ባጋጠመው አስተዳደራዊና የፋይናንስ ቀውስ የተነሳ የደቡብ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት የህልውና ፈተና ውስጥ መውደቁን የድርጅቱ ሠራተኞች እየገለጹ ይገኛሉ።
ተቋሙ የሥርጭት መሣሪያዎችን ለመጠገንም ሆነ ለሠራተኞቹ ደሞዝ መክፈል ባለመቻሉ ቀጣይ ህልውናው አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ተነግሯል። የደቡብ ኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ማህበር በበኩሉ የፌደራሉ መንግሥት ተቋሙን ከመፍረስ አደጋ እንዲታደግ ጠይቋል።
በየካቲት 1997 ዓ.ም በይፋ ሥራውን የጀመረው የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በ49 ቋንቋዎች በማሰራጨት የበርካቶች ድምፅ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። ድርጅቱ የቀድሞው የደቡብ ክልል መፍረስን ተከትሎ በአዲስ አስተዳደራዊ መዋቅር የተደራጁት የሲዳማ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ፣ የማዕከላዊ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች በጋራ ያስተዳርሩት ተብሎ ነበር።

በክልሎቹ እየተደጎመ፣ በውስጥ ገቢም እየታገዘ በማያመች ሁኔታ ሥራውን የቀጠለው ድርጅቱ አሁን ላይ ተቋማዊ ህልውናው አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የድርጅቱ ሠራተኞች ይናገራሉ።
ከአራት መቶ በላይ ሠራተኞች ያሉት ድርጅቱ የሥርጭት መሣሪያዎች ለመጠገንም ሆነ ለሠራተኞች ደሞዝ መክፈል ከማይችልበት ደረጃ ላይ መገኘቱን ነው ከሠራተኞቹ ሁለቱ ለዶቼ ቬለ የገለጹት።
ኤሌክትሪክ ሲጠፋ የጣቢያው ስርጭትም አብሮ እንደሚቋረጥ የጠቀሱት ሠራተኞቹ “አሁን ላይ የሬዲዮው ሥርጭት በፋይናንስ ችግር ምክንያት ከሳተላይት ወርዷል።
በተጨማሪም ጊዜውን የጠበቀ የደሞዝ ክፍያ እያገኘን አይደለም። በዚህም የተነሳ አብዛኛው ሠራተኛ ለቤት ኪራይና ለልጆች የትምህርት ቤት ክፍያ ለመክፈል ባለመቻሉ ለሥነ ልቦና ጫና ተዳርጎ ይገኛል” ብለዋል።
ድርጅቱ የቀድሞው የደቡብ ክልል መፍረስን ተከትሎ አራቱ ክልሎች በጋራ እንዲያስተዳድሩት በወቅቱ አቅጣጫ መቀመጡን ሠራተኞቹ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ የማዕከላዊ እና የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች ብቻ የፋይናንስ ድጋፍ ማድረጋቸውን የጠቀሱት ሠራተኞቹ ይህም ድርጅቱን ለከፍተኛ የፋይናንስ ቀውስ ዳርጎታል ብለዋል።
የድርጅቱ ቀጣይ ህልውና ግልጽ እንዲደረግ፣ የአስተዳደርና የፋይናንስ ቁጥጥር ሥርዓት እንዲሰፍንና ተቋሙ ባለቤት እንዲበጅለት ላለፉት አራት ዓመታት ሲወተውቱ መቆታቸውን ሠራተኞች ይናገራሉ። ነገር ግን ሁኔታዎች ከመባባሳቸው በስተቀር ለጥያቄዎቹ ምላሽ እንዳላገኙ ጠቅሰዋል።
አሁን ላይ የድርጅቱን ህልውና ለመታደግ እና የባለሙያውን ጥቅም ለማስጠበቅ ያስችለናል ያሉትን ውይይት በማካሄድ በተደራጀ ሁኔታ መብታቸውን ለማስከበር እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ገልጸዋል።
የዶቼ ቬለ የድርጅቱን የሥራ ሃላፊዎችንም ሆነ የአራቱ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድር ጽ/ቤቶችን ለማነጋገር ጥረት ቢደረግም በጉዳዩ ላይ ይመለከተኛል ብሎ ምላሽ የሚሰጥር አካል ሊያገኝ አልቻለም። ያም ሆኖ የደቡብ ኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ማህበር የፌደራሉ መንግሥት ተቋሙን ከመፍረስ አደጋ እንዲታደግ ጠይቋል።
ድርጅቱ ህብረ ብሄራዊት ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ እያገለገለ እንደሚገኝ የጠቀሰው መግለጫው አሁን ያለው ማነቆ ተፈትቶ የብሄር ብሔረሰቦች ድምጽ ሆኖ እንዲቀጥል መጠየቁን የገለጸው የማህበሩ ፀሀፊ ዮናታን ዘብዲዮስ “እየፈረሰ ያለው ተቋም ነው። ይሄ ደግሞ ከዴሞክራሲ ተቋማት አንዱ ነው። ዴሞክራሲ ተቋማትን እናጎለብታለን ከተባለ እንደዚህ አይነት ተቋማት መጠናከር እንጂ መፍረስ የለባቸውም። የሠራተኞች ደሞዝም በወቅቱ መከፈል እንዳለበት ጠቅሰናል። ይሄ የመብት ብቻ ሳይሆን ሰብአዊነትም ጉዳይ ጭምር ነው። ለዚህም ተፈጻሚ እንዲደረግ ድርጅቱን እየጠየቅን እንገኛለን” ብሏል።
ዋናው ማሠራጫው በሀዋሳ ከተማ የሚገኘው የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በ11 ቅርንጫፎቹ አማካኝነት ለበርካታ ሚሊዮን አድማጭ ተመልካቾቹ ተደራሽ እንደሆነ ይታወቃል።
WT Media | Voice of Marginalized Community