“ሠርግና ምላሽ፤ ሙሾና ተዝካር (ሁለቱም የክልላችን በርጋጊዎች መተንፈስ አለባቸው በርጋጊ፥ ህዝብ አይደለም)” - በአቶ አይናለም ታደሰ

“ሠርግና ምላሽ፤ ሙሾና ተዝካር (ሁለቱም የክልላችን በርጋጊዎች መተንፈስ አለባቸው በርጋጊ፥ ህዝብ አይደለም)” – በአቶ አይናለም ታደሰ ጥልቅ ሀተታና አስተያየት

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጎፋ ተውላጅ፣ የታሪክና የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ ምሁር የሆኑት አቶ አይናለም ታደሰ በይፋዊ የፌስቡክ ገጻቸው ያቀረቡት ጥልቅ ሀተታና አስተያየት እንደሚከተለው አዘጋጅተን አቅርበነዋል።

የኢትዮጵያ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር የዶርዜኛ ትርጉም ሥራ ፕሮጀክት ይፋ መደረጉን ተከትሎ ከህብረተሰቡ ዘንድ የተለያዩ አዎንታዊና አሉታዊ አስተያየቶች፣ ውዝግቦች እና የተቃውሞ ሃሳቦች ሲነሱ ቆይተዋል። ይህንን የተለያየ አስተያየትና ውዝግብ ተከትሎም ኢትዮጵያ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያና ማስተካከያ መግለጫ አውጥቶ እንደነበር ይታወሳል። 

እኛም WT Media ይህንን አጠቃላይ ሂደት እና የተሰጡ ማብራሪያዎችን በሰፊው መዘገባችን የሚታወስ ነው። በዚህ ወቅታዊ እና አከራካሪ ጉዳይ ዙሪያ የታሪክና የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኙ አቶ አይናለም ታደሰ የሰጡትን ሙሉ እና ያልተበረዘ ሃሳብ ከዚህ በታች እናቀርባለን።

በዚህ ዐምድ ላይ አቶ አይናለም በኢትዮጵያ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር የዶርዜኛ ትርጉም ሥራ ፕሮጀክት ምክንያት፥ የዎላይታና የጋሞ “በርጋጊዎች” የሰጥቶ መቀበል የመረብና የመሬት የልምሻ ፖለቲካ ወግን እንበረብራለን በሚል ይጀምራሉ። በዚህ ጽሑፍ የምከራከረው፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ሃይማኖታዊ ፋይዳው ላይ ሳይሆን፥ በሚያስከትለው ተዘዋዋሪ ማህበራዊ/ፖለቲካዊ ለውጥና ጥቅል የሽግግር ፋይዳው ላይ ነው ይላሉ። ትርጉሙ ተዘዋዋሪ ፋይዳ አለው።

“የኢትዮጵያ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ የዶርዜን ህዝብ በልዩነት ለመድረስ የመጽሐፍ ቅዱስ የትርጉም ሥራ መጀመሩን ይፋ ባደረገ ማግስት፥ የዎላይታ በርጋጊዎች እንደ ልማዳቸው የጋሞ በርጋጊዎችን ለማብሸቅና ለመተንኮስ አጀንዳውን ከዐየር ቀልበው ሠርግና ምላሽ ሲያደርጉት፥ የጋሞ “በርጋጊዎችም” ወዲያው በሽቀውላቸው አጀንዳውን የሙሾና የተዝካር አደረጉት፥ አጨሱት፥ አጠቆሩት” ይላሉ።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጎፋ ተውላጅ፣ የታሪክና የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ ምሁር የሆኑት አቶ አይናለም ታደሰ

“እርግጥ ነው፥ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበሩ ጋሞ ዞን ውስጥ ከሚነገሩ ቋንቋዎች በአንዱ (በዶርዜዎች) የትርጉም ሥራ መጀመሩ፥ በጋሞ ልጆች ክፉኛ ተቃውሞ ገጥሞታል። ነገር ግን የእኛ የዳር ህዝቦች፥ በአገሩ የፖለቲካ አናሶች የብዙ ጊዜ ጥያቄያችን የነበረው፦ “ቋንቋችን አልተጻፈበትም፣ ቋንቋችን የአደባባይ፣ የሃይማኖት፣ የመንግሥት፣ የስነጽሑፍ ስላልሆነ አላደገም፣ ወዘተ” ነበር” በሚል ያብራራሉ። 

