በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በኧሌ ዞን፣ በደቡብ ኦሞ ዞን (በና ፀማይ) እና በኮልሜ ወረዳ (ኮንሶ ዞን) አዋሳኝ አካባቢዎች ከጳጉሜ 5 ጀምሮ በተከፈተው የታጠቁ አካላት እርስበርስ ጥቃት በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ከስፍራው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ግጭቱ የፈነዳው 21 የሚሆኑ የበና ፀማይ ከብቶች በባለታወቁ ሰዎች መወሰዳቸውን ተከትሎ ‹‹ዘራፊዎቹ ወደ ኮልሜ አቅጣጫ ተጓዙ›› የሚል ሃሰተኛ መረጃ በመሰራጨቱ ነው። ማንነታቸውና ከብቱ በግልጽ የት እንደተወሰደ ሳይረጋገጥ ከኧሌና ከደቡብ ኦሞ ዞን አስቀድመው ለጥቃት የተዘጋጁ ታጣቂዎች በተቀናጀ ሁኔታ ጥቃት ከፍተዋል።
ትናንት ትማያ የተባለውን የኮልሜ ቀበሌ ለማቃጠል ተቃርበው ሳይሳካ ሲቀር እና የክልሉ አድማ ብተና ወደ አካባቢው ገብቶ ነበር።
ይሁን እንጂ ዛሬ ማሶያ እና ኩርቦ ቀበሌዎችን በማቃጠል ውለዋል፤ በዚህም ኩርቦ ቀበሌ ሙሉ በሙሉ መውደሙ ተገልጿል። በግጭቱ ህፃናትንና አረጋውያንን ጨምሮ ከ7 በላይ ሰዎች ተገድለዋል፤ ቤታቸው ተቃጥሏል፣ ንብረት ወድሟል፤ ከብቶች ተዘርፈዋል።



ለ WT Media ስሙ እንዳይጠቀስ ያነጋገሩት አንድ የአካባቢው የሀገር ሽማግሌ እንዳገለጹት ትናንት ከምሽቱ 5፡00 ሰዓት ላይ በኩርቦ ሊፈጸም ከነበረው ጥቃት ጋር ተያይዞ የክልሉ አድማ ብተና ኃይል ባልታወቀ ምክንያት ትናንት ከሌሊቱ 9፡00 ሰዓት ላይ ከኮልሜ እንዲወጣና ወደ ሆልቴ እንዲመለስ ተደርጓል።
እንዲሁም በኮልሜ የነበረው የፌዴራል ፖሊስም ከወረዳው እንዲወጣ መደረጉን ጠቁመዋል። በዚህም ምክንያት የኮልሜ ሕዝብ ከሁለት ዞኖች ለተከፈተበት ጥቃት በቂ የጸጥታ ድጋፍ ሳያገኝ ቀርቷል።


ሌላው የአካባቢው ነዋሪ በበኩሉ የኮንሶና ኧሌ ዞን አመራሮችና ሽማግሌዎች ከጥቂት አድማ ብተናዎች ጋር በመሆን ጥቃቱን ለማስቆም አቅደው የነበረ ቢሆንም ከኧሌ አመራሮች በኩል ወደ ኩርቦ ለመሄድ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ዕቅዱ እንዳልተሳካ አስረድቷል።
በቅርቡ በሰገን ዙሪያ ወረዳ በርካታ ቀበሌዎችና የወረዳው ማዕከል አመድ ሆኖ እስከዛሬም ሙሉ በሙሉ ባለመመለሱ፣ አሁን የኮልሜ ወረዳ ማዕከል በሆነችው ደልበና ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄና ፈጣን የመንግሥት እርምጃ እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል። በአሁኑ ሰዓትም በሳይሶሌ በኩል ከፍተኛ ተኩስ መከፈቱን ነዋሪዎች ለ WT Media ገልጸዋል።
WT Media ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ተጨማሪ መረጃ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ለማግኘት ያደረገው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም። ሚዲያችን የጉዳዩን ሂደት በቅርበት እየተከታተለ ለህዝብ ይፋ የሚያደርግ ይሆናል።
🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏
Voice of Marginalized Community – WT Media