ያለ ምርጫና ኦዲት 15 ዓመታት፤ የዎላይታ ቻምበር አመራሮች ሰብዓዊነት የጎደለው የሱቆችና የአክሲዮን ማጭበርበር ተጋልጧል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በዎላይታ ዞን የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት (ቻምበር) ከፍተኛ አመራሮች አካባቢ የተፈጸሙ መጠነ ሰፊ የሙስና፣ የንቅዘት እና የማጭበርበር ተግባራትን የሚያጋልጡ መረጃዎች ለ WT Media ደርሷል።
ከምክር ቤቱ የቀድሞ የቦርድ አባል የደረሱን ሰነዶች እና መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ ተቋሙ ለበርካታ ዓመታት ያለ ምንም ግልጽነት እና ሕጋዊ ተጠያቂነት በጥቂት ግለሰቦች አምባገነናዊ ቁጥጥር ሥር ወድቆ ይገኛል።
በደረሱን ሰነዶቹ መሠረት ዋና ዋና የተጋለጡ የሙስና እና የሕግ ጥሰት መካከል የማኅበሩ አመራር አባላት ላለፉት 15 ዓመታት ያህል ምንም ዓይነት ሕጋዊ የቦርድ ምርጫ ሳይካሄድ በሥልጣን ላይ ይገኛሉ።
ከተለያዩ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ከፍተኛ መጠን ያለው ገቢ የሚሰበሰብ ቢሆንም፣ የድርጅቱ የፋይናንስ እንቅስቃሴ በገለልተኛ ኦዲተር ተመርምሮና ተፈትሾ የሚያውቅበት አሠራር የለም እንዲሁም መንግሥት ለምክር ቤቱ በሰጠው ቦታ ላይ “ግንባታ እያካሄድን ነው” በሚል ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ የወጣ ቢሆንም በቦታው ላይ የታየው ግንባታ እጅግ አነስተኛ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ የተገነቡት ሱቆች ያለ ምንም ግልጽ የጨረታ ሂደት ለዘመድ አዝማድ፣ ለጓደኛ እና ለአመራሮቹ ራሳቸው ተከፋፍለው የግል መጠቀሚያ ሆነዋል።
እንደ መረጃው ከሆነ የመንግሥት እና የተቋም ሀብትን አለአግባብ መጠቀም ለቻምበሩ ከመንግሥት በሕገ-ወጥ መንገድ የተሰጠ ተሽከርካሪ፣ ላለፉት 12 ዓመታት ከምክር ቤቱ በጀት ነዳጅ እየተሞላበት የቁልፍ አመራሮች የግል መጠቀሚያ ሆኖ ቆይቷል።
ከሁሉ በላይ ሌላው አሳሳቢው ድርጊት በዎላይታ ሶዶ መርካቶ ገበያ ስም ሕገ-ወጥ አክሲዮን በማደራጀት እና በመሸጥ፣ ከንግዱ ማኅበረሰብ በርካታ ሚሊዮን ብሮችን በመሰብሰብ ለግል ጥቅም ማዋላቸው ነው።
ከንግዱ ማኅበረሰብ ዓመታዊ የንግድ ፈቃድ ዕድሳት ጋር ተያይዞ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ የሚሰበሰብ ቢሆንም፣ አመራሮቹ “ምክር ቤቱ ገንዘብ የለውም” የሚል ማታለያ መልስ ይሰጣሉ።
ይህንን ሕገ-ወጥ አሠራር እና የምዝበራ መረብ በጽኑ በመቃወሙ ምክንያት ከቦርድ አመራርነቱ የተወገደ የቀድሞ የቦርድ አባል እነዚህን መረጃዎች ያቀረበልን ሲሆን WT Media ከጉዳዩ ጋር የተያያዙ በርካታ ዝርዝር የሰነድ ማስረጃዎች የደረሱት በመሆኑ በቀጣይ ቀናት አንድ በአንድ ለሕዝብ ይፋ የሚያደርግ ይሆናል።
WT Media ሁልጊዜም ቢሆን የነፃ፣ ሚዛናዊ እና ገለልተኛ ጋዜጠኝነት መርሆዎችን የሚያከብር በመሆኑ በዚህ ዘገባ ላይ ስማቸው የተነሳው የዎላይታ ዞን ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አመራሮች ለቀረቡባቸው የሙስና እና የሕግ ጥሰት ክሶች መልስ፣ ማብራሪያ ወይም አስተያየት መስጠት የሚፈልጉ ከሆነ የሚዲያችን በሮች ክፍት መሆናቸውን በአክብሮት እናስታውቃለን።
WT Media | Voice of Marginalized Community