ባለፉት ወራት በደቡብ አፍሪካ በስደተኞች ጠል ቡድን ሲካሄድ ቆይቶ በመሃል ትንሽ ረገብ ብሎ የነበረው የ”ስደተኞች ይውጡልን” ጥያቄ ከትናት ትናንት እ.አ.አ ጥቅምት 7/2026 ጀምሮ ዳግም ማገርሻቱንና በተለያዩ ቦታዎች ሁከትና ብጥብጥ መጀመሩን በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና የኢትዮጵያዊያን ኮሚኒቲ አመራሮች አስረድተዋል።
ሁለት በደቡብ አፍሪካ ደርባን እና ጆሃንስበርግ ከተማ ነዋሪዎች የሆኑ ኢትዮጵያውያን በሰጡት ቃል፥ በደቡብ አፍሪካ በዳርባን እንዲሁም በጆሃንስበርግ ‘ሶዌቶ’ በተባሉ ከተሞች በድንገት በተፈጠረ አለመረጋጋት የንግድ ተቋማትና ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸውን ገልጸዋል።

ይህንን ተከትሎ በተከፈተ ተኩስ አንዲ ኢትዮጵያዊን ጨምሮ ሌሎች ሰዎች በጥይት ተመተው ሆስፒታል መግባታቸውንም አመልክተዋል።
ምንጮቻችን፤ በቅርቡ በሀገሪቱ ተከስቶ የነበረውን “የስደተኞች ይውጡልን” ዘመቻ ተከትሎ በተፈጠረው አለመረጋጋት እ.አ.አ ሐምሌ 7 ቀን 2026 በሀገሪቱ ሕገመንግስታዊ ፍርድ ቤት በስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች መብት ላይ ባተኮረ መዝገብ ላይ አስገዳጅ ውሳኔ ሰጥቶ ነበር።
በዚህ መሠረት ጥገኝነት ለመጠየቅ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች፣ ጉዳያቸው በይዘቱ ተመርምሮ ውሳኔ ከመሰጠቱ በፊት በህገ-ወጥ መንገድ በመግባታቸው ወይም የመሸጋገሪያ ቪዛ ባለመያዛቸው ብቻ በቀጥታ እንዳይከለከሉ ወይም ከአገር እንዳይባረሩ በማድረግ የስደተኞች መታወቂያ መሰጠት ተጀምሮ እንደነበር አስረድተዋል።
አንድ በደርባን ከተማ ነዋሪ የሆነ ኢትዮጵያዊ “የሀገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ሚንስትር ባወጣው መረሃግብር መሰረት ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ እጅግ በርካታ የሌሎች ሀገራት ዘጎች ተሰልፈው የስደተኝነት መታወቂያ እየወሰዱ ባሉበት የቡድኑ መሪዎችን ዳግም ባሰሙት ጥሪ መነሻ ሰልፍ የመበጥበጥ፣ መኪኖችና የንግድ ቦታዎችን የማቃጠል ኋላም የተኩስ እንቅስቃሴ ተጀምሯል” ብለዋል።
አንድ ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያዊያን ኮሚኒቲ አመራር የሆኑ የመረጃ ምንጭ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃል “በሀገሪቱ ምርጫ ሊካሄድ ከአንድ ወር ያነሰ ጊዜ ስለሆነ ያለው የስደተኛ ጠል ቡድኑ አባላትና አመራሮች ይህንን ወቅት ለፖለቲካ ፍጆታም አልፎም ለዝርፊያም ይጠቀሙበታል” ብለዋል።
ባለፉት ቀናት በደርባንና ጆሃንስበርግ ‘ሶዌቶ’ አከባቢዎችም የተፈጠረው የዚሁ ማሳያ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ለኢትዮጵያውያን ረቡዕ ረቡዕ የስደተኞች መታወቂያ እንዲያመለክቱ ወረፋ የነበረ ሲሆን እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያዊያን ከስደተኞች ምዝገባ ቢሮ የመስተንግዶ አቅም በላይ ተሰልፈው እንደነበር ጠቁመዋል።
ይህን ሰፍል በቲክቶክ የቀጥታ ስርጭት የሚያስተላልፉ ኢትዮጵያዊያን እንደነበሩም በመግለፅ “በዚህም ይሁን በዚያ መረጃው የደረሳቸው የፀረ ስደተኛ ቡድኑ አመራሮች ባስተላለፉት ቀጥተኛ የማህበራዊ ሚዲያ መልዕክት ሰልፍ የመበተንና ውከት የመፍጠር ሁኔታዎች ተከስተዋል” ሲሉ አስረድተዋል።
”ይህን ተከትሎም በተፈጠረው አለመረጋጋትና የንብረት ውድመት የነበረው እንቅስቃሴ ከፍተኛ ስጋት ምክንያት በማድረግ የደቡብ አፍሪካ የሀገር ውስጥ ሚንስትር ከትናት ጥቅምት 8/2026 ጀምሮ የጥገኝነት ጠያቂዎችን ማመልከቻ ለጊዜው መሰረዙን አሳውቋል” ብለዋል።
“የመመሪያው መሰረዝ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ተሽሯል ወይም የጥገኝነት ማመልከቻዎች በሙሉ ተቋርጠዋል ማለት አይደለም” ያሉት አመራሩ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ አሁንም ህጋዊ አስገዳጅነቱ የፀና እንደሆነ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
“ሚኒስቴሩ የህዝብን ደህንነት እና የድንበር አስተዳደር አቅምን በጠበቀ መልኩ ህጉን ተግባራዊ ማድረግ የሚቻልበትን ሌላ ዘላቂ አሰራር ለመቅረጽ ሲል ይህንን የተወሰነ መመሪያ ለጊዜው አቁሞታል” ሲሉም እክለዋል።
“የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ወደ ኢትዮጵያ ሄደው በመጡት ማግስት እንዲህ አይነት እንቅስቃሴ መጀመሩ የስደተኛ ጠል ቡድኑ ፕሬዝዳንቱን ስለሚቃወሙ ኢትዮጵያዊያን ላይ ትኩረት ሊያስደረግ ስለሚችል አሁንም ቢሆን ዜጎቻችን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው” ሲሉ አመራሩ አሳስበዋል።