1794842087780

በWT Media የምርመራ ዘገባ ክፍል ​በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በኧሌ ዞን በሚገኙ የተለያዩ የመንግስት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ በማገልገል ላይ የሚገኙ የመንግስት ሠራተኞች ያለ አንዳች ስምምነትና ግልጽ ሕጋዊ መሠረት በደመወዛቸው ላይ እየተደረገ ያለው ተደራራቢ ቅናሽ ከፍተኛ የኑሮ ጫና እንደደቀነባቸው ገልጿል።

ጉዳዩን አስመልክቶ ሠራተኞቹ ለ WT Media ባደረሱት ሰነድ የተደገፈ ጥቆማ ቅናሾቹ ከባለድርሻ አካላት ፍቃድ ውጪ በግዴታ በመፈጸሙ እና ቅሬታ ላነሱት አካላትም ማስፈራሪያና ዛቻ እየደረሰባቸው መሆኑን አሳውቀዋል።

​በዞኑ የሚገኙ ሠራተኞች ከሚከፈላቸው ወርሃዊ ደመወዝ ላይ የተለያዩ ተደራራቢ ቅናሾች ይደረግባቸዋል ተብሏል።

ከእነዚህም መካከል ከእያንዳንዱ የመንግስት ሠራተኛ 100% ደመወዝ በ10 ወራት ውስጥ ይሰበሰባል በሚል መርሃ ግብር፣ በየወሩ 10% የደመወዝ ቅናሽ ለ10 ተከታታይ ወራት እንዲቆረጥ መደረጉ ቅሬታ ፈጥሯዊ።

​ከዚህ በተጨማሪም 2% ለአለ ልማት ማህበር፣ 0.5% “ከተረጅነት ወደ ምርታማነት” በሚል፣ እንዲሁም በሕግ መሠረት የሚደረጉ የግብርና የጡረታ መዋጮዎች ይገኙበታል።

​ለአብነት ያህል 12,566 ብር ጠቅላላ ወርሃዊ ደመወዝ የሚያገኝ ሠራተኛ ከገቢ ግብር (2,419.80 ብር) እና ከጡረታ መዋጮ (879.62 ብር) ውጪ ተጨማሪው የ10% (1,256.60 ብር)፣ የ2% (251.32 ብር) እና የ0.5% (62.83 ብር) ቅናሾች ሲደረጉበት፤ በሠራተኛው እጅ የሚቀረው ንጹህ ገቢ ወደ 7,695.83 ብር ብቻ ዝቅ እንደሚል በሰነድ ተረጋግጧል።

ይህ ሁኔታ በወቅታዊው ከፍተኛ የኑሮ ውድቀት (የምግብ፣ የቤት ኪራይ፣ የመጓጓዣ እና የትምህርት ወጪዎች መጨመር) አኳሃን ሠራተኛውን ለከፍተኛ የህልውና ቀውስ እንደዳረገው ተመላክቷል።

​የኧሌ ዞን የመንግስት ሠራተኞች ተወካዮች ለ WT Media እንደገለፁት መሠረታዊ ጥያቄዎች “ከሠራተኞች ደመወዝ ላይ የሚደረገው 10% ቅናሽ ለ10 ወራት በየትኛው ሕግ፣ ደንብ፣ መመሪያ ወይም የሥልጣን ውሳኔ ላይ እንደተመሠረተ በግልጽ እንዲገለጽ” ብሏል።

ከዚህ ባሻገር​ 2% ለአለ ልማት ማህበር እና 0.5% “ከተረጅነት ወደ ምርታማነት” በሚል የሚደረጉ ቅናሾች ሕጋዊ መሠረታቸው እንዲጣራ፤ ከሠራተኞች የተቀነሰው ገንዘብ ለተጠቀሰው ዓላማ በትክክል መዋሉ እንዲመረመር እንዲሁም ሕጋዊ መሠረት የሌላቸው ቅናሾች ካሉ በአፋጣኝ እንዲቆሙ እና ተገቢው መፍትሔ እንዲሰጥ” የሚሉ ይገኝበታል።

​ሠራተኞቹ ለዞኑ እና ለክልሉ ሚመለከታቸው አካላት ጥያቄዎቻቸውን ቢያቀርቡም ተገቢ ምላሽ ማግኘት አልቻሉም። ከዚህ ይልቅ ጉዳዩን በመቃወማቸው እና ባለመተባበራቸው ምክንያት “ከፍተኛ መገለል፣ ጥቃት እና ስጋት እየደረሰባቸው ይገኛል” ብሏል።

​WT Media ባደረገው ተጨማሪ ማጣራት በ«የእለ ድምፅ» የተሰኙ ማህበራዊ ሚዲያ ገጾች እና መድረኮች ለዚህ ፕሮጀክት ለመተባበር ፈቃደኛ ያልሆኑ የመንግስት ሠራተኞችን ስም ዝርዝር ይፋ በማድረግ «እርምጃ እንወስዳለን» የሚሉ የማስፈራሪያ መልዕክቶች እና ዛቻዎች እየተሰራጩ መሆናቸውን ለመመልከት ችሏል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በኧሌ ዞን በሚገኙ የመንግስት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ሠራተኞች ያለ አንዳች ስምምነትና ሕጋዊ ማዕቀፍ በደመወዛቸው ላይ እየተደረገ ያለው ተደራራቢ ቅናሽ ከባድ ሰብአዊ ቀውስ እና ሕገ-ወጥነትን የፈጠረ መሆኑ ተመላክቷል።

በወቅታዊው ከፍተኛ የኑሮ ውድቀት ውስጥ ሆኖ ሀገርን እያገለገለ የሚገኘውን ሠራተኛ ከሚከፈለው አነስተኛ ደመወዝ ላይ 10% የደመወዝ ቅናሽ ለ10 ወራት፣ እንዲሁም ተጨማሪ 2% እና 0.5% ቅናሾች በግዴታ እንዲቆረጡ መደረጉ የሠራተኛውን መሰረታዊ ሰብአዊ መብት እና የኑሮ ዋስትና አደጋ ላይ የጣለ ነው ይላሉ።

​ቅሬታ ያሰሙ ሰራተኞች ከዞኑ እና ከክልሉ አካላት ተገቢ ምላሽ ባለማግኘታቸው ብቻ ሳይሆን ተባባሪ ላልሆኑ አካላት «እርምጃ እንወስዳለን» በሚል በማህበራዊ ሚዲያዎች ጭምር የዛቻና የማስፈራሪያ ርምጃዎች እየተወሰደባቸው ይገኛል።

​ይህ ድርጊት በሥራ ላይ ያለውን የኢትዮጵያ ህግ እና ሰብአዊ መብቶች የሚጥስ በመሆኑ፣ ሰራተኞቹ ተገቢው መፍትሔ እንዲሰጣቸው እና ሕገ-ወጥ ቅናሾች በአፋጣኝ እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።

WT Media ጉዳዩን በጥልቀት መከታተሉን የሚቀጥል ሲሆን የዞኑን አስተዳደር ምላሽ ለማካተት ያደረገው ጥረት በባለሥልጣናቱ ዝምታ ምክንያት ለጊዜው ሳይሳካ ቀርቷል።

Voice of Marginalized Community | WT Media