የቀጠለው የሞያሌ ግጭት እና ሰብዓዊ ቀውስ

የኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ ከተማዋ ሞያሌ ግጭት ከተከሰተ ከሁለት ሳምንታት በላይ ቢሆነዉም ግጭቱ ዛሬም ድረስ ተባብሶ መቀጠሉ እየተነገረ ነው። በአስተዳደር ወሰን ውዝግብ የጀመረው በከባባድ መሳሪያ ጭምር ታግዞ በቀጠለዉ ግጭት የሰዎች ህይወት ጠፍቷል ንብረት ወድሟል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ወደ ኬንያ ተፈናቅለዋል፡፡

የኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ ከተማዋ ሞያሌ ግጭት ከተከሰተ ከሁለት ሳምንታት በላይ ቢሆነዉም ግጭቱ ዛሬም ድረስ ተባብሶ መቀጠሉ እየተነገረ ነው። በአስተዳደር ወሰን ውዝግብ የጀመረው ይህ ግጭቱ በከባባድ መሳሪያ ጭምር ታግዞ በመቀጠሉ የሰው ህይወት ቀጥፏል፣  በርካታ ንብረትንም አዉድሟል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎችን ወደ አጎራባች አገር ኬንያ አፈናቅሏል። ግጭቱ እስካሁን አለመገታቱና የተናፈቀው ሰላምም አለመመለሱን አካባቢዉ ላይ የሚገኙ ነዋሪዎች እየገለጹ ነው፡፡

ጥቅምት 08 ቀን 2019 ዓ.ም. የክልላዊ ሰንደቅ ዓላማ አሰቃቀል የአስተዳደር ወሰን ውዝግብ በማስነሳቱ የአንዲት የ13 ዓመት ታዳጊ ህይወት ካለፈ በኋላ በደቡባዊ የኢትዮጵያ ጠረፍ ከተማ ሞያሌ የተነሳው ግጭት ሁለት ሳምንታትን ቢሻገርም ዛሬም እልባት አልተገኘለትም፤ ግጭቱም አልበረደም። አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የከተማዋ ነዋሪ እንደተናገሩት ባለፉት ሁለት ሳምንታት የታየዉ ግጭት ብርቱ ጉዳት ማስከተሉን ተናግረዋል። “ከባድ ጦርነት ሲካሄድባት የከረመችው ሞያሌ ከባድ ጊዜን እያሳለፈች ትገኛለች” ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ በተነሳው ከባድ ግጭት ከሁለቱ በኩል ማህበረሰቡ ወደ ተለያዩ አቅጣጫውች ለመሰደድ ተገዷል ብለዋል፡፡

ለዶይቼ ቬለ አስተያየታቸውን የሰጡት ሌላው የሞያሌ ከተማ ነዋሪ፤ “አሁንም የሚደረገው የተኩስ ልውውጡ እንደቀጠለ ነው፡፡ ተኳሾቹ ሲደክማቸው ብቻ ነው የሚያርፉት፡፡ በዚህ በቀጠለው ተኩስ ሰው እየተሰደደ ለሆዱ የሚቀምሰውም ፈተና እየሆነበት ነው” ብለዋል፡፡ ሌላ አንድ የሞያሌ ከተማ ነዋሪ በበኩላቸዉ በሰጡት አስተያየት፤ “ከባድ የጦር መሳሪያ እየተወረወረ የሰው ቤት ላይ እየወደቀ እያቃጠለ ነው። አሁን አንድ የሰላማዊ ሰው ቤትን እሳት አጥፍተናል” በማለት የቀውሱን መቀጠል አመላክተዋል።

