1793376881278

የሞያሌው ግጭት ከፍተኛ ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ እያስከተለ በመሆኑ የፌዴራል መንግስት አስቸኳይ ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጥ ነዋሪዎች ጠይቋል።

​በኢትዮጵያና ኬንያ ድንበር አዋሳኝ በሆነችው ሞያሌ ከተማ በኦሮሚያ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ወሰን አካባቢዎች ከ10 ቀናት በፊት በባንዲራ መስቀል ውዝግብ ምክንያት የተቀሰቀሰው አውዳሚ ግጭት አሁንም ድረስ ከፍተኛ የጸጥታ ስጋት እና አጣዳፊ የሰብአዊ ቀውስ ደቅኖ ቀጥሏል።

ከቀናት በፊት በወሰን አካባቢዎች የጀመረው ውጥረት እና ከባድ የተኩስ ልውውጥ ዛሬም ቢሆን የተወሰነ አንጻራዊ መረጋጋት ቢታይም፣ የሁኔታው ስጋት እና ውጥረት ግን ሙሉ በሙሉ አለመቀነሱን የአከባቢው ነዋሪዎች ለ WT Media አስረድተዋል።

​በሞያሌ ከተማ በሁለቱ ክልሎች የፖሊስ እና ልዩ ኃይሎች መካከል ላለፉት ቀናት ሲካሄድ የቆየው አውዳሚ የተኩስ ልውውጥ አሁን ላይ ከበፊቱ ጋር ሲነጻጸር የተወሰነ መረጋጋት ቢታይም፣ የከባድ እና የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎች ተኩስ ሙሉ በሙሉ አልቆመም ብሏል። አልፎ አልፎ በቀን ውስጥ የሚሰሙ ድምጾች ለነዋሪዎች ከፍተኛ ስጋት ፈጥረዋል።

የሞያሌ ተፈናቃዮች ወደ ኬኒያ ጋምቦ በተፈናቀሉበት ምግብ እየሰሩ

ከተማዋ ውስጥ የሚገኙ አብዛኞቹ የንግድ ተቋማት፣ የትራንስፖርት አገልግሎቶች እና የባንክ ስራዎች ሙሉ በሙሉ ተዘግተው የሚገኙ ሲሆን ነዋሪዎች የወደሙ ንብረቶቻቸውን ለመቃኘት እንኳን በስጋት ውስጥ ሆነው የሚንቀሳቀሱበት አስከፊ ሁኔታ ተፈጥሯል።

WT Media ዛሬ ጥቅምት 20/2019 ዓ.ም ( Oct 30/2026 G.C) በቀጥታ ከስፍራው ከተለያዩ ምንጮች ጋር በስልክ ባደረገው መረጃ ልውውጥ ከዚህ ቀደም ከስልክ ንግግሮች በስተጀርባ በጎልህ ይሰማ የነበረው የከባድና የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎች የተኩስ ድምፅ አልተሰማም።

​ሞያሌ የሁለቱ ሀገራት (የኢትዮጵያ እና የኬንያ) ድንበር ተሻጋሪ የንግድና የኢኮኖሚ ማዕከል በመሆኗ፣ ከሶማሌ እና ከኦሮሚያ ነዋሪዎች ባለፈ ከሌሎች የሀገራችን ክፍሎች (እንደ ደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ያሉ) መጥተው በንግድና በዕለት ጉልበት ስራ ላይ የተሰማሩ በርካታ ዜጎች ይኖሩበታል።

​ከ10 ቀናት በላይ በዘለቀው የከተማዋ መዘጋት ምክንያት አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ከቤት መውጣት ባለመቻሉ ለከፍተኛ የምግብ እጥረት እና ለረሃብ አደጋ ተጋልጧል።

የሞያሌ ተፈናቃዮች ወደ ኬኒያ ጋምቦ በተፈናቀሉበት ምግብ እየሰሩ

​ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ እና ከኬንያ ወደ ኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ ትራንዚት መኪኖች እና እቃዎች ባሉበት ቆመዋል። የድንበር ንግዱ በመቋረጡ የብዙዎች የኑሮ መሰረት ሙሉ በሙሉ ተናግቷል።

​በግጭቱ ሳቢያ ህይወታቸውን ለማዳን ሲሉ ድንበር ተሻግረው ወደ ኬንያ ማርሳቢት ካውንቲ (ጋምቦ እና አካባቢው) የተሰደዱ ዜጎች ቁጥር ከ50,000 እስከ 60,000 እንደሚደርስ ተገልጿል።

​የኬንያ ቀይ መስቀል ማህበር እና ሌሎች ሰብአዊ ድርጅቶች ለአረጋውያን፣ ለህጻናት እና ለእናቶች አስቸኳይ ድጋፍ እያደረጉ ቢሆንም፣ የችግሩ ስፋት ከድርጅቶቹ አቅም በላይ እየሆነ መጥቷል።

​በከተማዋ ውስጥ በቤት ውስጥ ተደብቀው ያሉ፣ የቆሰሉ እና አስከሬናቸው ያልተነሳ ዜጎች መኖራቸው የጤና እና የጸጥታ ስጋቱን አባብሶታል።

​የአካባቢው ነዋሪዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እና አባቶችን በማቀራረብ በኩል ጥረቶችን እያደረጉ ቢሆንም የፌዴራል መንግስት እና የጸጥታ አካላት ፈጣንና በቂ መፍትሄ በመስጠት ረገድ የውሃ አቁማዳ ምላሽ መስጠታቸው ከፍተኛ ቅሬታ አስነብቷል።

በግጭቱ ምንም ዓይነት እጅ የሌላቸው፣ ከተለያዩ የሀገሪቱ ማዕዘናት መጥተው በሰላም የሚተዳደሩ ንጹሃን ዜጎች ለዚህ ሰቆቃ መዳረጋቸው አሳሳቢ ነው።

የፌዴራል መንግስት እና የሁለቱ ክልሎች አስተዳደሮች በአስቸኳይ በመግባት ዘላቂ የተኩስ ማቆም እንዲያውጁ፣ የሰብአዊ እርዳታ ኮሪደር እንዲከፍቱ እና ለተጎዱ ዜጎች አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡ የአካባቢው ነዋሪዎች እና ተፈናቃዮች በጥብቅ ጠይቋል።