የፖሊስ ደንብ ልብስ ለብሰው በቲክቶክ ተገቢ ያልሆነ ተንቀሳቃሽ ምስል ሲለቁ የነበሩ ሶስት የፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን የፖሊስ አባላት የሆኑ ሶስት ግለሰቦች የፖሊስ የደንብ ልብስ ለብሰው ከተቋሙ ደንብና መመሪያ ውጪ በቲክቶክ (TikTok) ማህበራዊ ገጽ ተገቢ ያልሆኑ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ሲለቁ በመገኘታቸው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።
እንደ ኮሚሽኑ ገለጻ፤ የተጠረጠሩት “የፖሊስ አባላት የተከበረውን የተቋሙን የደንብ ልብስ ለብሰው በዋዛ ፈዛዛ እና በቀልድ መልክ የሰሯቸውን ምስሎች በማህበራዊ ሚዲያ በማሰራጨት የተቋሙን ክብርና ዝና የሚያስንቅ ተግባር ፈጽመዋል” ተብለዋል።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አክሎ እንደገለጸው፤ መሰል ከፖሊስ ስነ-ምግባር እና ደንብ ያፈነገጡ ተግባራት ላይ በተሰማሩ ሌሎች አባላት ላይም ጥብቅ ክትትል እየተደረገ የሚገኝ ሲሆን አጥፊዎች ላይ አስተማሪ የሆነ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አሳስቧል።
Voice of Marginalized Community – WT Media