በ መንግስት ከተማዋን ለማረጋጋት የተመለከቱትም እንቅስቃሴ ነዋሪዎቹ ተመልክተውት ይሆን? ነዋሪዉ እንደተናገሩት “አልፎ አልፎ ከተማዋ የመረጋጋት መልክ ይታይባታል፡፡ ከፌዴራል የመጡ የጸጥታ አካላትም ግጭት አቁሙና እርቅ አውርዱ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። ፍላጎት የሚሳይም አሻፈረኝ ብሎ ተኩሱን የሚቀጥልም አለ” ሲሉ፤ ሌላውም አስተያየት ሰጪ በፊናቸው፤ “የፌዴራል መንግስትም ሆነ የሁለቱ ክልሎች መንግስታት ሰላም ለማውረድ ጥረት ሲያደርጉ አስተውለናል፡፡ ከተማዋ ለግማሽ ቀንም ለሙሉ ቀንም ሰላም ትሆንና መልሳ ወደ ግጭት አውድማነት ትገባለች፡፡ የከተማዋ መሃል ላይ ነው ጦርነት የሚካሄደው” በማለት ግጭት የማስቆም ጥረት እስካሁን እንዳልሰመረም ገልጸዋል፡፡

አስተያየት ሰጪዎቹ የሞያሌ ነዋሪዎች ግጭቱ ከሞያሌም አልፎ ወደ ሌሎች አከባቢዎች እንዳይዛመት እየሰጉ ነው፡፡ “በከተማዋ ዳርድንበርና በሌሎች ወረዳዎች ግጭቱ እንዳይዛመት ስጋቱ አይሏል” ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ በተለይም በሞያሌ አቅራቢያ በሚገኙ ሶስት የአዋሳኝ ወረዳዎች ላይ ስጋቱ ከፍ እያለ በመምጣቱ ከወዲሁ ቀዬያቸውን የለቀቁ መኖራቸውንም ገልጸዋል። ሌላኛውም አስተያየት ሰጪ ቀጥለው በሰጡት አስተያየት፤ “መልካ አሎ የሚባል ወደ ነገሌ ቦረና አቅራቢያ ተኩስ ልውውጥ መከሰቱን ሰምተናል፤ መሃል የገባም ሃይል የለም” ብለዋል፡፡

ሊገታ ባልቻለው በዚህ የድንበር ከተማዋ ሞያሌ ግጭት ወደ ኬንያዋ ሞያሌ የሰሜናዊ ግዛቷ ማርሳቤት የተሻገሩ ተፈናቃዮች ቁጥር 50 ሺህ ማለፉን የዓለማቀፉ ፍንሰተኞች ድርጅት IOM መረጃ ያሳያል፡፡ በግጭት ሽሽቱ የሰዎች ፍልሰት መቀጠሉን ያመለከተው ድርጅቱ ምናልባትም በቅርብ ቀናት የሚፈልሱ ሰዎች ቁጥር ወደ 80 ሺህ እንደሚደርስ ግምቱን አስቀምጧል። IOM ለሰብዓዊ እርዳታው ምላሽ በግምቱ መጠን ዝግጅት ለማድረግ ረጂ ተቋማት እየተንቀሳቀሱ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡

የሞያሌ ከተማዋ ነዋሪዉ በሰጡት አስተያየት ድርጅቱ ካስቀመጠዉ ግምት ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡ “በሞያሌ የንግድ ቤቶች ሱቆች የሰዎች ቤት በስፋት ተቃጥሏል” የንግድ ከተማዋን ጭር ወዳለ ስፍራ ቀይሮታል፤ ምንም አይነት የሰው እንቅስቃሴ ብሎም የትራንስፖርት እንቅስቃሴ የማይታይባት ከተማ ሆናለች” ሲሉ ገልጸዋል። በግጭቱ የብዙ ሰዎች ህይወት እንደጠፋ እንደሚታመን አስተያየት ሰጭዉ ቢጠቁሙም፤ ተጨባጭ መረጃ ግን እንደማይኖራቸዉ ተናግረዋል። ግጭቱን በተመለከተ በ ኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት በኩል የተሰጠ ማብራሪያ እስካሁን የለም።