“አሁን ታዲያ ሊጻፍበት ሲሆን ምነው አበይንበት አብዮት ጠራንበት? ዶርዜኛ ማደግ መመንደግ የሚገባው ቋንቋችን አይደለምን? በዓለም የመጀመሪያ/native ተናጋሪ ህዝብ የሌላቸው ቋንቋዎች (ለምሳሌ፦ ላቲን እና ግዕዝ) እንኳን ከሞቱበት ተነስተው እንዲጻፍባቸውና እንዲነገርባቸው ብዙ ጥረት በሚደረግበትና ገንዘብ በሚፈስበት ዓለም፥ አፋን የፈታበት ሰፊ ህዝብ ያለውን ቋንቋ (ዶርዜኛ) እንዲህ ማፈን ማንን ያስደስታል? ጋሞን በምን ይጠቅማል? ማንን እየታገልንበት ነው? እውነት የፈራነው ጋኔን የሚወርሰን እሱ ነውን” በሚል አቶ አይናለም ይጠይቃሉ።

እውነት ለመናገር ብዙ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን (አማርኛን ጨምሮ) ያደረጀውና ያዘመነው የሚሲዮናውያን (መጽሐፍ ቅዱስን በብዙ ቋንቋዎች የማስተርጎማቸው) ሥራ መሆኑን አቶ አይናለም ታደሰ ጠቅሰዋል። በተለይም የባርያው (የአባ አናሲሞስ ነሲብ) የኦሮምኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፥ ለኦሮምኛ ቋንቋ የስነ ጽሑፍ ዕድገት – ቁቤ፥ ሚናው ትክ እንዳልነበረውና የኦሮሞ ህዝብ ክርስትናን ለመስማትም እጅግ እንዳገዘው ተናግረዋል። ኦርቶዶክሳዊ ክርስትናን ጨምሮ እስከ ዛሬ የሚጠቀመው የኦሮምኛ ትርጉም (Macaafa Qulqulluu) የሚሲዮናውያን ሥራ መሆኑን አክለዋል።

ሌላው ቢቀር፥ እኛ አካባቢ (በጋሞ፣ በጎፋና በዳውሮ) የወላይትኛ ቋንቋን እጅግ ያስፋፋው፥ በአካባቢው መጽሐፍ ቅዱስ ለመጀመሪያ ጊዜ በወላይትኛ መተርጎሙና ስብከት/ዝማሬውም ለእነዚያ አካባቢዎች በወላይትኛ መሸጋገሩ/መነገሩ መሆኑን አቶ አይናለም አንስተዋል። እስከ ዛሬም ቢሆን ዎላይትኛ በጋሞ፣ በጎፋ፣ በዳውሮ የወንጌላዊ አማኙ ክርስቲያን የአምልኮና የአገልግሎት ቋንቋ ሆኖ መቀጠሉን ገልጸዋል። የካምባ ልጅ፣ የጨንቻ ልጅ፣ የዛላ ልጅ፣ የጎፋ ልጅ፣ የዑባ ልጅ፣ የዳውሮ ልጅ፣ … በየየአካባቢያቸው በየራሳቸው ቋንቋ ቢያወሩም፥ ዝማሬዎቻቸው በወላይትኛ መሆናቸውን ጠቁመው፥ እርግጥ ነው አሁን አሁን በጋሞኛም፣ በጎፍኛም፣… የሚሞክሩ ብቅ ብቅ እያሉ መሆኑን እና ይህ እንደሚበረታታ ተናግረዋል።

አቶ አይናለም ታደሰ አያይዘውም ሲናገሩ፦ “መጽሐፍ ቅዱስ በዓለም በብዙ ቋንቋዎች የተተረጎመ ብቸኛ መጽሐፍ ነው” ብለዋል። ምናልባት ኢትዮጵያ ውስጥም በብዙ ቋንቋዎች የተተረጎመው መጽሐፍ ቅዱስ ሳይሆን አይቀርም ሲሉ ገልጸዋል። ይህ አንዳንዶች እንደሚሉት “ኢትዮጵያን የማዳከምና የማፍረስ የነጮች አጀንዳ” አይደለም ያሉት ተንታኙ፥ እዚህ ሰፈር ደግሞ ይህን የትርጉም ሥራ፦ “የጋሞን አንድነት ለማዳከም የቅርብና የሩቅ ጠላቶች ሴራ ነው” የሚልም እንዳለ ጠቅሰው፥ “በፍፁም አይደለም፤ ጠላት ፍለጋ መባዘን ብርታት አይደለም” ብለዋል።

