በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን እና በገረሴ ወረዳ ባለሥልጣናት አከራካሪ ውሳኔ ሳቢያ በአካባቢው አርሶ አደሮች እና በጸጥታ ኃይሎች መካከል ከትናንት ጀምሮ በተከሰተው ግጭት ከፍተኛ ደም መፋሰስ ያስከተለ ግጭት መቀስቀሱን የ WT Media ምንጮች ተናግረዋል።
አርሶ አደሩ ለዘመናት አርሶ ሲጠቀምበት የነበረውን መሬት የዞኑ እና የወረዳው አመራሮች በኢንቨስትመንት ስም ለባለሀብቶች በመቸብቸባቸው የተነሳ አከባቢው ውጥረት ውስጥ ገብቷል።
የኮሻሌ ቀበሌ ነዋሪዎች (ከገረሴ ወረዳ በ15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ) “መሬታችን በግፍ ተነጥቋል” በማለት አሻፈረኝ ማለታቸውን ተከትሎ ውዝግቡ ማገርሸቱን በቦታው የነበሩ ምንጮች ለ WT Media ገልጸዋል።
ባለሀብቶቹ መሬቱን ለማልማት ባሰማሩት ማሽነሪና ሠራተኞች ላይ ነዋሪዎቹ ተኩስ በመክፈት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
ሁኔታውን በኃይል ለማረጋጋት የዞኑ እና የክልሉ የጸጥታ ኃይሎች ወደ ስፍራው የገቡ ሲሆን፤ በቀበሌው ነዋሪዎች እና በጸጥታ ኃይሎች መካከል ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ ተካሂዷል።
በዚህም የተነሳ ለጊዜው ቁጥር ያልተገለፀ የጸጥታ ኃይሎች ተገድለዋል፤ ብዙዎችም ቆስለው ወደ ገረሴ እና አርባምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታሎች መግባታቸው ታውቋል።
ከግጭቱ ሰለባዎች መካከል ዋ/ሣጅን ዮሴፍ ኡማቶ በደረሰበት ከፍተኛ ጉዳት በሆስፒታል ሕክምና ላይ እያለ በዛሬው ዕለት ሕይወቱ ማለፉ ተረጋግጧል።
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አገር መከላከያ ሠራዊት እና የፌዴራል ፖሊስ አባላት ወደ አካባቢው ገብተው የማረጋጋት ሥራ እየሰሩ ቢሆንም ሁኔታው ሙሉ በሙሉ ወደ ሰላም አልተመለሰም።
ከአካባቢው የተገኙ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በሰፈረው ውጥረት ሳቢያ በነዋሪዎች ላይ ጭስ ቦምብ ጭምር መወርወሩን እና እስከአሁን በቁጥር በትክክል ያልታወቁ ንጹሃን ዜጎች በጸጥታው አካላት መገደላቸውን ለማወቅ ተችሏል።
እንዲሁም በጸጥታ ኃይሎች በኩልም ጉዳት የደረሰባቸው መኖራቸው ተገልጿል።
መሬታቸውን እና የኑሮ መሰረታቸውን ለማስጠበቅ በተነሱት አርሶ አደሮች እና በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች መካከል ያለው ግጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰ ሲሆን WT Media በጉዳዩ ዙሪያ የሚኖሩ ተጨማሪ መርመራዎችን እና የተሟላ መረጃዎችን ለአንባቢያን የሚያደርስ ይሆናል።
Voice of Marginalized Community – WT Media