ኤርትራዊው የቀድሞ የባህር ኃይል አባል የኢትዮጵያ ፓስፖርት ለማግኘት ሲሞክር በአርባምንጭ ከተማ በቁጥጥር ሥር ውሏል
በሐሰተኛ ሰነዶች እና መታወቂያዎች በመጠቀም በህገ-ወጥ መንገድ የኢትዮጵያ ፓስፖርት ለማግኘት ሲንቀሳቀስ የነበረ ግለሰብ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋሉን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጋሞ ዞን ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል።
WT Media ከዞኑ ባገኘው መሠረት ይሄ የተለያዩ ሀሰተኛ የቀበሌ መታወቂያዎችን፣ የፋይዳ ቁጥሮችን እና የትምህርት ሰነዶችን በመያዝ ሲያጭበረብር የነበረው ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር ውሏል፡፡


የጋሞ ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኢንስፔክተር አብርሃም ቡሄ እንደገለጹት፤ ዳዊት ጎይቶም መስፍን የተባለው ተጠርጣሪ በኦንላይን ፓስፖርት ለማግኘት በማመልከት ወደ ኢሚግረሽንና ዜግነት አገልግሎት አርባምንጭ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በመምጣት ሰነዶችን ባቀረበበት ወቅት ጥርጣሬ በማደሩ ለፖሊስ ጥቆማ ተሰጥቷል።

በዚህም ፈጣን እርምጃ ተጠርጣሪው በቁጥጥር ሥር ውሎ ምርመራ መጀመሩ ተረጋግጧል።
በመረጃው መሠረት ፖሊስ ማጣሪያ የተደረሰባቸው፦ ተጠርጣሪው የፋይዳ መታወቂያ ከአዲስ አበባ፣ የ8ኛ ክፍል የሰርተፍኬት ማስታወሻ ከትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ እንደተሰጠ አድርጎ ስካን ኮፒ በማሰራት እንዲሁም የቀበሌ መታወቂያና ወሳኝ ኩነት መረጃ ከአርባምንጭ ከተማ የተሰጠ በማስመሰል ፓስፖርት ለማውጣት ሞክሯል።

ፖሊስ ባደረገው ጥልቅ ምርመራ ግለሰቡ የኤርትራ ባህር ኃይል አባል እንደነበር፣ ከዚያም በመኮበለል ትግራይ ክልልን አቋርጦ አዲስ አበባ እንደገባ እና በመቀጠልም መስከረም 26/2019 ዓ.ም አርባምንጭ ከተማ በመገኘት ይህንን የማጭበርበር ተግባር ለመፈጸም ሲሞክር መያዙን አረጋግጧል።
የዞኑ ፖሊስ አዛዥ በሰጡት ማሳሰቢያ ተቋማት የሰዎችን ትክክለኛ ማንነት ሳይረዱ አገልግሎት መስጠት የለባቸውም ብለዋል። እንዲሁም ለህገ-ወጥ ግለሰቦች መረጃ በመስጠት ረገድ ተሳትፎ ባላቸው አካላት ላይ ጥብቅ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አስጠንቅቀዋል።
ፖሊስ በጥርጣሬው ላይ ወቅታዊ ጥቆማ በመስጠት ትብብር ላደረጉት የኢሚግረሽንና ዜግነት አገልግሎት አርባምንጭ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አመራሮችና አባላት ምስጋና አቅርቧል።