አዎን፥ ጋሞ ዞን ውስጥ ብዙ ቋንቋዎች መኖራቸውን የገለጹት አቶ አይናለም፥ እኛ እነዚያን የግድ “የጋሞኛ dialects” አልላቸውም ማለታቸውን አስረድተዋል። እሳቸው ለምሳሌ ዎላይትኛን፣ ጋሞኛንና ጎፍኛን ጠንቅቄ ብሰማ/ባውቅም ባልታ፣ ሻራ፣ ዛርጉላና ጋንታ የሚወሩ ቋንቋዎችን እንደማይሰሟቸው ገልጸዋል። ባልታ ለአንድ አመት ገደማ ሙሉ ጊዜ ቀበሌያቱን አዳርሼ ሠርቻለሁ ቢሉም፥ አዲስ ቋንቋ ለመልመድ ደካማ በመሆናቸው ቋንቋውን እንዳልቻሉትና ጓደኛቸው (ጉቼ) እንደቻለው ተናግረዋል። ወላይትኛንና ጋሞኛንም ቢሆን naturally/fluently ማውራት እንደማይችሉ ጠቅሰው፥ ነገር ግን ሁለቱንም ከ97/8% በላይ እንደሚሰሙ ገልጸዋል። 

ጎፍኛንማ… ስለ እኔ ሌላው ይናገር ማለታቸውን አንስተው፥ ነገር ግን ጋሞ ዞን ውስጥ፥ ኦቾሎና ዶርዜ የሚወሩትን በተወሰነ ርቀት መከታተል እንደሚችሉና “እሰማለሁ” ማለት ግን እንደማይችሉ፣ እጠረጥራለሁ እንጂ ማለታቸውን ገልጸዋል።

ዘዬ/dialect የሚባለው የዎላይትኛ/የጋሞኛ/የጎፍኛ ዓይነቱ መመሳሰሎችና መለያየቶች መሆኑን የጠቀሱት ተንታኙ፥ የንጹህ ወላይትኛ/ጋሞኛ/ጎፍኛ ተናጋሪዎች እየተሳሳቁ እርስ በርስ በቀላሉ መግባባት እንደሚችሉ ተናግረዋል። ነገር ግን የባልታ ሰው አፋን በፈታበት ቋንቋው (በባልትኛ) ከቦንኬና ከዲታ ሰው ጋር እንኳን እንደማይግባባ ገልጸዋል። የባልታ ሰው የራሱን ትቶ ነው ከቦንኬ/ከጨንቻ ሰው ጋር የሚግባባው ያሉት አቶ አይናለም፥ የዶርዜ ሰውም በራሱ ካወራ ሌላው በውጤታማነት እንደማይከታተለው ጠቁመዋል። ነገር ግን የወላይታ ሰው ከዲታ ሰው ጋር ከ95% በላይ ሊግባባ እንደሚችል፣ የዲታ ሰው ግን ከባልታ ሰው ጋር (የባልታው ሰው ለዲታው ሲል የራሱን ካልተወ በስተቀር) 50% መግባባት እንደማይችል ገልጸው፥ “ይህ እውነት ነው” ብለዋል።

ሆነም ቀረ፥ መጽሐፍ ቅዱስ ለሰዎች በቀለለ ቋንቋቸው መቅረቡን መቃወም፥ ሃይማኖታዊ ተልዕኮ ከሌለው በስተቀር ዓላማው/ጥቅሙ ምንድነው ሲሉ አቶ አይናለም ጠይቀዋል። መደበኛ ትምህርትስ ቢሆን የባልታ ሶቄ ህጻን በቋንቋው ቢማር፥ በጤናማ ጭንቅላታችን ልንቃወም ነው ሲሉ አበክረው ተናግረዋል። የቦንኬው ልጅ “Aso hayssi aazee?” ሲል የባልታው ልጅ፦ “Ye Gero hay alaa?” እንደሚል ጠቅሰዋል።

