1000148566

የሰላም አማራጭ ወይስ የጥፋት አዙሪት? የብርጋዴር ጀኔራል ደሳለኝ ዳቼ ጥልቅ ትንታኔ እና ከሰራዊት ዕረፍት እስከ ፖለቲካ ትግል ያደረጉት የህይወት ጉዞ – የ WT Media ልዩ ዘገባ

​በኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ እና የጸጥታ ምህዳር ውስጥ እየተስተዋሉ ያሉ ተግዳሮቶች አሳሳቢ ምዕራፍ ላይ ደርሰዋል።

በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ኃይሎች እና ተቃዋሚ አካላት መንግሥትን በኃይል ገልብጦ ሁሉ አቀፍ የሽግግር መንግሥት ለማቋቋም የሚያደርጉት ጥረት ከባድ አደጋን እያስከተለ መሆኑ ተገለጸ።

​በሠራዊቱ ውስጥ ረጅም ዓመታት አገልግለው በጡረታ የተሰናበቱት እና በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ትንታኔዎችን የሚያቀርቡት ብርጋዴር ጀኔራል ደሳለኝ ዳቼ ኡልቴ፤ አሁን ላይ በሰሜን ኢትዮጵያ እና በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የተከሰቱትን ጦርነቶች እና የፖለቲካ ውጥረቶች አስመልክተው ሰፊ ሃሳብ አጋርተዋል።

WT Media ያገኘው ይህ መረጃ፣ የሀገሪቱን ወቅታዊ የፖለቲካ አቅጣጫዎች እና የጀነራሉን የህይወት ምዕራፍ በዝርዝር ይቃኛል።

​ብርጋዴር ጀኔራል ደሳለኝ ዳቼ እንደገለጹት፤ በሀገሪቱ የሚታዩ የታጠቁ ግጭቶች መዋቅራዊ ስጋታቸው ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ መጥቷል። የታጠቁ አካላት “መንግሥት ሕጋዊነቱን አጥቷል፤ በመሆኑም በኃይል ተወግዶ ሁሉ አቀፍ የሽግግር መንግሥት መቋቋም አለበት” የሚለው አካሄድ በውስጡ እጅግ አደገኛ ስትራቴጂያዊ ስጋቶችን አዝሏል።

​አንድ መንግሥት በኃይል ሲወድቅ ሕገ-መንግስታዊ መዋቅሩ እና የደህንነት ተቋማት አብረው እንደሚፈርሱ ያነሱት ጀነራሉ፤ እንደ ሊቢያ፣ ሶማሊያ እና አፍጋኒስታን ሁሉ የታጠቁ ኃይሎች የጋራ ራዕይ ከሌላቸው ሀገሪቱ ወደባሰ የርስበርስ ፍጅት እና የጦር አበጋዞች (Warlords) ግዛትነት የምትቀየርበት አጋጣሚ ሰፊ መሆኑን አስገንዝበዋል።

​የችግሩ ዋና መዋቅራዊ መንስኤዎች በተመለከተ ብርጋዲየር ጀነራሉ “የመከላከያና የደህንነት ተቋማት የሀገር እና የሕግ የበላይነት ማስከበሪያ ከመሆን ይልቅ የገዥው ፓርቲ ማጠናከሪያ መዋቅር የመሆን አዝማሚያ ማሳየታቸው በሰራዊቱ እና ህዝቡ መካከል እምነት እንዲሸርሸር አድርጓል” ይላሉ።

​አክለውም “በምዕራብ ዓለም የሚኖሩ ጽንፈኛ የዲያስፖራ አካላት እና አክቲቪስቶች በሶሻል ሚዲያ በሚያደርጉት የጥላቻ ቅስቀሳ ወጣቱን ለጦርነት ማገዶ ሲያደርጉት፣ የውጭ ኃይሎችም ሀገሪቱን የፕሮክሲ ጦርነት አውድማ ለማድረግ እየሰሩ ይገኛሉ” ሲሉ ጀነራሉ ያብራራሉ።

​ጀነራሉ አያይዘውም፤ ማንኛውም ወገን “ግጭቱን በወታደራዊ የበላይነት ብቻ እቋጫለሁ” ወይም “በኃይል ገልብጬ የሽግግር መንግሥት እመሠርታለሁ” ብሎ የሚያደርገው ጥረት ፍፁም የተሳሳተ መሆኑን ጠቁመዋል። ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጠው በወታደራዊ ስብራት ሳይሆን በሁሉም አካላት አሳታፊነት በሚደረግ ፖለቲካዊ ድርድር እና ሀገራዊ መግባባት ብቻ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

​ብርጋዴር ጀኔራል ደሳለኝ ዳቼ ኡልቴ ድፍን ሰላሳ ስድስት ዓመታት በውትድርና መስክ ሀገራቸውን አገልግለዋል። ከተራ ወታደርነት ጀምሮ እስከ ጀነራል መኮንንነት ማዕረግ የደረሱ ሲሆን፤ በስራ ላይ እያሉም ትምህርታቸውን በመከታተል ባለ ሶስት ዲፕሎማ፣ አንድ ባችለር ዲግሪ እና ሁለት ማስተርስ ዲግሪዎች (በሴኪዩሪቲ እና አንትሮፖሎጂ) ባለቤት መሆን ችለዋል።

በተጨማሪም በሰራዊቱ ውስጥ እያሉ እንደ ጋዜጠኛ፣ አስተማሪ፣ አሰልጣኝ፣ የዲፕሎማት፣ የታጋይ፣ የህዝብ አስተዳዳሪ እና ተመራማሪ በመሆን ሁለገብ አበርክቶ አበርክተዋል።

​ሰላሳ ስድስት ዓመታት የውትድርና አገልግሎታቸውን አጠናቀው የወጡበትን አስመልክተው ሰኔ 2 ቀን 2017 ዓ.ም. በፌስቡክ ገጻቸው ባስተላለፉት የስንብት መልዕክት፤ “ወታደር ሲያረጅ አቃቤ ይሆናል” በማለት ከውትድርና ቢሰናበቱም ባለብዙ ሙያ እና ልምድ ባለቤት በመሆናቸው እጃቸውን አጣጥፈው እንደማይቀመጡ እና በቀጣይ በሲቪል ሕይወት ለራሳቸውና ለሀገራቸው በሚጠቅም መስክ እንደሚሳተፉ ገልጸው እንደነበር WT Media ተመልክቷል።

​ከሰራዊት ጡረታ ከወጡ በኋላ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በንቃት መሳተፍቀቸውን የቀጠሉት ብርጋዴር ጀኔራል ደሳለኝ ዳቼ፤ ዘንድሮ በተካሄደው 7ኛ ሀገር አቀፍ ምርጫ ላይ አንድ ተፎካካሪ ፓርቲን ወክለው በተወለዱበት አከባቢ በደቡብ ኢትዮጵያ በዎላይታ ዞን ሁምቦ ጠበላ ምርጫ ክልል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እጩ በመሆን ለውድድር ቀርበው ነበር።

​አሁን ላይ ከሰራዊት ዕረፍታቸው ጎን ለጎን የራሳቸውን የግል የደህንነት ተቋም በመገንባት በሙያቸው ማገልገላቸውን መቀጠላቸውን WT Media ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሰላም እና የህዝብ ደህንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ ከፖለቲካ ትግል ባለፈ ሙያዊ አስተዋጽኦአቸውን ማበርከታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።

​Voice of Marginalized Community – WT Media