ይህ የምርመራ ዘገባ በ Pulitzer Center ድጋፍ የተዘጋጀ ነው።
አዘጋጅ፡ ናትናኤል ጌቾ ቤታሎ /WT Media
ማንዴራ፣ ኬንያ – በኬንያ፣ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ ድንበሮች መገናኛ ላይ የሚገኘው የማንዴራ ሶስት ማዕዘን የድህነት፣ የግጭት እና የአየር ንብረት ጫናዎች ሰዎችን ከቀያቸው አፈናቅለው የሚያጋጩበት የሩቅ ድንበር አካባቢ ነው። በዳዋ ወንዝ የፀሐይ ብርሃን በሰፈረባቸው ዳርቻዎች ላይ አንዲት በእንጨት የተሰራች ጀልባ መቶ የኬንያ ሽልንግ እየተከፈለባት ወንዙን አቋርጣ ትወስዳለች።

በዚህ ስብራት የተሞላ ድንበር ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን መሸሸጊያን ይፈልጋሉ፤ ቤቶችን ይገነባሉ፣ ትናንሽ ንግዶችን ያካሂዳሉ፣ እንዲሁም ወሳኝ የሆኑ የጉልበት እጥፎችን ይሞላሉ። ነገር ግን ይህንን የሚያደርጉት የማያቋርጥ የአስተዳደር እርምጃዎች፣ የዘፈቀደ እስሮች እና የድንገተኛ ማባረር ስጋቶች በተጋረጠባቸው ጥላ ስር ሆኖ።
በስደት ላይ ሆኖ የሰውን ልጅ ስቃይና እውነት ለአንባቢ ለማድረስ የሚደረገው ጥረት ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍላል። ይሁን እንጂ WT Media በከፍተኛ ሙያዊ ጽናት ከአምስት ወር በፊት በስልክ መረጃዎችን በማሰባሰብ ብቻ ያካሄደው በኬኒያ የማንዴራ የምርመራ ዘገባ ተከትሎ ቢቢሲ፣ ዶቼቬሌ እና የኬንያ ታዋቂ ሚዲያዎችም ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ በማድረግ በአካባቢው ላይ የነበረው ኢትዮጵያውያን በተለይም የዎላይታ ተወላጆች የጅምላ ማባረር እና መፈናቀል እርምጃና አዋጅ በመቀልበስ ረገድ ታሪካዊ ለውጥ ማምጣቱ ይታወሳል።
የኢትዮጵያውያን ሰራተኞች በማንዴራ ኢኮኖሚ ውስጥ ያላቸውን የማይተካ ድርሻ እና የሰብአዊ መብት ጉዳይ በአንክሮ ያጋለጠው ይኸው ተደማጭ ዘገባ የአካባቢው ባለስልጣናት እና ማህበረሰብ የጅምላ መፈናቀል ፖሊሲያቸውን እንዲያጤኑት እና ውጥረቱ እንዲረግብ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ይህ በተጨባጭ መረጃ ላይ ተመስርቶ የተሰራ ጥልቅ የምርመራ ስራ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ እውቅናን አግኝቷል።
WT Media ከአምስት ወር በኃላ በተደረገው ከፍተኛ ድምፅ ማሰማት እነኚህ ኢትዮጵያዊውን ለበርካታ ዓመታት ከኖሩበት እንዲባረሩ የተሰጠው አዋጅ እንዲቀለበስ ከተደረገ በኃላ ያለውን ሁኔታ በቦታው ተገኝተው ለማየትና የምርመራ ዘገባ ለመስራት ያሰናዳውን ዕቅድ ለሌሎች የየራሳቸው ዕቅድ ያቀረቡ ከዓለም ዙሪያ ከተሰለፉ አንጋፋ እና ታዋቂ ጋዜጠኞች ጋር ባደረገው ጠንካራ ውድድር ድል በማድረግ ይህንን ውድ ዓለም አቀፍ የሪፖርቲንግ ግራንት (የምርመራ ጋዜጠኝነት ገንዘብ ድጋፍ) መቀመጫውን አሜሪካ ካደረገው ስመጥር ተቋም (ፑሊትዘር ማዕከል (Pulitzer Center) ለማሸነፍ ችለናል።
በአስቸጋሪ በስደት ሆኖ እንዲህ አለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ ተወዳዳሪ የምርመራ ዘገባ መስራት እና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወትና መብት ማስጠበቅ መቻሉ የነጻ ሚዲያውን በግልጽ የሚያሳይ ነውና ኩራት ይሰማናል።
ይሄንን ዘገባ የምርምር ዘገባ ለመስራት ወደ በአካል ወደ ኬኒያ ማንዴራ በተጓዝንበት ወቅት ከዎላይታ ተሰዳ ወደ ማንዴራ በመምጣት ለአራት ዓመታት ያህል በቤት ውስጥ ሰራተኛነት ስራ ላይ የቆየችውን የሜክሊት ያዕቆብን ታሪክ ስንመለከት፣ የድንበር ህይወት ምን ያህል ከባድ እና ጥልፍልፍ እንደሆነ ያሳያል። ከዚህ ቀደም በማንዴራ በኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ ላይ ጠንካራ የማባረር ትዕዛዞች በወጡበት ጊዜ፣ ሜክሊት ከፍተኛ የችግር አደጋ አጋጥሟት ነበር።