የባልታው/የሻራው/የዛርጉላው/የዶርዜው/የጋንታው ልጅ ማኅበራዊ ግዴታው ስለ ሆነበት፥ መደበኛውን ጋሞኛ የሚለማመደው በሂደትና ከቤት ወጥቶ መሆኑን የገለጹት አቶ አይናለም፥ ነገር ግን መደበኛው ሥርዓት ለቦንኬው፣ ለካምባው፣ ለዲታው፣ ለወዘተው ልጅ እንደሚያደላ ገልጸዋል። ስለዚህ ለሁሉም ቋንቋዎች ተናጋሪዎች እኩል ዕድል ቢሰጥ፥ ለቋንቋዎች ዕድገትና ለሰው ልጆች ደስታ፥ ሚናው ጉልህ መሆኑን አብራርተዋል።

አብዛኞቻችን የደቡብ ኢትዮጵያ ልጆች አማርኛን እንኳን በውጤታማነት መጻፍ የቻልነው መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ በማንበባችን መሆኑን የገለጹት ተንታኙ፥ አማርኛ በአገሪቱ ደቡብ እጅግ እንዲስፋፋም የሚሲዮናውያን የመጽሐፍ ቅዱስ የስርጭት ሥራ ትልቅ ድርሻ እንደነበረው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር የምሥረታ ዓላማው መጽሐፍ ቅዱስንና የምስራቹን ቃል ተናጋሪ ባላቸው የአገሪቱ ቋንቋዎች በሙሉ ለሁሉም የሰው ልጆች ማድረስ እንጂ መንገድ፣ ንፁህ ውሃ፣ ትምህርት ማስፋፋት እና ጤና ማዘመን እንዳልሆነ፣ ይህ የመንግሥት ሥራ መሆኑን አቶ አይናለም አብራርተዋል።

የጋሞ ልህቃን በየጊዜው የሚያነሱት፦ “የጋሞ ዞን ቋንቋዎች ልዩነት ዘዬ ነው” የሚል መሆኑን የጠቀሱት ተንታኙ፥ ዘዬስ ቢሆን በዘዬ የሚለያይ ህዝብ እስካለ፥ በዘዬም ቢሆን መጽሐፉ ቢጻፍ ህዝብ ይጠቀማል እንጂ ምኑ ይጎዳል ብለዋል። ነገሩ ግን ከዚያም ያለፈ መሆኑን ጠቁመዋል።

የዎላይታ በርጋጊዎች እንደ መብት ፋና ወጊ ስላስጮኹት፥ የጋሞ በርጋጊዎችም እንደ ከዚህ ቀደሙ የእልህ ልማዳቸው ይህን ድንቅ ሥራ መቃወማቸውና መጠለፋቸው ግን እንደሚገርም አቶ አይናለም ተናግረዋል። ለምሳሌ ቁጫ ወረዳዎች ውስጥ ከቁህዴፓና ከደጋፊዎቹ የፖለቲካ እንቅስቃሴና ምርጫ የተነሳ፥ በህዝቡና በፓርቲው ደጋፊዎች ላይ በመንግሥት ፊታውራሪነት ይፈፀም የነበረውን ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ፥ የዎላይታ በርጋጊዎችና የሚዲያ ሚሊሺያዎች ስለሚያስጮኹት ብቻ (ነገሩ እውነት ቢሆንም)፥ የጋሞ ልህቃን በሰብዓዊነት መኰነን እንዳልቻሉ አንስተዋል። 

ዘይሴ ላይ የቀጠለውንም ቀውስ እንዲሁ መሆኑን ጠቁመዋል። እዚህ ላይ ያንን ድርጊት ለመኰነን በቂ ጥረት ያደረገውን (የዎላይታ ሚሊሺያውንም፥ ቁህዴፓንም፥ የጋሞ ዞን የመንግሥት መዋቅርንም) በድፍረት ይወቅስ የነበረውን ወንድማቸውን (ደፋሩ ደበበን) መቼም እንደማይረሱት ገልጸዋል።

