የዎላይታ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል ጊፋታ የዓለም የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ በዩኔስኮ (UNESCO) ከተመዘገበ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሦስት ቀናት በኋላ በታላቅ ደስታና ድምቀት ይከበራል።
ጊፋታ በቀን መቁጠሪያ ላይ የሚቀየር የቀናት ቁጥር ብቻ ሳይሆን የዎላይታ ሕዝብ ጥልቅ ማኅበራዊ፣ ሥነ-ልቦናዊና ሞራላዊ እሴቶች የሚንጸባረቁበት፣ የታሪክና የማንነት መገለጫ የሆነ ትልቅ የሕይወት መድረክ ነው።

ከሁለት ወራት ቅድመ ዝግጅት በኋላ ከመስከረም አጋማሽ እስከ ጥቅምት መጀመሪያ ባለው ጊዜ ውስጥ የሚከበረው ይህ በዓል፣ ዘንድሮ የተቀናጀ ዓለም አቀፍ ትኩረትና ልዩ ባህላዊ አክብሮት ታክሎበት ይከናወናል።
በዓሉ ከመድረሱ በፊት ባሉት ቀናት በዎላይታ ቀዬዎች የሚታየው የዝግጅት እንቅስቃሴ ራሱን የቻለ የበዓል አካል ነው። እናቶችና እህቶች ባህላዊ ምግቦችንና መጠጦችን ለማሰናዳት ሽርጉድ ይላሉ።
ባህላዊ ምግቦች እንደ ሙቾ፣ ቆጮ፣ ቂጣ፣ ባጭራ እና ጠረኑ የሚስብ የምግብ ማጣፈጫ የሆነው ዳታ ይዘጋጃሉ። ባህላዊ መጠጥችን ደግሞ እነዚህን ምግቦች ለማወራረድና እንግዶችን ለማስተናገድ ‘ቦርዴ’ የተሰኘው ባህላዊ መጠጥ በየቤቱ ይጣላል።


ለፍትሐዊ አብሮነት ደግሞ ማኅበረሰቡ ለበዓሉ የሚታረዱትን ከብቶች በጋራ በመግዛት (ቅርጫ)፣ የሥጋ ማከፋፈሉን ሥራ በወንዶች በኩል በፍትሐዊነት ያከናውናል፤ ይህም ቤተሰብና ጎረቤት በአንድ ማዕድ ተሰባስበው እንዲቋደሱ ያደርጋል።
ጊፋታ በዘመናዊው ዓለም እየጠፋ የመጣውን የጠበቀ ጉርብትና እና አብሮነት በተግባር የሚያሳስብ ነው። ኑሮን ለማሸነፍ ከትውልድ ቀዬአቸው የራቁ ወጣቶች በአካል ተገኝተው እናትና አባታቸውን የሚያቅፉበት፣ እህትና ወንድሞቻቸውን የሚሳሙበትና የልጅነት አብሮ አደጎቻቸውን የሚያገኙበት የልብ ትርታ ነው።

በሥራና በኃላፊነት ምክንያት በአካል መገኘት ያልቻሉት ወጣቶች እንኳ ካላቸው ላይ ቀንሰው ለቤተሰቦቻቸው በመላክ የበዓሉ ደስታ ሙሉ እንዲሆን ያደርጋሉ።
በተጨማሪም ጊፋታ የዕርቅና የሰላም ማግስ ነው። በዎላይታ ባህል ማንም ሰው በልቡ ቂም ይዞ ወይም ወንድሙን አስቀይሞ በዓሉን አያከብርም። አዲሱ ዓመት ሲጠባ፡- የተጣላ ይታረቃል፤ የተቀያየመ ይቅርታ ይደራረጋል።
ቂምና በቀል በአሮጌው ዓመት ተጥሎ አዲሱ ዘመን በንጹሕ ልብ ይቀበላል። የአካባቢው አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች አዲሱን ትውልድ በሰላምና በመልካም ምግባር እንዲያልፍ ይመክራሉ፣ ይመርቃሉም።
የበዓሉ ትልቁ ማሳረጊያና ድምቀት የ’ጉልያ’ (የችቦ) ማብራት ሥርዓት ነው። ችቦው ሲበራ ማኅበረሰቡ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከሐዘን ወደ ደስታ፣ ከክረምት ጭቃ ወደ በጋው ፀዳል መሸጋገሩን ያበስራል።
በዚህ የብርሃን ጅማሮ ወቅት “ሃያያ ለኬ” የተሰኘው ባህላዊ ዘፈን በወጣቶችና በጎልማሶች ይንቆረቆራል።

ወጣቶች በየቤቱ እየዞሩ በመልካም ምኞት ዘፈን ሁሉም በአንድ ድምፅ፦ ”ሃሹ ላይታፔ ላይታ ሰሯን ጋቲስ!” (ከዓመት ወደ ዓመት እንኳን በሰላም አሸጋገረን) እያሉ ሀገርንና ሕዝብን በሰላም ላቆየው ፈጣሪ ምስጋናቸውን ያቀርባሉ።
በታኅሣሥ 2025 ዓ.ም. በዩኔስኮ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች መዝገብ ላይ የሰፈረው ጊፋታ የኢትዮጵያ ሰባተኛው የዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ መመዝገቡ ይታወቃል።
እንደ የአከባቢው ምሁራን ገለፃ ይህ ዕውቅና ቅርሱ ዓለም አቀፍ ጥበቃ እንዲያገኝ ከማድረጉም በላይ በዎላይታ ዞን የሚገኙ እንደ ሞቼና ቦራጎ ዋሻ፣ የአሩጂያ ዋሻዎችና የዳሞታ ተራራ ያሉ ተፈጥሯዊና እንዲሁም ሌሎችንም ታሪካዊ ሀብቶችን ለባህላዊ ቱሪዝም (Eco-cultural Tourism) ያላቸውን እምቅ አቅም ያጎላል።
እንዲሁም ዛሬ ጊፋታ የዎላይታ ብሔር ፍቅርን፣ ሰላምን፣ መተሳሰብንና ኩራቱን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና ለተከታዩ ትውልድ የሚያስተላልፍበት ትልቅ የኢትዮጵያዊነትና የዓለም ሀብት ሆኗል።