፤ አቶ አቢቲ ብርሃኑ በድንገተኛ አደጋ ህይወቱን ማጣቱን ገልጾ፣ በወቅቱ ሊፈጠር የነበረውን አለመረጋጋት ከሰላም ወዳዱ ማህበረሰብና ከክልሉ አድማ ብተና ጋር በመሆን ወደ ከፋ ደረጃ ሳይደርስ መረጋጋቱን አስታውቋል።

ፖሊስ ጉዳዩን በህግ አግባብ እየመረመረ መሆኑን ገልጾ ማህበረሰቡ እንዲረጋጋና ከማንኛውም ያልተፈለገ እንቅስቃሴ ራሱን አርቆ ከህግ ጋር እንዲተባበር ጥሪ አቅርቧል።
​
የአካባቢው ማህበረሰብ እና የወጣቱ ቤተሰቦች በሰጡት አስተያየት፣ ወንጀለኛው የፌዴራል ፖሊስ አባል በአፋጣኝ ለህግ ቀርቦ ተገቢውን ቅጣት ካላገኘ ማህበረሰቡ ፍትህን በራሱ እጅ ለመውሰድና በጉምሩክ ጣቢያው ላይ የሚገኙ አካላትን እስከ መደምሰስ የሚደርስ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድ በግልጽ አስጠንቅቋል።

ህብረተሰቡ ​የግድያውን እውነታ ለመሸፈን የሚደረግ ማንኛውም ጸረ-ህዝብ ዝውውር እና ቸልተኝነት በአፋጣኝ ሊቆም ይገባል እያለ ሲሆን WT Media የጉዳዩን ሂደት በቅርበት እየተከታተለ ለህዝብ ይፋ የሚያደርግ ይሆናል።

🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏

Voice of Marginalized Community – WT Media