ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን በተፈጠረ የመሬት መንሸራተት1

በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና በሌሎች አምስት ክልሎች በሚገኙ ተራራማና ለናዳ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች በ2019 ዓ.ም. የበጋ ወራት ከባድ የመሬት መንሸራተትና ናዳ ሊከሰት እንደሚችል የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን አሳስቧል።

በ2019 ዓ.ም. የበጋ ወራት (ከጥቅምት እስከ ጥር ባለው ጊዜ) የመሬት መንሸራተትና ናዳ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያና ኦሮሚያን ጨምሮ በአምስት ክልሎች ሊከሰት እንደሚችል፣ የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን አስጠንቅቋል።

ኮሚሽኑ ‹‹ብሔራዊ የበጋ ወቅት የመሬት መንሸራተትና ናዳ ማንቂያ›› በሚል ርዕስ ከቀናት በፊት ባወጣው መረጃ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በሲዳማና በኦሮሚያ ክልሎች በ2019 ዓ.ም. የበጋ ወራት የመሬት መንሸራተትና ናዳ ሊከሰት እንደሚችል አስታውቋል።

ከፍተኛ ዝናብ፣ የአካባቢው የመሬት አቀማመጥ በተለይ ተዳፋታማ የሆነ መሬት፣ የቀድሞ የመሬት መንሸራተት ታሪክና ተጋላጭነት፣ አካባቢዎቹ አደጋ ሊያጋጥማቸው ይችላል ተብሎ በቅድሚያ የተለዩባቸው መሥፈርቶች ናቸው።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስልጤ ዞን ዳሎቻና ሁልበርግ ወረዳዎች፣ በሀድያ ዞን ዱና ወረዳ፣ በከምባታ ዞን ቃጫ ቢራ፣ አንጋጫና ቃዲዳ ጋሜላ ወረዳዎች፣ በየም ልዩ ወረዳ፣ በማረቆ ልዩ ወረዳ፣ በጉራጌ ሙሁርና አክሊል፣ እንዲሁም በምሥራቅ ጉራጌ መስቃን አካባቢዎች ለመሬት መንሸራተትና ናዳ ተጋላጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ ኮሚሽኑ አስጠንቅቋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዎላይታ ዞን ቦሎሶ ሶሬ፣ ኪንዶ ኮይሻ፣ ኦፋ፣ ኪንዶ ዳዳዬ፣ ቦሎሶ ቦምቤ፣ ዱግና ፋንጎ፣ ዳሞት ወይዴ፣ ዳሞት ሶሬና ሶዶ ዙሪያ፣ በጎፋ ዞን ደንባ ጎንፋ፣ ኡባ ደብረ ፀሐይ፣ ገዜ ጎፋ፣ መልኮዛ፣ አይዴና ዛላ ወረዳዎች ለመሬት መንሸራተትና ናዳ የተጋላጭነት ሥጋት እንዳለባቸው ኮሚሽኑ ገልጿል።

በጋሞ ዞን ዲታ፣ ዳራሞሎ፣ ገረሴ፣ ጋጮ ባባ፣ ከምባ ዙሪያ፣ ቦንኬ፣ ጋርዳ ማርታና ቁጫ፣ በጋርዱላ ዞን ደራሼ ወረዳ፣ በደቡብ ኦሞ፣ በደቡብ አሪ፣ በሰሜን አሪ፣ ባካ ዳውላና የባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች ተጋላጭ ተብለው የተለዩ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሌሎች አካባቢዎች ናቸው።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ኮንታ ዞን ዱካ ዞላና አመያ ወረዳዎች፣ በከፋ ዞን ቶሌ፣ ጨታ፣ ደቻ፣ ጨና፣ አድዮ፣ ቢታ፣ ጋታዋ፣ ጌሻ፣ ጊምቦ፣ ጎባ ልዩ፣ በዳውሮ ዞን ቶጫ፣ ማረካ፣ ሎማ፣ ገና፣ እዝራ፣ ካቺ፣ ዲሳ፣ ዛባ ጋዞ ወረዳዎች፣ በቤንች ሸኮ ሰሜን ቤንችና ሸይ ቤንች በምዕራብ ኦሞ፣ ሜኒት ሻሻ፣ ሜኒት ጎልዲያ ወረዳዎች ተጋላጭ ተብለው ተለይተዋል።

