የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)፣ የክልሉ ዋና የመንግሥት ተጠሪና የካቢኔ አባላት በዎላይታ ዞን በግንባታ ላይ የሚገኙና የተጓተቱ አበይት የልማትና የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን የመስክ ምልከታ አድርገዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በምልከታቸው የሱማሞ አየር ማረፊያ ፕሮጀክትን፣ ድንገተኛ የእሳት አደጋ ደርሶበት የነበረውን የኦቶና ሆስፒታል መልሶ ግንባታ እንዲሁም በዎላይታ ሶዶ ከተማ ከኮካቴ እስከ ግብርና ኮሌጅ በመገንባት ላይ ያለውን የኮንክሪት አስፓልት መንገድ የደረሱበትን የግንባታ ደረጃ ተዘዋውረው ተመልክተዋል።


አጠቃላይ የግንባታ አፈጻጸሙ 42 በመቶ የደረሰውንና የአፈር ቆረጣ ሥራው 99 በመቶ መጠናቀቁ የተገለጸውን የአየር ማረፊያ ግንባታ የተመለከቱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ፕሮጀክቱ ለክልሉ ብቻ ሳይሆን ለሀገር ኢኮኖሚ ወሳኝ በመሆኑ የሰው ኃይልና የማሽነሪዎችን ቁጥር በመጨመር ግንባታው በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ አሳስበዋል።
የኦቶና ሆስፒታል ታሪካዊና ለበርካታ ዜጎች የህክምና አገልግሎት የሚሰጥ አንጋፋ ተቋም መሆኑን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)፤ አላስፈላጊ የሆኑ ብሮክራሲዎችን በመቀነስ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ የተቃጠለውን ህንጻ ግንባታ ለማጠናቀቅ እንዲሰራ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

በሌላ በኩል 77 በመቶ የግንባታ አፈጻጸም ላይ የሚገኘውን የኮንክሪት አስፓልት መንገድ የመስክ ምልከታ ያደረጉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የመንገዱ መጠናቀቅ የከተማዋን እድገት በማፋጠን የኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ተመራጭነቷን ለማሳደግ ወሳኝ በመሆኑ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆን በቀንና በሌሊት እንዲሰራ አሳስበዋል።
እነዚህ ፕሮጀክቶች በመጓተታቸው ምክንያት የክልሉ ማኅበረሰብ ለከፍተኛ ምሬትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ሲዳረግ ቆይቷል።
በተለይም የኦቶና ሆስፒታል ህንፃ በመቃጠሉና የመልሶ ግንባታው በመዘገየቱ በኅብረተሰቡ የጤና አገልግሎት ማግኘት ላይ ትልቅ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን፤ የሶዶ ከተማ የኮንክሪት አስፓልት መንገድ መጓተትም የከተማዋን ውበት ከመንካቱ ባሻገር የንግድና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን አስተናቅፎ ቆይቷል።

በመሆኑም አዲሱ የክልሉ አመራር የሰጣቸው አቅጣጫዎችና የሁለት ወራት ጊዜ ገደብ ከቃላት ባለፈ በተግባር ተተርጉመው ለዓመታት የዘለቀውን የሕዝብ እንግልት እንደሚያበቁ ማኅበረሰቡ በትልቅ ተስፋ የሚጠብቀው ይሆናል።
Voice of Marginalized Community – WT Media