1794498728910

በኢትዮጵያ፣ አማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ጠለምት ደጃች ሜዳ እና ጃን አሞራ ወረዳዎች በተከሰተው የከፋ ድርቅ ምክንያት ነዋሪዎች ለከፍተኛ ረሃብና ለስደት መዳረጋቸው ተሰምቷል።

የአካባቢው ነዋሪዎችና የቀበሌ አስተዳዳሪዎች አንዳስታወቁት ባለፈው ክረምት በቂ ዝናብ ባለማግኘታቸው ማህበረሰቡ ለከፋ ረሃብና ስደት ተዳርጓል።

አንድ የአካባቢዉ ነዋሪ እንደተናገሩት፤ «ድርቁ አለ፤ ሕዝቡም በስደት አለቀ፤ ምን እንድርግ? “አይዟችሁ” እያሉ ሐምሌን ነሐሴን መስከረምን ፤ እርዳታ ይመጣልናል ብለን ጠበቅን ፤ አሁን ግን ህዝቡ አካባቢዉን ጥሎ ሙልጭ ብሎ ጠፍቷል» ብለዋል።

ህዝቡ ወዴት ተሰዶ፤ የት እንዳደረ አናዉቅም። ገበሪዉ ያለዉን በሪ እና የቤት እንስሳ በርካሽ የሸጠ አለ፤ የሚገዛም የለም።

እንደ ዶቼ ቬለ ዘገባ 60 ሺህ ይሸጥ የነበረዉን በሬ 15 ሺህ ብር እየሸጠ የስደት ስንቅ አድርጎት ከአካባቢዉ ወቷል።

የየረን ቀበሌ አስተዳዳሪ በሰጡት ማብራሪያ፣ በቀበሌው በረሃብ ምክንያት በቀጥታ የሞተ ሰው ባይኖርም፤ በምግብ እጥረትና በረሃብ ሳቢያ ከባድ ህመም ላይ የወደቁ እና ለሞት የተጋለጡ ዜጎች መኖራቸውን አስታውቀዋል።

​በጦርነት እና በተለያዩ ሁነቶች ተጎድቶ የነበረው የዚህ አካባቢ ህብረተሰብ፣ አሁን ደግሞ በከፋ ድርቅና በረሃብ ሳቢያ ማህበረሰቡ መበታተኑ አሳሳቢ መሆኑ ተገልጿል።

የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት እና ሰብአዊ ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች በአፋጣኝ ድረንታ እንዲደርሱላቸው ነዋሪዎችና አስተዳዳሪዎች ጥሪ አቅርበዋል።