የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) በደቡብ ኦሮሚያ ቦረና ዞን ሞያሌ ከተማ እና አዋሳኝ አካባቢዎች እየተባባሰ የመጣውን ጥቃት፣ የታጠቁ ኃይሎች ሰርጎ መግባት እና ኢ-ሕገመንግሥታዊ የአስተዳደር ለውጥ እንቅስቃሴዎችን በጥብቅ እንደሚያወግዝ ጥቅምት 14 ቀን 2019 ዓ.ም. ባወጣው ይፋዊ መግለጫ አስታውቋል።
ኦፌኮ በመግለጫው፤ ጥቅምት 8 ቀን 2019 ዓ.ም. በሞያሌ ከተማ የ13 ዓመቷ ታዳጊ ዲቆ ጃተኒ በሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል በአሰቃቂ ሁኔታ መገደሏን ተከትሎ የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልጿል።
በተጨማሪም በግጭቱ ምክንያት የ9 ሌሎች ንጹሃን ዜጎች ህይወት ማለፉን እና ከ2,400 በላይ ሰዎች ተፈናቅለው ወደ ኬንያ መሰደዳቸውን ማረጋገጡን ገልጾ፣ ለሟች ቤተሰቦችና ለቦረና ኦሮሞ ማህበረሰብ መጽናናትን ተመኝቷል።

ኦፌኮ ባለፉት ሳምንታት ከሶማሌ ክልል በመጡ የታጠቁ ኃይሎች የሚደረገው የድንበር ጥሰት አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ መጨመሩን ጠቅሶ፤ ድርጊቱ መሬትን በኃይል ለመያዝ፣ አርብቶ አደሩን ለማፈናቀል እና የአስተዳደር ወሰኖችን በአንድ ወገን ውሳኔ ለመቀየር የሚደረግ ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን የጣሰ አካሄድ ነው ብሏል።
የኦሮሞ እና የሶማሌ ህዝቦች የረጅም ጊዜ የሰላማዊ አብሮ መኖር፣ የንግድ እና የባህል ትስስር ታሪክ ያላቸው ማህበረሰቦች መሆናቸውን ያወሳው ፓርቲው፤ ሁለቱም ህዝቦች ግጭትን ለመፍጠር እና የመንግስት የአስተዳደር ውድቀቶችን ለመሸፈን የተወጠኑ ከፋፋይ የፖለቲካ አጀንዳዎችን ውድቅ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።
ከኦፌኮ በቦረና ኦሮሞ ህዝብ ላይ የሚሰነዘሩ ማናቸውም የትጥቅ ጥቃቶች በአፋጣኝ እንዲቆሙ እና የፌደራል መንግሥት የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቋል።
በታዳጊ ዲቆ ጃተኒ እና በሌሎች ንጹሃን ግድያ ዙሪያ ግልጽ፣ ገለልተኛ እና ፈጣን ምርመራ ተካሂዶ ትዕዛዝ የሰጡትን ጨምሮ ፈጻሚዎች በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ።
ሕገ-መንግሥታዊ አሰራርን ማክበር፦ የድንበር ውዝግቦች እ.ኤ.አ. በ2004 (በ1997 ዓ.ም.) በተካሄደው የህዝበ ውሳኔ የመጨረሻ ውጤት መሰረት ብቻ እንዲፈቱ እና የሶማሌ ክልል ያደረጋቸውን ኢ-ሕገመንግሥታዊ የአስተዳደር መዋቅር ለውጦች በአፋጣኝ እንዲሰርዝ።
የፌደራል እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስታት የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ባለመቻላቸው ተጠያቂ መሆናቸውን በመጠቆም፤ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ አባ ገዳዎችን እና የአካባቢ ተወካዮችን ያሳተፈ ፈጣን ውይይት እንዲጀመርም ጠይቋል።
አከለውም ፓርቲው ለተፈናቀሉ ዜጎች የምግብ፣ የውሃ እና የህክምና አስቸኳይ እርዳታ እንዲቀርብ እና በሰላም ወደ ቀዬአቸው የመመለስ ዋስትና እንዲሰጣቸው ጠይቋል።