ይሁን እንጂ ከአስተዳዳሪዋ ጋር የነበራት የቆየ ጥልቅ ዝምድና ከመፈናቀል አድኗታል። አቀጣሪዋ ከአካባቢው ባለስልጣናት እና ማህበረሰብ አባላት ጋር በቀጥታ በመነጋገር፣ እንደ ቤተሰብ የምትታመን እና የረጅም ጊዜ ታማኝ አባል እንጂ ችግር ፈጣሪ ስዳልሆነች በመሟገት ተከላክላለች።
የአካባቢው ማህበረሰብ ከስርዓት ውጭ የሆኑትን እና ጥሩ ስነ-ምግባር ያላቸውን ሰራተኞች ለይቶ የማየት ዝንባሌ ስላለው ታዛዥ የሆኑ የቤት ውስጥ ሰራተኞች ውጥረቱ እስኪያልቅ ድረስ ተደብቀው እንዲቆዩ አስችሏቸዋል።
እንደ ብዙዎቹ ስደተኞች ሁሉ ሜክሊትም በችግሩ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ አስባ ነበር፤ ነገር ግን በአገር ውስጥ የቤት ውስጥ የስራ እድሎች ሙሉ በሙሉ መጥፋታቸው እና ልጆቿን ለመርዳት የነበራት ፍላጎት መቆየትን ብቸኛ አማራጭ አድርጎታል።

የማንዴራ ማህበረሰብ አባል እና የሆቴል ባለቤት የሆነው አብዱልከሪም ኢብራሂም እንደገለጸው፣ የጅምላ ማባረር ትዕዛዞች ሲወጡ የማንዴራ የንግድ ማዕቀፍ ወዲያውኑ ይናጋል። አብዛኛዎቹ ትናንሽ ንግዶች እና ሆቴሎች በዕለት ተዕለት ስራዎቻቸው ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን ጉልበት ላይ የተመሰረቱ ስለሆኑ፣ ድንገተኛው መፈናቀል ኢንተርፕራይዞች በሮች እንዲዘጉ አስገድዷቸዋል።
እንዲሁም ከኦሮሚያ (ባሌ) መጥቶ ለአሥር ዓመታት የኖረው ዐብዱ መሐመድ እና የሞተር ጥገና ባለሙያው ቢያ ቶሎሳ እንደሚሉት፣ ስደተኞች በማንዴራ ማህበረሰብ ውስጥ የራሳቸውን ንግድ ገንብተው በሐቀኛ ስራ እየተዳደሩ ይገኛሉ።
የሴቶች ሰላም እና ልማት ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አብዲያ ሼክ አብዲራህማን እንደገለጹት ማህበሩ ከ2015 ጀምሮ በድንበር አካባቢዎች የሴቶችን አቅም የማጎልበት፣ የሰላም ግንባታ እና የንግድ ስራዎችን በመደገፍ ላይ ይገኛል።

የጋራ ማህበረሰብ ሽማግሌዎች ምክር ቤት ኃላፊ ሱልጣን ዩሱፍ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ስደተኞች እና የአካባቢው ማህበረሰብ ተመሳሳይ የኦሮሞ ቋንቋ በመናገራቸው ውህደቱ ያለ ቋንቋ እንቅፋት እንደሚካሄድ ይገልጻሉ፤ ነገር ግን መደበኛ ሰነዶች አለመኖር ለደህንነት ስጋት እንደሚሆን ያሳስባሉ።

የማንዴራ ኮሚሽነር ስቲቨን ኮሞቴ በበኩላቸው የሱፍቱ ድንበር ለዕለት ተዕለት ገበያ ክፍት መሆኑን ጠቅሰው የዓለም ባንክ በደገፈው የኢሲኦሎ-ማንዴራ መንገድ እና የድንበር ማቋረጫ ፕሮጀክቶች ይህንን መደበኛ ያልሆነ እንቅስቃሴ ወደ ህጋዊ ማዕቀፍ እንደሚያመጡት አስረድተዋል።

በኬንያ የማንዴራ ኢኮኖሚ ሕልውና ከኢትዮጵያውያን ስደተኞች ጉልበት እና ጽናት ጋር የተሳሰረ መሆኑ ተረጋግጧል። WT Media ዓለም አቀፍ እውቅናን ያስገኘለትን ይህን የመሰለ የምርመራ ስራ አጠናክሮ በመቀጠል፣ በድንበር አካባቢዎች ያሉ ሰብአዊ መብቶችን እና የኢኮኖሚ ትስስሮችን የሚጠብቁ መደበኛ የህግ ማዕቀፎች እንዲዘረጉ ድምፁን ማሰማቱን ይቀጥላል።
ይሄ ምርመራ ዘገባ እንዲሰራ የገንዘብ ድጋፍ የሰጠው ፑሊትዘር ማዕከል እ.ኤ.አ. በ2006 የተቋቋመና አድናቆትን ያተረፈ የአሜሪካ ለትርፍ ያልቆመ አንጋፋ የጋዜጠኝነት ተቋም ሲሆን ዋና መሥሪያ ቤቱ በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው የዚህ ማዕከል ዋና ተልዕኮ፣ ገለልተኛና ጥልቅ የሆኑ ድርጅታዊ ጋዜጠኝነት ሥራዎችን መደገፍ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት ባልተሰጣቸው ሥር የሰደዱ ቀውሶች ላይ የሚደረገውን የዘገባ ሽፋን ጥራት ለማሻሻል ያለመ ነው።
ይህ የምርመራ ዘገባ በ Pulitzer Center ድጋፍ የተዘጋጀ ነው።
አዘጋጅ፡ ናትናኤል ጌቾ ቤታሎ /WT Media
#Mandera #Ethiopia #Kenya #Migration #HumanRights #Journalism #EastAfrica