ይልቅ ይህ የትርጉም ሥራ በጎ ነውና እጅግ ሊበረታታ እንደሚገባ አቶ አይናለም አሳስበዋል። በእውነቱ ሠርጉና ምላሹ ለጋሞ ህዝብ እንደነበር ገልጸው፥ ለዎላይታ ቀድሞ ባይተረጎም ኖሮ፥ የዎላይታ የመረብ ሚሊሺያዎች የዶርዜን ትርጉም በመቃወም የዐየር መረቡን ያጠቡ ነበር ብለዋል። አንድ ቋንቋ ሃይማኖታዊ መጽሐፍት ሲጻፉበት በህዝብ ህሊና ጠልቆ ይቀበራልና ቋንቋው እጅግ የመልማት ተስፋ እንዳለው ተናግረዋል።

አሁንም የዎላይትኛ ቋንቋን ምሳሌነት ማንሳት እንደሚፈልጉ የገለጹት አቶ አይናለም፥ የዎላይትኛ ቋንቋ በጥበብ ተውቦ በጋሞ፣ በጎፋና በዳውሮ ምድሮች እጅግ እንዲሸጥ ያደረገው የዘማሪዎችና የሰባኪዎች ሥራ መሆኑን ተናግረዋል። በተለይም ዝማሬ የጥበብ ሥራ ነውና ከቋንቋ ጋር ስሜት እንደሚፈጥርና ፍቅር እንደሚያስይዝ ገልጸዋል። የእነ ደስታ ቢራሞን፣ የእነ ዻውሎስ ካባቶን፣ የእነ ዮሐንስ ዳላቾን፣ የእነ ኢያብ ዳንኦን፣ የእነ ታይባ ዋጄን፣… ውብ በዎላይትኛ ቅኔ የተዘመሩ መዝሙራት መቼም እንደማይረሱ ተናግረዋል። ዎላይትኛን በጥበብ በማሻገርና በማስፋፋትም የእነዚያ መንፈሳዊ ዝማሬዎች ሚና ግዙፍ መሆኑን ገልጸዋል። 

“ዻውሎስ ጋሞ ነው፥ ታይባላ ዳውሮ ነው” የሚሉትን እንደሚያውቁ ጠቅሰው፥ ነገር ግን የዘመሩት በዎላይትኛ መሆኑን አንስተዋል። ታይባላ፥ በዳውሮኛም ዘምሮ እንደሚያውቅ ጠቅሰው፥ “መቸም ‘ዎላይትኛ በዻውሎስ ካባቶ ሲሆን ጋሞኛ ነው፥ ዎላይትኛ በታይባላ ዋጄ ሲሆን ዳውሮኛ ነው’ እንደማትሉኝ አውቃለሁ” ብለዋል።

የጋሞ የሚዲያ ልህቃን (በርጋጊዎች)፥ በዎላይታ የሚዲያ ሚሊሻዎች ተደናብረውና ተጠልፈው፦ “በእኔ ቋንቋ መጽሐፍ ተጻፈ” ብለው ሰሞኑን ሙሾ ማውጣታቸው በምንም መስፈርት ተገቢነት እንደሌለው አቶ አይናለም አጥብቀው ተናግረዋል። እውነት ነው ጋሞ ዞን ውስጥ ብዙ ቋንቋዎች እንዳሉ አንስተዋል። 

ነገር ግን እንዲያው እውነት ለመናገር፥ ጋሞ ዞን ውስጥ ያሉ ቋንቋዎች ልዩነታቸው አንዳንዶች እንደሚሉት “በጎጃምና በጎንደር የአማርኛ ቅላጼዎች መካከል እንዳለው ዓይነት” ነውን? ሲሉ ጠይቀው፥ “ጨርሶ አይደለም፤ ከዚያ እጅግ በጣም የሰፋ ነው” ብለዋል። የትኛው ቋንቋ የየትኛው ቋንቋ ዘዬ እንደ ሆነ ማን ያውቃል? ካልተካካድንና “ዐይኔን ግንባር ያድረገው” ካላልን በስተቀር፥ ወላይትኛ የሚያወራ (በመቶ ሺሆች የሚቆጠር) የጋሞ ዞን ህዝብ (ብሔረ ጋሞ) አለ ሲሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የመጽሐፍ ቅዱስ ማህበር በማብራሪያ መግለጫው እንዳስቀመጠውም በኦሮምኛ በአርሲ ዘዬ፣ በጉጂ ዘዬ እና በምሥራቅ ኦሮምኛ ዘዬ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራዎች መከናወናቸውን አቶ አይናለም አውስተዋል። እንዲሁም በጉሙዝኛ፥ በደቡብ ጉሙዝና በሰሜን ጉሙዝ ዘዬዎች የትርጉም ሥራዎች መሠራታቸውን፣ በጉራጌኛም በቸሃ፣ በቀቤና፣ በመስቃንና በክስታኔ ዘዬዎች የተሠሩ የትርጉም ሥራዎች መኖራቸውን መጥቀሳቸውን ገልጸዋል።

