ከኢትዮጵያ አባላ አባያ እስከ ጄኔቫ የዓለም አቀፍ ድል – ዶ/ር ልሳነወርቅ ሆንሴቦ የ2026 Global Humanitarian Hero of the Year አሸናፊ ሆኑ
ከአንድ ወር በፊት በ “AidEx Humanitarian Hero of the Year Award” ከዓለም አቀፍ ደረጃ ከተመረጡ 7 የሰብአዊ መሪዎች መካከል አንዱ በመሆን ለዕጩነት መመረጣቸውንና ድምጽ እንድንንሰጥ WT Media መዘገቡ ይታወሳል።
አሁን ደግሞ በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ከተካሄደው ታላቅ የዓለም አቀፍ መድረክ እጅግ አስደሳችና ሀገራዊ ኩራት የሆነ የምስራች ተሰምቷል።
በ AidEx Geneva 2026 የሽልማት ስነ-ስርዓት ላይ ከ100 በላይ አገራት የተውጣጡና ከዓለም ዙሪያ የተወዳደሩ በርካታ የሰብአዊነት መሪዎችን በመብለጥ፣ ኢትዮጵያዊው የሰብአዊ መሪ ዶ/ር ልሳነወርቅ ሆንሴቦ የ2026 Global Humanitarian Hero of the Year Award ብቸኛ እና አንደኛ አሸናፊ በመሆን ታላቁን የዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ጀግና ሽልማት ተጎናጽፈዋል።

ይህ ታላቅ የዓለም አቀፍ እውቅና በዎላይታ ዞን በአባላ አባያ ወረዳ ጠቅላላ ሐኪም በመሆን ከጀመሩት የሙያ አገልግሎት ጀምሮ ማህበረሰባቸውን በቅንነት ለማገልገል የገቡት ጽኑ ቃል ፍሬ ነው።
ዶ/ር ልሳነወርቅ ወላጅ እናታቸው በማህበረሰብ ደረጃ መሰረታዊ የጤና እና የድጋፍ አገልግሎት በማጣታቸው የደረሰባቸውን እንግልት እና ህመም በቅርብ በመመልከታቸው፣ ተመሳሳይ ሰቆቃ ውስጥ ላሉ ወገኖች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት በመነሳት “ሪዲዮ ኢትዮጵያ” (READIO Ethiopia) የተሰኘውን በጎ አድራጎት ድርጅት መስርተዋል።

በ2020 በደቡብ ኢትዮጵያ በአንድ ሰው እና በአንድ ራዕይ የተጀመረው ይህ ጉዞ፣ ዛሬ ላይ 16 የሰብአዊ ምላሽና የመቋቋም አቅም (Resilience) ግንባታ ፕሮጀክቶችን በመተግበር፣ ከ200 በላይ የበጎ ፈቃደኞችን አስተባብሮ ከ63,000 በላይ ወገኖችን መድረስ ችሏል።
ድርጅቱ አገልግሎቱን ከደቡብ ኢትዮጵያ እና ሲዳማ ክልሎች አልፎ ወደ አዲስ አበባ እና ጋምቤላ ክልል በማስፋፋት ዘርፈ ብዙ የሰብአዊና የልማት ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል።
ሽልማቱን ከተረከቡ በኋላ ዶ/ር ልሳነወርቅ የተሰማቸውን ታላቅ ደስታ የገለጹ ሲሆን፣ ይህ ታላቅ ክብር የእሳቸው ብቻ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
”ይህ ድል የREADIO Ethiopia ቤተሰብ፣ ከ200 በላይ የበጎ ፈቃደኞቻችን፣ የማህበረሰባችን፣ የአጋሮቻችን እና በዚህ ጉዞ ከጎኔ የቆሙት ሁሉ ድል ነው!” በማለት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
አክለውም በዚህ ዓለም አቀፍ መድረክ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት (UN)፣ ከዓለም ጤና ድርጅት (WHO)፣ ከዓለም አቀፍ የሰብአዊነት መሪዎች፣ ፕሮፌሰሮች፣ ሳይንቲስቶች፣ ፖሊሲ አውጪዎችና የልማት ባለሞያዎች ጋር በመገናኘት የማህበረሰብ ኃይልና ባለቤትነት ምን ያህል ዓለምን ሊያስተምር እንደሚችል ለማሳየት በመቻሉ ኩራት እንደተሰማቸው ተናግረዋል።

READIO Ethiopia በዋናነት የሚያከናውናቸው ሰብአዊ ስራዎች፦
🔹 ሁለንተናዊ ጤና እና የጤና እኩልነት፣
🔹 የአደጋ እና አስቸኳይ ጊዜ ምላሽ፣
🔹 ንጹህ ውሃ፣ ንጽህና እና አካባቢ ጥበቃ፣
🔹 የስነ-ምግብ እና የምግብ ዋስትና፣
🔹 የስነ-ልቦና እና የአእምሮ ጤና ድጋፍ፣
🔹 የዲጂታል ጤና መፍትሄዎች፣
🔹 የህጻናት ጥበቃ፣ የሴቶች እና የወጣቶች ማበቃት፣
🔹 ትምህርት እና የማህበረሰብ አቅም ግንባታ ስራዎች ናቸው።
ዶ/ር ልሳነወርቅ እና ሪዲዮ ኢትዮጵያ ያከናወኗቸው ግዙፍ የበጎ አድራጎት ስራዎች ቀደም ሲል በጋቪ (Gavi’s VaccinesWork) እና በ Healthy Lungs for Life 2026 የዓለም አቀፍ መድረኮች እውቅና ማግኘታቸው የሚታወስ ሲሆን የዛሬው የ2026 Global Humanitarian Hero of the Year ሽልማት የዚህ ጥረት አክሊል ሆኗል።
WT Media ለዶ/ር ልሳነወርቅ ሆንሴቦ፣ ለREADIO Ethiopia ቤተሰቦች እና ሙሉ ለሙሉ ለኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አላችሁ ይላል።
Voice of Marginalized Community – WT Media