1000150855

​በትግራይ ክልል ውስጥ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የቀድሞ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን በአቅራቢያቸው ለሚገኝ የፌደራል መከላከያ ሠራዊት አሃድ በማስረከብ ወደ ተሃድሶ ማዕከላት እንዲገቡ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ጥሪ አቅርቧል።

​የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴር ጄኔራል ደርቤ መኩሪያው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ ኮሚሽኑ ከህዳር 2017 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ በማቋቋም ወደ መደበኛ ሕይወት የመመለስ ሥራዎችን ማከናወኑን አስታውሰዋል።

​የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴር ጄኔራል ደርቤ መኩሪያው

​ምክትል ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው መንግስት በትግራይ ክልል ከፍተኛ ሃብት በመመደብ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም ጥረት ቢያደርግም ሕገ-ወጡ የህወሓት ቡድን በፕሪቶሪያው ስምምነት የፈረመውን ትጥቅ የማስፈታት ስምምነት በማፍረስ ወደ ተሃድሶ ማዕከል ለመግባት ፈቃደኛ የነበሩ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና እንዳይወስዱ ሲያደናቅፍ መቆየቱን ተናግረዋል።

እንዲሁም ወጣቶችን በማፈስ ለተጨማሪ ግጭት ሲያዘጋጅ እንደነበር ጠቁመዋል።

​ነገር ግን በእነዚህ ጫናዎች መሀልም ቢሆን መንግስት በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት የመልሶ ማቋቋም መርሃ ግብሩ እንዳይቋረጥ ሰፊ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል።

የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ለሚመጡ የቀድሞ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና በመስጠት ወደ መደበኛ ሕይወት ለመመለስ የመንግስት በር ክፍት መሆኑን አረጋግጠዋል።

​በመሆኑም በትግራይ ክልል የሰላም መንገድን መርጠው ወደ ፌዴራል መንግስት የሚመጡ የቀድሞ ታጣቂዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰር፣ የቀሩትም ታጣቂዎች ትጥቃቸውን በአቅራቢያቸው ለሚገኝ የመከላከያ ሠራዊት አሃድ እያስረከቡ ወደ ተሃድሶ ማዕከላት እንዲገቡ ጥሪ አቅርበዋል።

መንግስትም ዜጎችን በዘላቂነት ወደ መደበኛ ሕይወት ለመመለስ በርካታ ሃብት መድቦ ቁርጠኛ ሆኖ እየሰራ መሆኑ ተገልጿል።

​የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ማዕቀፍ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተቋቋመ ሲሆን በግጭት ውስጥ የነበሩ የቀድሞ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ወደ ማህበረሰቡ በሰላም እንዲቀላቀሉ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለው ተነግሯል።