ታዲያ በእነዚያ ሥራዎች የበሸቀ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበሩንም ያስጠነቀቀ፣ በመረብም በመሬትም ማኅበሩን የከሰሰና አብዮት የጠራበት የኦሮሞ፣ የጉራጌና የጉሙዝ ልህቅ እንዳልሰሙ የገለጹት አቶ አይናለም፥ “የጋሞ ልህቃን ምን ነካቸው?” ሲሉ ጠይቀዋል።

የወላይታ በርጋጊዎች የጋሞ በርጋጊዎችን ለማብሸቅ፥ ይህን አጀንዳ ከዐየር ቀልበው ሰርግና ምላሽ ሲያደርጉት፥ የጋሞ በርጋጊዎች ደግሞ ወዲያው በሽቀውላቸው የለቅሶ/የሙሾና የተዝካር አደረጉት ሲሉ ተችተዋል።

ይህ ሥራ በማናችን ቢደገፍ ለቋንቋው ዕድገት ጠቃሚ መሆኑን አቶ አይናለም አብራርተዋል።

ነባር ልዩነትን መካድ የህዝብ ውግንና አይደለም ያሉት ተንታኙ፥ መጽሐፉ በየዘዬው (በሌሎችም) ቢተረጎም ጥቅም እንጂ ጉዳት እንደሌለው ገልጸዋል። እንዳልኩት ገና በባልታም፣ በጋንታም፣ በሻራም፣ በወዘተም እንደሚተረጎም ጠቅሰው፥ ልንደግፈው እንደሚገባ አሳስበዋል። ይህ ለጋሞ ህዝብ በረከት ነው እንጂ ማንነቱ ላይ የሚመጣ አንዳች አደጋ አይደለም ብለዋል።

ነባሩን ችግር አንካድ ሲሉ አቶ አይናለም ገልጸዋል። ለምሳሌ፦ የባልታ ዬሌን organic ህጻን ወስደን ከቦሮዳ ጎቾ organic ህጻን ጋር ብናስቀምጥ፥ ሊግባቡ እንደማይችሉ ጠቁመዋል። የወላይታ ሁምቦን፣ የጎፋ ዛላን እና የጋሞ ቦንኬን organic ህጻናት አንድ ላይ ብናስቀምጥ፥ በየቅላጼዎቻቸው/በየዘዬዎቻቸው እየተሳሳቁ እንደሚግባቡ ተናግረዋል። የዶርዜና የባልታ ህጻናት ግን ከዚህ እንደሚለዩ ገልጸዋል። የቦንኬ ዬላ ቀበሌ ህጻንና የባልታ ሶቄ ቀበሌ ህጻን መግባባት እንደማይችሉ ጠቅሰው፥ “ይህ ቲዮሪ አይደለም፥ አውቀዋለሁ” ብለዋል። 

እርግጥ ነው የባልታ or የዛርጉላ ልጅ ትንሽ አደግ ሲል ተንቀሳቅሶ conventional ጋሞኛን እንደሚለማመድ ገልጸዋል። እሳቸው ባልታ ቶላታ ሲሠሩ፥ በመደበኛው (እሳቸው በማውቀው) ጋሞኛ ራሳቸውን effectively የማይገልፁ ዐዋቂዎችን ሁሉ እንደሚያውቁ ተናግረዋል። “Ta Gamothoy izas geluwa, izas dhaacethon yootuwee?” ሲሉ የቡድን መሪዎች መልዕክቱን እንደተረጉሙላቸው ገልጸው፥ “ይህ ሀቅ ነው፤ የምዋሽበት ምንም ምክንያት የለኝም” ብለዋል።

