ከ130 ዓመታት በኋላ እውን የሆነው ታሪካዊው የኬንያው የዎላይታ ማህበረሰብና የቤተሰብ መገናኘት ተግባር ለራሱ የተሰደደው ጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ እንዴት ለማሳካት ቻለ?
በደልና ስደት ከ130 ዓመታት በፊት የጀመረው የዎላይታ ህዝብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቁስል ዛሬም ፍቱን መፍትሄ አላገኘም፤ በኬንያ የሚገኙ ወገኖችና የቤተሰብ መገናኘት ግን አዲስ ተስፋ ፈጥሯል።
ከ130 ዓመታት በፊት በ1880ዎቹ አቆጣጠር በዎላይታ ሀገር መሪ ንጉስ/ካዎ ጦና እና በወቅቱ አቢሲኒያ የአሁኑ ኢትዮጵያ መሪ የነበሩት አጼ ምኒልክ መካከል በተደረገው ከፍተኛና ደም አፋሳሽ ጦርነት ማጠቃለያ አከባቢ በአቢሲኒያዊያን አገዛዝ ላለመገዛት ከዎላይታ ተሰደው ወደ ኬንያ በመሄድ በስደት የሚገኙት ታሪክ የትውልድ ጥልቅ ማህበራዊ ቁስል ሆኖ ቆይቷል።
በወቅቱ ከፍ ያለ የጦር መሪ የነበሩ ቤተሰቦችን ጨምሮ በርካታ ዜጎች ወደ ኬንያ የተሰደዱ ሲሆን በወቅቱ በተደረገ የመስክ ምልከታና ጥናት እንደተረጋገጠው በኬንያ ከ130 ዓመት በፊት መጥተው የሚኖሩት እነዚህ ወገኖች ቁጥራቸው ከአስር ሺዎች በላይ ይደርሳል።
መጀመሪያ በዋናነት መኖር የጀመሩበት ኢሲዮሎ ከተማ ከኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ 280 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን አሁን ግን በኬንያ በተለያዩ ቦታዎች ተበታትነው ዜግነት አግኝተው በተለያዩ የንግድና በመንግሥት ከፍተኛ ተቋማት ጭምር እያገለገሉ ይገኛሉ።
ትውልዳቸው እስከ አራተኛ ትውልድ ተባዝቷል፤ ነገር ግን እስካሁን ዜግነታቸው በወረቀት ቢቀየርም ሀገራቸው ዎላይታ እንደሆነ በጽኑ ያምናሉ። የጊዜ ርዝመት ስለማንነታቸው ያለውን ጥልቅ ፍለጋና ፍቅር ሊያጠፋው አልቻለም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከዕለታት አንድ ቀን ትውልዳቸው ከዚህ ከከበረ ታሪክ ጋር ከተያያዙት መካከል አንዷ የሆነችው ፋቱማ ከኬንያ (እሲዮሎ) ወደ ዎላይታ በማቅናት ከረጅም ዘመናት መለያየት በኋላ በዚህ ስምንት (September 13/2026) እውነተኛ ቤተሰቦቿን በዎላይታ ደልቦ አካባቢ ማግኘት ችላለች።



ይህ ድል ከ130 ዓመታት በላይ ማንነታቸውንና ቤተሰባቸውን ሲፈልጉ ለነበሩት ትልቅ ታሪካዊ ብስራትና የጽናት ማሳያ ነው። ከዚህ በኋላ እዚያ የሚኖሩ ሌሎችም ወደ ቤተሰቦቻቸው በቀላሉ ሄደው ለመጎብኘትና ለመጠያየቅ መንገዱ የተከፈተ ሲሆን ለዓመታት የናፈቁት የማንነት ጥያቄም ትልቅ ምላሽ አግኝቷል።
የ WT Media መስራችና ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ Natnael Gecho ከሶስት ዓመት በፊት በሀገሩ በሚዲያ ስራው ምክንያት በደረሰበት እስራትና ጥቃት ወደ ኬንያ በተሰደደበት ወቅት የዚህን ወገኖቻችንን ታሪክ ከዎላይታ ኮሚኒቲ ሰምቶ፣ በተለያዩ ምክንያት መጥተው በናይሮቢ ከሚኖሩ ከዎላይታ ኮሚኒቲ በማስተባበር ከናይሮቢ እስከ 280 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ወደምትገኘው ኢሲዮሎ(Isiolo) በመጓዝ እነዚህን ወገኖችን በመጀመሪያው መኖሪያ አካባቢያቸው ላይ አግኝቷቸዋል።


