በገንዘብ ማስተርስ ድግሪ የሚሸጥበት፣ ተማሪዎች የፈለጉትን ውጤት በገንዘብ የሚያገኙበት ዎላይታ ሶዶ ዩንቨርስቲ
በWT Media የምርመራ ዘገባ ክፍል ታዋቂ የመንግስት ዩንቨርስቲ በሆነው በዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ሬጅስትራር እና የመጀመሪያ አመት ተማሪዎች ዲን (Freshman) ዲን ቢሮዎች ዙሪያ የተፈጸመ አስደንጋጭ የሙስና፣ የተማሪዎች ውጤት ሺያጭ እና የኃላፊነት ንግድ ቅሌት ይፋ ሆኗል።
WT Media ከዩኒቨርሲቲው መምህራን፣ ከተጎጂ ተማሪዎች እንዲሁም ጉዳዩን በቅርበት ከሚያውቁ አካላት በሰነድ አስደግፎ የሰበሰበው መረጃ እንደሚያሳየው፤ ተቋሙ ለከፍተኛ ብልሹ አሠራር እና ለአስተዳደራዊ ቀውስ ተጋልጦ ቆይቷል።
በተለይም በዩኒቨርሲቲው የሬጅስትራር እና አልሙኒ ዳይሬክተር ሆኖ በሰራው ዶ/ር በረከት ተሰማ እንዲሁም የፍሬሽማን ዲን በነበሩት አቶ እሸቱ ተስፋዬ የተመራው ህገ-ወጥ ተግባር ማህበረሰቡን ለከፍተኛ እንግልት፣ ዩንቨርስቲውን ለውድቀት ዳርጎታል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት የሬጅስትራር ቢሮ እና የፍሬሽማን ዲን ቢሮ ተቀናጅተው ተማሪዎች ወደ ፈለጉት የትምህርት መስክ (Field) ለመሰማራት ሲያስቡ ከ20 እስከ 30 ሺህ ብር ድረስ እየተቀበሉ ሲቸበችቡ ቆይተዋል።
የሬጅስትራር እና አልሙኒ ዳይሬክተሩ የነበሩት ዶ/ር በረከት ተሰማ ከ13 በላይ ተማሪዎች የማስተርስ (Master’s Degree) ዲግሪ በህገ-ወጥ መንገድ ሰርተው መስጠቷቸው ተረጋግጧል።
በተጨማሪም ተማሪዎች በመጀመሪያ ዓመት ቆይታቸው ማግኘት የማይችሉትን ውጤት (Grade) በራሱ ጊዜ እያስተካከለ ወደ ፈለጉት መስክ እንዲገቡ በማድረግ ከ20 እስከ 30 ሺህ ብር ሲቀበል እንደነበር ተገልጿል።
ከ10 እስከ 20 ሺህ ብር እየወሰዱ ያለ ኮርስ አስተማሪ እውቅና የሚሰጡበት አሰራር ተዘርግቶ ነበር። ባለጉዳዮች በአንድ ቀን ማለቅ ያለባቸውን አገልግሎቶች ከሳምንት በላይ እንዲሰቃዩ ይደረግ ነበር።
በምስክርነትም አንድ አካባቢውን የሚያውቅ አካል የራሱ ዘመዶች ውጤት እንዲስተካከልላቸው 24 ሺህ ብር እንደተወሰደባቸው አስመስክሯል።
የፍሬሽማን ዲን የነበሩት አቶ እሸቱ ተስፋዬ ተማሪዎች ያለ በቂ ውጤት ወደ ፈለጉት የትምህርት መስክ እንዲገቡ በማድረግ ከ20 ሺህ ብር በላይ ሲሰበስቡ እንደነበር ተመላክቷል።
አሁን ላይ ሁለቱም ኃላፊዎች ከየቦታቸው መታገዳቸው እየተሰማ ነው።
ጉዳዩ ከዚህም የባሰ በመሆኑ ከብሔራዊ የፈተና መውጫ (Exit Exam) ጋር በተያያዘ ትልቅ አሻጥር ተፈጽሟል።
የግቢው የአይቲ (IT) ባለሙያዎች ከኃላፊዎቹ ጋር በመነጋገር አንድ የመፈተኛ ኮምፒዩተር ላብ (Computer Lab) ክፍል ኮድ (Code) በመውሰድ ለሌሎች አስተማሪዎች እንዲሰሩ አድርገዋል።
በሰኔ እና ጥር 2018 ዓ.ም በተደረጉት ሂደቶች ህገ-ወጥ ሰዎችን እጅ ከፍንጅ በመያዝ ጭምር ቢጋለጡም ተገቢው እርምጃ ሳይወሰድ ቀርቷል።
ዶ/ር በረከት ተሰማ የተማሪዎች ገንዘብ ቁጭ ብሎ ሲፈርምባቸው የነበረ ሲሆን ከውጭ ደላሎች ጋር በመቀናጀት ገንዘብ ሲጋሩ እንደነበር እና ይህ ሁሉ አሰራር እስከ ከፍተኛ የዩኒቨርሲቲው ኃላፊዎች ድረስ ይታወቅ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።
ከሙስና እና ከውጤት ንግድ ባሻገር በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ለምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ የሚመደበው በጀት አጠቃቀም ከፍተኛ ጥያቄ አስነስቷል።
ለኃላፊነት በሚደረጉ ውድድሮች (የዲን፣ የዳይሬክተር እና የትምህርት ክፍል ቦታዎች) ፍትሃዊነት የጎደለው እና ብልሹ አሠራር የሰፈነበት መሆኑ ተገልጿል።
የምርምር ፕሮፖዛሎች (Proposals) ሲገመገሙ ህጉን የጣሱ፣ ሆን ብሎ በትውውቅና በግል ጥቅማጥቅም ውጤት እንዲሰጣቸው እየተደረገ እንዲያልፉ እንደሚደረጉ ተመላክቷል።
ይህ ሁሉ ሕገ-ወጥ ተግባር ሲፈጸም የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕረዚዳንት (Academic V/President) ምን እየሰራ ነበር የሚለው ጥያቄ አሁን ላይ የመምህራን እና የተማሪዎች ዋና መነጋገሪያ ሆኗል።
ሁኔታውን በቅርበት የተከታተሉት የተማሪዎች ህብረት ከትምህርት ሚኒስቴር አካላት ጋር በመተባበር ሁኔታውን አጣርተው የእገዳ ደብዳቤዎችን ማስጻፋቸው ተገልጿል።
WT Media በምርመራው ያጠናቀራቸው እነዚህ መረጃዎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለምን ያህል ኋላቀርነት፣ ዘረፋ እና የሞራል ውድቀት እንደተጋለጡ በግልጽ ያሳያሉ።
ተቋሙ ገለልተኛና ጥልቅ ማጣርያ በማድረግ ህጉን የጣሱ አካላት ለህግ እንዲቀርቡ የማድረግ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት የጠቆሙት ምንጮች WT Media ጉዳዩን በቀጣይነት አጠናክሮ እንደሚከታተለው ገልጸዋል።
በዘገባችን የተነሱትን ከባድ የሙስና እና የብልሹ አሠራር ውንጀላዎች አስመልክቶ የዩኒቨርሲቲውን አመራሮች አስተያየት ለማካተት WT Media ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ እስከ አሁን ድረስ በዩኒቨርሲቲው በኩል ምላሽ ባለማግኘቱ ሊሳካ አልቻለም።