ዳሌ፣ ወንሾ፣ ጭሪ፣ ማለጋ፣ ሸበዲኖ፣ በንሳ፣ ጫቤ ጋምቤልቱ፣ ብላቴ ዙሪያ፣ ሎክ ዓባያ ወረዳዎች የመሬት መንሸራተትና ናዳ ሊያጋጥማቸው ይችላል ተብለው የተለዩ የሲዳማ ክልል አካባቢዎች ናቸው።

በኦሮሚያ ክልል ጅማ፣ በሰቃ፣ ሰቃ ጨቆርሳ፣ ጌራ፣ ዴዶ፣ ኦሞ ናዳ፣ ሸቤ ሳምቦ፣ ቀርሳ፣ መና ጮራ ወረዳዎች፣ በምዕራብ ወለጋ ደያ ቢላ ወረዳ፣ በምዕራብ ሸዋ ሜታ ወልቂጤ፣ ጮቤ፣ ጭሌያና ጎሮ ባቲ ወረዳዎች፣ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን አመያ ወረዳ፣ በቡኖ በደሌ ደጋ፣ ገቺና ደዴሳ ወረዳዎች፣ በምዕራብ ጉጂ ሀምቤላ ዋመና፣ ገላናና ዓባያ ወረዳዎች በኮሚሽኑ ተጋላጭ ናቸው ተብለው የተለዩ አካባቢዎች ናቸው።

ኮሚሽኑ በዚህ ማስጠንቀቂያው ከላይ በተጠቀሱት ወረዳዎች ውስጥ ባሉ ሁሉም ቀበሌዎች የመሬት መንሸራተት ይከሰታል ማለት እንዳልሆነ መታወቅ እንዳለበት፣ ሆኖም በእነዚህ ወረዳዎች ውስጥ ተጋላጭ ቀበሌዎችን የአካባቢው አስተዳደሮች ይህንን መረጃ በመጠቀም የመለየት፣ የማረጋገጥና የአካባቢ ክትትል ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አሳስቧል።

ከዚህ ዝርዝር ውጪ ያሉ ሌሎች ወረዳዎችም በአደጋ የሚጠቁ ሊኖሩ ስለሚችሉ ማኅበረሰቡ በአካባቢው የአደጋ ምልክቶች ሲኖሩ ጥንቃቄ ማድረግና ለሚመለከተው የአካባቢ አስተዳደር ሪፖርት ማድረግ እንዳለበት፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የመከላከያ ዕርምጃዎች ሊወስድ እንደሚገባ ተነግሯል።

ሊከሰት የሚችል አደጋን ለመከላከል ክልሎችና የወረዳ አስተዳደሮች የክልል፣ የዞን፣ የወረዳና የቀበሌ የመሬት መንሸራተትና ናዳ ምላሽ ግብረ ኃይሎችን ማንቀሳቀስና ማጠናከር፣ እንዲሁም የቅድመ ማስጠንቀቂያ መልዕክቶችን ለኅብረተሰቡ እንዲያደርሱ ኮሚሽኑ አሳስቧል።

የወረዳና የዞን አስተዳደሮችና የክልል አደጋ ሥጋት ቢሮዎች ተጋላጭ ወረዳዎችን፣ ቀበሌዎችንና ሕዝቡን በቁጥር መለየትና ዝርዝር የማዘጋጀት ሚና እንዳላቸው ተገልጿል።

የክልል መንግሥታትና የፌዴራል መንግሥት በተደጋጋሚ የመሬት መንሸራተትና ናዳ በሚያጋጥሟቸው አካባቢዎች የሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ ወደ ሌሎች ቦታዎች በዘላቂነት ሽግግር እንዲያደርጉ ሚናቸውን እንዲወጡ ኮሚሽኑ አሳስቧል።

የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃን በወቅቱ ማድረስ፣ የሥጋት ሁኔታን በቀጣይነት መከታተል፣ የዝግጁነትና ቅድመ ዕርምጃን ማጠናከር፣ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽን ማጠናከር፣ የተቀናጀ ተቋማዊ አሠራርን መፍጠርና የሰው ሕይወትና መሠረተ ልማቶችን ከጉዳት መቀነስ የዚህ የመሬት መንሸራተትና ናዳ ሥጋት ቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃ ዋና ዋና ዓላማዎች መሆናቸው ተገልጿል።

ለመሬት መንሸራተት ተጋላጭ ሊሆኑ በሚችሉ አካባቢዎች መወሰድ ያለባቸውን የዝግጁነት ዕርምጃዎች ኮሚሽኑ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ የማኅበረሰብ ተሳትፎና ግንዛቤን ማሳደግ፣ የአስቸካይ ጊዜ ምላሽ ተግባራትን በአንድ የተቀናጀ ዕቅድ ሥር አካቶ መምራት ተጠቃሽ ናቸው።

የአፈር መንሸራተት፣ የድንጋይ መውደቅ፣ የቁልቁለታማ ቦታዎች መደርመስ፣ ስንጥቅ ወይም መለያየት መታየት፣ ዛፎች፣ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች፣ አጥሮች ወይም ሌሎች ቋሚ ነገሮች ወደ አንድ ጎን ማዘንበል፣ በመንገድ ስንጥቅ መፈጠር፣ የውኃ ፍሰት በድንገት መቀየር፣ መጨመር ወይም መቀነስ የመሬት መንሸራተት አደጋ ምልክቶች መሆናቸው ተጠቅሷል።

በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ አካባቢዎች የመሬት መንሸራተት አደጋዎች እየተከሰቱ የሰው ሕይወት መጥፋት፣ መፈናቀልና ከፍተኛ የሆነ የንብረት መውደም አጋጥሟል። ለአብነት በ2016 ዓ.ም. በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን በተፈጠረ የመሬት መንሸራተት ከ230 በላይ ዜጎች ሕይወት ማለፉን የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ማስታወቁ ይታወሳል።

በተመሳሳይ በሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም. በሲዳማ ክልል ዎንሾ ወረዳ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት ከአሥር በላይ ሰዎች ማለፉን የክልሉ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዎላይታ ዞን ሁለት ወረዳዎች ውስጥ ደግሞ ከአሥር በላይ ሰዎች ሕይወት ማለፉን የዞኑ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መግለጻቸው አይዘነጋም።

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታና ግድም ወረዳ መስቀል በር ቀበሌ፣ ነሐሴ 2 ቀን 2017 ዓ.ም. ንፋስ ቀላቅሎ በጣለ ከባድ ዝናብ ምክንያት በተከሰተ የጎርፍና የመሬት መንሸራተት አደጋ የአምስት ሰዎች ሕይወት ማለፉንና በ569 ነዋሪዎች ንብረት ላይ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት መድረሱን የወረዳው መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መረጃን ተጠቅሶ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን መጋቢት 1 ቀን 2018 ዓ.ም. በተለያዩ አራት ወረዳዎች በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ ተከስቶ ከ80 በላይ ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ፣ ከ125 በላይ ሰዎች የገቡበት እንዳልታወቀ፣ ከ11 ሺሕ በላይ ዜጎችም ከመኖሪያ ቀዬአቸው መፈናቀላቸውም በወቅቱ ተዘግበን ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አደጋ ወደ ተከሰተበት ሥፍራ አቅንተው የአካባቢውን ማኅበረሰብ ያፅናኑ ሲሆን መሰል አደጋዎችን በዘላቂነት ለመፍታትና የዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅ ተገቢው ጥናትና ሥራ እንዲከናወን ትዕዛዝ መስጠታቸው ይታወሳል። ከጥናቱ ጎን ለጎንም የዝናብ ወቅትን ተከትሎ አስፈላጊ የሆኑ የጥንቃቄ ተግባራት ቅድሚያ ተሰጥቶባቸው ሊከናወኑ እንደሚገባ ማሳሰባቸው አይዘነጋም።