በጉብኝት ወቅቱ ማለትም ከ3 ዓመት በፊት “ከአፄ ሚኒሊክ ወረራ ያመለጡ ዎላይታዎች ህያው ታሪክ” በሚል ርዕስ የተሰራውን የሚዲያ ስራ ማየት ይቻላል።
ከዚያ የሶስት ዓመት ትውውቅ ወዲህ በደስታም ሆነ በሀዘን ጠንካራ ማህበራዊ ትስስር በመፍጠር የቆዩ ሲሆን አሁን ደግሞ እነሆ ትክክለኛ ቤተሰቦቻቸውን አግኝተው ታሪካዊ ህልማቸው እውን ሆኗል።

ጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ በዚህ ታሪካዊ ክስተት አስመልክተው በግል ይፋዊ ፌስቡክ ገፅ “ይህ ጉዳይ ቀላል የሚመስል ማህበራዊ ክስተት ብቻ አይደለም። ይህ ታሪክ በወቅቱ በዎላይታ ህዝብ ላይ የደረሰው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ የጀመረበት አንዱ ቁልፍ መነሻ ነው። «ስንቶቹ በጦርነቱ ምክንያት በወቅቱ ወደተለያዩ ሀገራት ተሰደው እየኖሩ ይሁን?» የሚለው ለሁላችንም ትልቅ የቤት ስራ ነው” ብሏል።
አክሎም “ያኔ የተበተነው ህዝባችን ዛሬም ሙሉ በሙሉ አልተሰበሰበም፤ ያኔ የወደመው ሀብታችንና ንብረታችን ለካሳ ተብሎ አንዳችም ስር ነቀል ትኩረት አልተሰጠውም። ትውልዱ ይህንን አውቆ ለቀጣይ መፍትሔ መዘጋጀት አለበት። የዎላይታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቁስልና እየገጠሙ ያሉት ውስብስብ ችግሮች ከዚህ የሚነሱ ናቸው” በማለት የሁኔታውን ጥልቀት አስረድተዋል።
“ዛሬ በዎላይታ ውስጥ ከ300 ሺህ በላይ የተማሩ ስራ አጦች ያለምንም የስራ እድል መሰቃየት፣ ህፃናት መማር ሲገባቸው በሀገሪቱ በሁሉም ጎዳናዎች ተበትነው ለተለያዩ አላስፈላጊ ብዝበዛና ግፊቶች ተጋልጦ መገኘታቸው የዚሁ ጥልቁ ታሪካዊ በደል ነጸብራቅ ነው። ይህ ትውልዳዊና ስር የሰደደ ችግር የዛሬው ትውልድ ብቻ ሳይሆን የ130 ዓመታት ታሪካዊ ሸክም ውጤት ነው።
ስለዚህም አሁን ያለው መንግስትም ሆነ የዎላይታ ምሁራኖችና የህብረተሰብ ክፍሎች ይህንን እውነት በመገንዘብ ችግሩን በላዩ ላይ ከሚታየው የፖለቲካ ገጽታ ባሻገር በመሰረታዊነት ማየት ይኖርባቸዋል። በአስተዳደርና በታሪክ ሰለባነት የተበተኑትን ወገኖች አንድ ለማድረግ ጥልቅ ጥናት፣ ታላቅ ቁርጠኝነት (Commitment) እና የጋራ ንቃት ይጠይቃልም” ብሏል።
ይህ ታሪካዊ ህልማቸው እንዲሳካና እንዲገናኙ ላደረጉት በኬንያ የሚገኘው የዎላይታ ኮሚኒቲ፣ የዎላይታ ልማት ማህበር አመራሮች እንዲሁም ለተባበራችሁት ሁላችሁም ምስጋና ይገባል” ሲልም ጋዜጠኛ ናትናኤል ገልጿል።
“ከዚህ ባሻገር በመላው ዓለም የተበተኑ ወገኖቻችን የመሰብሰብ፣ የማቀራረብና ማንነታቸው እንዲያውቁ የማድረግ ትልቅ ኃላፊነት በእኛ ላይ መውደቁን WT Media ያምናልና፤ የትላንቱ ጠባሳ እንዲጠገን እና የተበተነው ህዝባችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍትህ እንዲያገኝ የሁለቱም ጎን (የመንግስት፣ የምሁራን እና የህዝቡ) የጋራ ርብርብ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል” የሚለውን ጥሪ በመጨረሻው አስተላልፏል።