1000159089

​በሶማሊላንድ ቦራማ ከተማ በኦሮሞ ማህበረሰብ አባላት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች መፈጸማቸውን የሶማሊላንድ ባለስልጣናት እና የማህበረሰብ መሪዎች በጥብቅ አውግዘዋል።

በጥቃቱ ከ150 በላይ የሚሆኑ የነዋሪዎች መኖሪያ ቤቶች መውደማቸው፣ መዘረፋቸው እና ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል።

​እንደ ሂራን ኦንላይን ዘገባ ከሆነ፣ ጥቃቱን የፈጸሙት የቡድን ወጣቶች ሲሆኑ፤ ለዓመታት በከተማዋ ሲኖሩ የነበሩ የኦሮሞ ማህበረሰብ አባላትን ቤቶች አውድመዋል፣ ዘርፈዋል እንዲሁም በእሳት አቃጥለዋል።

ጉዳቱ የደረሰባቸው አንዳንድ ነዋሪዎችም ደህንነታቸውን ለመጠበቅ ሲሉ ወደ ቦራማ አውሮፕላን ማረፊያ እና ደህና ወደሚሏቸው አካባቢዎች ተሰደዋል።

​የአውዳል ክልል ገቨርነር ቦቆር ሀሰን ዳሂር ሀዲ ድርጊቱን አውግዘው፣ ይህ ድርጊት የማህበረሰቡን የሰላማዊ አብሮነት እና እንግዳ ተቀባይነት እሴቶች የሚቃረን መሆኑን ተናግረዋል።

የጸጥታ ኃይሎች በጥቃቱ ተሳትፈዋል ተብሎ የተጠረጠሩ አንዳንድ ወጣቶችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን እና ሌሎች አጥፊዎችን እያሳደዱ መሆናቸውን ገልጸው፣ በህግ ፊት እንደሚቀርቡ ቃል ገብተዋል።

​የሶማሊላንድ መረጃ ሚኒስትር በካርክ ጃማ ባቱን ጥቃቱን አውግዘው፣ ባለስልጣናት ኃላፊዎቹን እንደሚያጣሩ ገልጸዋል። ማንም ሰው ህግን በራሱ እጅ መውሰድ መብት የሌለው መሆኑን አስጠንቅቀው፣ እንዲህ ያሉ ድርጊቶች የሶማሊላንድን ዴሞክራሲያዊ ገጽታ እና አስተዳደር እንደሚያጎድፉት ተናግረዋል።

​የቦራማ ከተማ ከንቲባ ማሀሙድ ሼክ ኢብራሂም ለተጎዱት ነዋሪዎች ይቅርታ ጠይቀው፣ የተፈጸመው ድርጊት የከተማዋን እሴቶች እንደማይወክል ገልጸዋል።

Homes allegedly belonging to Oromo residents burning in Borama, Somaliland. Photo: Hiiraan Online.

ወጣቶች በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚለቀቁ እና በማህበረሰቦች መካከል ጥላቻን ሊያነዱ የሚችሉ አነቃቂ ጽሑፎችን እና ቪዲዮዎችን ተጽዕኖ ስር እንዳይወድቁ አሳስበዋል።

​የአገር ሽማግሌዎች እና የህግ አውጪዎችም ጥቃቱን አውግዘው፣ የኦሮሞ ነዋሪዎች ጥበቃ እንዲደረግላቸው እና ኃላፊዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ ጠይቀዋል። የሶማሊላንድ የሀገር ሽማግሌዎች ምክር ቤት አባል የሆኑት አብዱላሂ ሀሺ አብዲ ቤቶችን ማቃጠል፣ ንብረት መዝረፍ እና ዜጎችን ማስፈራራት ምንም ማረጋገጫ ወይም ምክንያት የሌለው መሆኑን ተናግረዋል።

የህግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል ሞሀመድ አቢብም ባለስልጣናት ጥቃቱን ለመከላከል ባለመቻላቸው በመተቸት፣ የጎሳ ወይም የፖለቲካ ቅሬታዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚሰነዘር ጥቃትን ሊያጸድቁ እንደማይችሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

​ጥቃቶቹ ከመፈጸማቸው አስቀድሞ እና በሂደት ላይ እያለም በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በቦራማ በሚገኙ የኦሮሞ ማህበረሰብ አባላት ላይ ጥላቻን የሚያነሳሱ አነቃቂ ጽሑፎች እና ቪዲዮዎች ተሰራጭተዋል።

​የከተማዋ ከንቲባ ማሀሙድ ሼክ ኢብራሂም ወጣቶች ውጥረትን የሚቀሰቅሱ የመስመር ላይ ይዘቶች እንዳያሳስቷቸው አስጠንቅቀው፣ ነዋሪዎች በጎረቤት ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ግጭት ምክንያት ንጹሃን ዜጎችን ኢላማ እንዳያደርጉ አሳስበዋል።

የማህበረሰብ መሪዎችም በቦራማ የሚኖሩ ሰዎች በሞያሌ ለተከሰተው ግጭት ተጠያቂ መሆን እንደሌለባቸው በመግለጽ የጥላቻ እና የመበቀል ስሜቶች እንዲስፋፉ አስጠንቅቀዋል።

​በኢትዮጵያ በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ በምትገኘው ሞያሌ ከተማ በቦረና እና ጋሬ ማህበረሰቦች መካከል በነበረው የይገባኛል ጥያቄ እና ጥቅምት 18 ቀን የ13 ዓቷን ታዳጊ ዲቆ ጃታን አጋን መገደል ተከትሎ ግጭት መቀስቀሱ ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ በደቡብ ኦሮሚያ በተደረጉ ተከታታይ ግጭቶች ሞት፣ መፈናቀል እና የቤት መውደም አደጋዎች አጋጥመዋል። በሁነቱም ሳቢያ ሺዎች ወደ ኬንያ መሰደዳቸው እና በጎረቤት አካባቢዎች በሚገኙ የኦሮሞ ዜጎች ላይ ጥቃት ይሰነዘራል የሚል ስጋት ማደሩ ተመላክቷል።

​WT Media | Voice of Marginalized Community