የኢሕአፓ አመራሩ አቶ አበበ አካሉ እና አባላት ከሁለት ወራት እስር በኋላ በዋስትና መለቀቃቸው ተረጋገጧል
በቅርቡ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን መዋቅር በሚገኘው በዘይሴ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ስልታዊ የባህልና የማንነት አፈና እንዲሁም የሰብአዊ መብት ጥሰት በተመለከተ በአደባባይ ሚዲያ በይፋ በመግለጽ የሚታወቁት ታዋቂው መምህር፣ ፖለቲከኛና ደራሲ አቶ አበበ አካሉ ከእስር ተፈተዋል።
በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ለሁለት ወራት ያህል በእስር ላይ የቆዩት የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) አመራር አቶ አበበ አካሉን ጨምሮ ሌሎች የፓርቲው አባላት እና ጠበቃ ከእስር መለቀቃቸው ተረጋገጧል።

አቶ አበበ አካሉ ጥቅምት 06 ቀን 2019 ዓ.ም ምሽት 12:00 ገደማ ከእስር ከተፈቱ በኋላ ወደ ቤታቸው መግባታቸውን በስልክ ደውለው እንዳሳወቋቸው ጠበቃቸው ሰለሞን ገዛኸኝ ለWT Media እና ለሌሎች የመገናኛ ብዙኃን አረጋግጠዋል።
የኢሕአፓ ፕሬዚዳንት አቶ አብርሃም ሃይማኖት እንደገለጹት፣ አቶ አበበ ከእስር የተፈቱት በልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተወሰነ እና በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፀና የብር 50,000 (ሃምሳ ሺህ) ዋስትና ነው። ፍርድ ቤቱ የዋስትና ውሳኔውን የሰጠው መስከረም 27 ቀን 2019 ዓ.ም ቢሆንም፣ ፖሊስ ይግባኝ በመጠየቁ ምክንያት የዋስትና ገንዘቡ ተይዞም አቶ አበበ ላለፉት 15 ቀናት ሳይፈቱ በእስር እንዲቆዩ ተደርጓል።
ለሁለት ወር ከዘጠኝ ቀናት በእስር ላይ የቆዩት የኢሕአፓ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ይስሓቅ ወልዳይ፣ አቶ አበበ አካሉ እና ጠበቃ አበራ ንጉሥ ተፈተዋል። አቶ ይስሓቅ ወልዳይ እና ጠበቃ አበራ ንጉስ ጥቅምት 07 ቀን 2019 ዓ.ም ረፋድ ላይ መለቀቃቸውን ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ አረጋግጠዋል።

ሦስቱም ግለሰቦች «ስውር የአገር ማፍረስ ሴራዎችን በማቀድ» እና «የሀገርን አንድነት በሚያፈርስ ውስብስብ የሽብር ወንጀል ድርጊት» በተሳሳተ መንገድ ተጠርጥረው በእስር ላይ ቆይተዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) የሦስቱም አባላቱን መፈታት «በደስታ እንቀበላለን» ያለው ሲሆን፣ በሌላ በኩል በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኢሕአፓ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ደረጀ ደለና «እስካሁን በእስር ላይ» መቆየታቸው «ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት» እንደሆነ በመግለጽ ተቃውሞውን አሰምቷል።
ፓርቲው አክሎም «በሰላማዊ ትግል በመሳተፍ ወይም የመንግሥትን አካሄድ በመተቸት ማንኛውም ዜጋ ለአላግባብ እስርና ለመብት ጥሰት መዳረግ የለበትም» ሲል ገልጾ፣ አቶ ደረጀ ደለና «ወዲያውኑ» ከእስር እንዲፈቱ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጠንካራ ጥሪ አቅርቧል።
WT Media በዘይሴ በቁጫ እና በሌሎችም አካባቢዎች የሚፈጸሙ የማንነትና የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን እንዲሁም በሰላማዊ የፖለቲካ ተሳታፊዎች ላይ የሚደርሱ አፈናዎችን በተከታታይ ሲዘግብ የቆየ ሲሆን፣ እውነታውን ለሕዝብ ማድረሱን አጠናክሮ ይቀጥላል።