እውነት ለመናገር ወላይትኛና conventional ጋሞኛ ያላቸው ልዩነት በጣም ጥቂት መሆኑን አቶ አይናለም ገልጸዋል። የወላይታ ኦፋ/የቦዲቲ/የሁምቦ… የጋሞ ካምባ/የቦንኬ/የዲታ/… ልጆች ፍፁም እንደሚግባቡ ተናግረዋል። የባልታና የቦንኬ ልጆች ግን፥ የባልታው ልጅ፦ “Yeno waakkonee, allolayte, ye gero aala wala… ማለት ቢጀምር ከቦንኬው ልጅ ጋር እንደማይግባቡ ገልጸዋል። ዘንድሮ ግን ሽማግሌዎች ክደው መቆሙን አንስተዋል። እርግጥ ነው ከባልታ ጋር የሚዋሰኑ የቦንኬ ቀበሌያት (ለምሳሌ የካሎ ጋጉላ ምዕራቡ) ባልትኛ እንደሚያወሩ ተናግረዋል።

እሳቸው ይህንን የትርጉም ሥራ በዲሞክራሲያዊነትና በሰብዓዊነት እንደ በጎ እንደሚወስዱት ገልጸዋል። ነገር ግን የወላይታ በርጋጊዎች የጋሞ በርጋጊዎችን ለማብሸቅ ሲያስጮኹትና ሠርግና ምላሽ ሲያደርጉት፥ የጋሞ በርጋጊዎችም ሙሾና ተዝካር ማድረጋቸው እንደሚያሳዝናቸው ተናግረዋል።

“የብሔር ብሔረሰቦች መብት ይከበር” ሲባል፥ “ይህ የኢጣሊያና የግብጽ ተልዕኮ ነው” ይባል እንደነበር እና ዛሬም የሚሉ እንዳሉ አቶ አይናለም አንስተዋል። መጽሐፍ ቅዱስ በየህዝቦች ቋንቋ ተተርጉሞ የመቅረቡን አጀንዳ፦ “ኢትዮጵያን የማዳከምና የማፍረስ የጀርመኒ ሚሲዮናውያን ተልዕኮ ነው” እንደሚሉ እና እስከ ዛሬም እንደሚቀጥሉ ገልጸው፥ “ግን አይደለም” ብለዋል።

ይልቅ ይህ በጎ ሥራ ነውና እጅግ ሊበረታታ እንደሚገባ አቶ አይናለም አሳስበዋል። ቆም ብለው ካሰቡ፥ ሠርጉና ምላሹ ለጋሞ ዞን መሆኑን ገልጸዋል። ይህ ሥራ በተዘዋዋሪነት ለጋሞ ዞን ቋንቋዎች ዕድገትና የጋሞ ዞን አንድነትና ሥልጣኔ እጅግ በጣም ምሰሶ ነውና ቢደገፍ እንደሚሻል ተናግረዋል። ወደ ፊት በባልትኛም፣ በጋንትኛም፣… እየተተረጎመ ቢስፋፋ ጥቅም እንጂ ጉዳት እንደሌለው ገልጸዋል። የጋሞ በርጋጊዎች ከማመፃቸውና መንጋውንም ከማሳመፃቸው በፊት፥ ቆም ብለው ቢያስቡ ጥሩ መሆኑን አሳስበዋል።

በአቶ አይናለም ታደሰ ጥልቅ ትንታኔ እና አቋም መሰረት፣ የቋንቋዎች እና የዘዬዎች ልዩነት እንደ መከፋፈያ ሳይሆን እንደ ህዝብ ሀብት ሊወሰድ እንደሚገባ ተንታኙ አጽንኦት ሰጥተዋል። አቶ አይናለም አበክረው እንደገለጹት፣ መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ሌሎች የዕውቀት ሥራዎች በህዝቦች የየራሳቸው አፍ መፍቻ ቋንቋና ዘዬ መተረጎማቸው የቋንቋዎችን ዕድገት፣ ማህበራዊ ስልጣኔ እና የህዝብን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ እንጂ ማህበራዊ ትስስርን የሚያፈርስ አደጋ አይደለም። 

በመሆኑም በልህቃንና በፖለቲካ አክቲቪስቶች (“በርጋጊዎች”) የሚደረጉ ከንቱ የፖለቲካ ውዝግቦችና ተቃውሞዎች ሊቆሙ እንደሚገባ፣ ይልቁንም የቋንቋዎችንና የህዝቦችን እውነተኛ ነጻነትና ዕድገት በሚያስከብሩ በጎ ተግባራት ላይ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ ተንታኙ በጥብቅ አሳስበዋል።

                     WT Media | Voice of Marginalized Community